ሰው በመነገድ ወንጀል ኤርትራዊው ተፈረደበት

መሀመድ አህመድ የተባለው ኤርትራዊ በፈጸመው ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል በተመሰረተበት 3 ተደራራቢ ክሶች በ15 ዓመት ጽኑ እስራትና በ105 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ ተቀጣ

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ መሀመድ አህመድ የተባለው ኤርትራዊ ዜግነት ያለው እና የመኖሪያ አድራሻው አዲስ አበባ ከተማ የነበረው ግለሰብ በፈጸመው ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 20ኛ ወንጀል ችሎት 3ተደራራቢ ክሶች መስርቶ ክርክሩን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡

ክርክሩን የመራው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 20ኛ ወንጀል ችሎት ነው።

የተከሳሽን የዋስትና መብት በተመለከተ ተከሳሽ የተከሰሰበት የወንጀል ድንጋጌ የዋስትና መብትን የሚያስከለክል በመሆኑ ጉዳዩን በማረሚያ ቤት ሆኖ ሲከታተል ቆይቷል፡፡

ተከሳሽ በ3ቱም ክሶች በሰው መነገድ እና ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ/ አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀፅ 8/1 እና 3/መ ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ነው የወንጀል ድርጊቱን የፈጸመው፡፡

የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ተከሳሽ ለጊዜው ካልተያዙ ግብረአበሮቹ ጋር በመሆን ሳላህ ዑመር አህመድ የተባለውን እና በወንጀል ድርጊቱ ለሞት የተዳረገውን ግለሰብ ቀኑ በውል ተለይቶ ባልታወቀበት ግንቦት ወር 2013 ዓ.ም በህገ-ወጥ ጉዞው ላይ የነበሩ ሌሎች 2 ግለሰቦችን ከኢትዮጵያ ግዛት ወደ ሱዳን ድንበር ለማሻገር እያንዳንዳቸው 700 የአሜሪካን ዶላር እንዲከፍሉት እና ወደ ሱዳን የሚወስዳቸውን መኪና ሊልክላቸው ይስማማሉ፣ ግንቦት 18 ቀን 2013 ዓ.ም በግምት ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት አካባቢ ለጊዜው ያልተያዘው ዑመር የተባለው ግብረአበሩ ተከሳሽ ልኮኝ ነው ተዘጋጁ መኪና ይመጣል በማለት እንዲዘጋጁ በማድረግ፤ 3፡30 ሰዓት ሲሆን ሟች እና ሌሎች 2 ግለሰቦች ወደ ነበሩበት ወደ ጎንደር ከተማ በተከሳሽ በኩል መኪና ተልኮላቸው ወደ ሱዳን እየተጓዙ እያለ አብርሀ ጅራ ወደተባለ ቦታ ሲቃረቡ የመኪናው ሹፌር እና ረዳት አብርሀ ጅራ ኬላ በመሆኑ ፍተሻ ስላለ በሞተር ነው የምትሄዱት በማለት ከመኪና ካስወረዷቸው በኋላ ለጊዜው ላልተያዙ እና በቁጥር 5 ለሆኑ ግብረ አበሮቻቸው ያስረክቡዋቸዋል፡፡ የተረከቡት ግለሰቦችም ጉዞውን በሞተር እንዲሁም በእግር ይዘዋቸው ከሄዱ በኋላ ስፍራው መለየት ባልተቻለ ቦታ ሲደርሱ ተጓዦቹ