ይህ የ”እኔ እበልጣሉ፣ እኔ ነኝ የምገዛህ፣ እኔ ነኝ ስልጡን” ፖለቲካ ብዙም እንደማያስኬድ የስካሁኑ ልምድ በቂ ነውና ይቁም። እናንተ እልቂትን ስፖንሰር የምታደርጉ እስከዛሬ በጎ ፈንድና በባንክ፣ እንዲሁም በተለያዩ አግባቦች ብራችሁን ስትበትኑ የነበራችሁ የዘር ቅስቀሳ ተጋላቢዎች አቁሙ። አስቡ። መጠየቅ በመላው ዓለም ሊመጣ እንደሚችል አትዘንጉ። ዓለም አንድ መንደር ሆናለች።

የኢትዮ 12 አቋም

የምትልካት ስሙኒ፣ የምትልከው ስሙኒ ሚስጢር አይደለም። በጎ ፈንድ የደም ነጋዴዎችን የምተረዳ የምትረጂ አቁሚ። አቁም። እናቁም። በአንድ ወቅት እጅህን፣ እጅሽን፣ እጃችንን በነከርነበት የንጹሃን ጭፍጨፋ መጠየቅ ይመጣል። ገዳዮችንና አስገዳዮችን መደገፍ ሲጀመር ለህሊና ጥቁር ተባሳ ነው። ሲቀጥል በሰማያዊው ቤት ያስጠይቃል። በምድር ላይ ህግም በተመሳሳይ ለፍርድ ሰይፍ ይዳርጋል።

አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ለደም ነጋዴዎች ጀርባውን የሰጠ መሆኑ ጥርጥር የለውም። ለዚህ ማስረጃው ኢትዮጵያ በተቆሰቆሰችው የዘር እሳት መተን ሳትነድ ዛሬ ላይ መድረሷ ነው። በገራችን አንዱ ዘር ሌላው ላይ እንዲነሳ ያልተረጨ መርዝ የለም። ያልተበተነና ያልታተመ የፈጠራ ድርሰት የለም። ይሁን እንጂ የድርሰቱ ባለቤቶች የሉም። በፍርድም ይሁን በፈጣሪ ቁጣ አፈር ሆነዋል። ኢትዮጵያም ሆነች ህዝቧ ግን አሉ። ወደፊትም ይቀጥላሉ። አሁ7ን ላይ ያሉት የደም ነጋዴዎች ከቀደሙት በላይ አቅምና የተመቻቸው ሁኔታ የላቸውም። ሊኖራቸው ቢጥሩም ሊፈቀድ አይገባም።

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፣ አንቺ፣ አንተ፣ እኛ፣ እነሱ ስለምን ነው በዘር ተቧድነው፣ ከዘርም ወርደው በአካባቢነት ተሰባስበን ጠብመንጃ በመታጠቅ ገንዘብ የምናሰባስበው? ሌላውን ለመግደል? ሌላውን ዘር ለመጨፍጨፍ? ሌላውን ብሄር ለማጥፋት፣ እኮ ለምን? የዛሬ ተገዳይ ነገ ገዳይ ሆኖ ስላለመምጣቱ ምን ማስረጃ አለ? ስለምንስ ነው ማቆሚያ ከሌለው የደም አዙሪት ውስጥ የምንባዝነው? መቼ ነው የምንነቃው? ምን ስንሆን ነው የመንማረው? ከዚህ በላይ ለትምህርት የሚሆን ምን ይድረስብን?

በኢትዮጵያችን ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ያየነው እልቂት፣ መተላለቅ፣ ግፍ፣ ወንጀል፣ ጭካኔ፣ ስቃይ፣ ስደት፣ የጅምላ ግድያ፣ ረሃብ፣ የህጻናትና እናቶች ጠኔ፣ ፈር የለቀቀ የቡድን ወንጀል፣ ስቅላት፣ ውድመት … ቢትዮጵያ ድንኳን ስር ምን ያልተፈጸመ ወንጀል አለ? ሙሉ ከተማና ነዋሪዋ ሲጋዩ አላየንም? ቁማርተኞች ያሳበዷቸው ወረበሎች በዘሩ ምክንያት አባት ልጁ ፊት ሲታረድ ከማየት፣ የተገደለ ሰው ሞቱ እንደማይበቃው ተደርጎ ተሰቅሎ ሲወገር፣ ይህ ሲሆን ደግሞ ፊልም እየተቀረጸ ሌላውን በንዴት ለማነሳሳት በማህበራዊ ሚዲያ ሲሰራጭ አለየንም? እና ምንድን ነው የምንናፍቀው? ያማል!!

ኦሮሞ ዛሬ ላይ መሳሪያ አንስቶ አማራን የሚያርደው ምን ለማግነት ነው? አማራ ሆነው በከበረው የፋኖ ስም ኦሮሞን የሚያርደው (ደረጃውና መጠኑ ቢለያይም) ምን እንዲሆንለት ነው? በግልጽ መነጋገርና በፍጹም ነጻነት መረጃ ማስተላለፉ ስለማይፈለግ ወይም የዕልቂቱን ዓላማ ስለሚያስት እንጂ ኦሮሞ ክልል ገብተው የሚያርዱ በአማራ ስም የተደራጁ አሉ። ምስኪኑንን ገበሬ የሚያርዱና የሚዘርፉ አሉ። ግን አይወገዙም። አይዘለፉም። ይልቁኑም ” ጀግና” እየተባሉ በየአምቡላው ቤት ይሾማሉ። ብር ይላክላቸዋል። ” እኔም እገሌ ነኝ” ይባልላቸዋል። በድመነፍስ ሁሉም ያዜምላቸዋል። አሁን ላይ ቅርጽ እየያዘ የመጣውን የአማራ ክልል ለማፍረስ ይህ ሃይል ሌት ተቀን እየጫረ ነው። አማራ ከዚህ ምን ይጠቀማል? አፍርሶ ምን ያገኛል? ከማፍረስ በርጋታ የፖእልቲካ ስራ ሰርቶ ለውጥ ማምጣት አይሻልም? ዋ !!

ሸኔም ሆነ ማንም ስለምን ሌሎችን ትገላላችሁ? ትዘርፋላችሁ? ታፍናላችሁ? እናንተ ይህን በማድረጋችሁ ኦሮሞ ምን ይጠቀማል? ኦሮሞ ምን ያገኛል? ለኦሮሞ የወደፊት እድሉስ መላክም ይሆናል? እናንተ በግልጽ ባልተቀመጠ አጀንዳ ሌሎችን የምተገሉና በኦሮሞ ስም ራሳችሁን የሰየማችሁ ስለምን ከሌሎች የተዋለዱ ኦሮሞዎችን ታሳፍራላችሁ? ታሳቅቃላችሁ? ተቀላቅለው የተወለዱና ከኦሮሞ ሌላ ምን የማያውቁትን ስለምን ታገላላችሁ? እነሱን አግልላችሁ ስንት ሚሊዮን ኦሮሞ ልትይዙ ነው? ለመሆኑ አብዣኛው ኦሮሞ መማረሩን ታውቃላችሁ? ህዝብ እንደሰለቸው አልገባችሁም? የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ” እናንተ ግደሉ፣ እኔ ሂሳቡን አወራርዳለሁ” እያላችሁ በመግለጫ ጋጋታ እልቂት የምታውጁት እስከመቼ ነው? ምን እስኪሆንና ምን ያህል ህዝብ ሲያልቅ፣ ሲፈናቀል፣ ሲረሸን፣ ሲራብ … ነው “አሳደህ በለው” ጥሪያችሁን የምታቆሙት? እስከመቼ ነው የሰለጠነ ትግል ሸሽታችሁ ስትከፋፈሉ የምትኖሩት? የአሽከርነት ፖለቲካ የሚበቃችሁህ መቼ ነው? መቼ ነው አረጀን የምትሉት? ስልጣን ሳልይዝ እርጅናዬን አልቀበልም በሚል ህዝብ መማገድና በህዝብ ሰቆቃ ውስኪ የምታወራርዱት… ያማል። ዋ!! ለናነትም።

ዛሬ ኦሮሞ በጥይትና በደም የሚያስከበረው እስካሁን ያልተከበረለት ጥያቄው ምንድን ነው? ወለጋን ለይቶ ያስኮረፈው ጉዳይ ካለ ነጥሎ ማየት እንጂ ድፍን ኦሮሞን ባልገባውና ሊረዳው በማይችል የአካባቢያዊ የበላይነት ጥያቄ መማገድ አድሮ ዋጋ ያስከፍል ካልሆነ በቀር አሰቡት ደረጃ አያደርስም። ይህ የ”እኔ እበልጣሉ፣ እኔ ነኝ የምገዛህ፣ እኔ ነኝ ስልጡን” ፖለቲካ ብዙም እንደማያስኬድ የስካሁኑ ልምድ በቂ ነውና ይቁም። እናንተ እልቂትን ስፖንሰር የምታደርጉ እስከዛሬ በጎ ፈንድና በባንክ፣ እንዲሁም በተለያዩ አግባቦች ብራችሁን ስትበትኑ የነበራችሁ የዘር ቅስቀሳ ተጋላቢዎች አቁሙ። አስቡ። መጠየቅ በመላው ዓለም ሊመጣ እንደሚችል አትዘንጉ። ዓለም አንድ መንደር ሆናለች።

መንግስትም ከሕዝብ አብራክ የወጡ ሁሉ በፖለቲካው ሜዳ ዕኩል እንዲጫወቱ ፍቀድ። ካሳደገህ የግፍና የሴራ ፖለቲካ እሳቤ ተለይ። በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ መእራፍ በመክፈት ለመውደስና በታሪክ ለመታወስ ወስን። ህዝብ ያሻውን እንዲመርጥ ካሁኑ በልኩ ስራ። አትርመጥመጥ። በሌብነት ላይ ያዝኩት እንዳልከው አቋም ህዝብ በመረጠው እንዲተዳደር የጎን ለጎን ዘመቻህን አጠናክር። ስልጣንን ርስት አድርጎ ከመዋረድ ራስህን ጠብቅ። ሌብነት አንዱ ምንጩ ስልጣንን ርስት ከማድረግ የሚቀዳ ነውና ዴሞክራሲ ላይ በጥንቃቄ ስም በርህን አትዝጋባት።

እናንተ በተለይ በአማራና ኦሮሞ ስም የማክረር የዘር ፖለቲካ የተጠመቃችሁ ንጹሃንን አትግደሉ። አትረዱ። አታፈናቅሉ። አትዝረፉ። አታፍኑ። ከትህነግ ተማሩ። ለልጅ ልጃችሁ የደም እዳ አታኑሩ። እስከዛሬ የሆነው ይበቃልና ተጨማሪ የደም ማህተም አታትሙ። በህዝብ ስም ህዝብ ላይ ግፍ አትስሩ። ደረጃው ቢለያይም ኢትዮጵያን እያወካችሁ ያላችሁት እናንተ ናችሁና አድቡ። በዘር መደራጀት ሌላውን በዘሩ ላማጥፋትና ለመጨፍጨፍ ነውና ይቁም!! ብዙ የሚጠበቅበት የዕርቅ ኮሚሽኑ ይህ ዕገዳ እንዲጣል ቀድሞ ህዝብ ያወያይ። ሕዝብ አለ ማለት “አለ” ነውና!! የሰለቸው ህዝብ የሚለውን ያውቃል!!

Leave a Reply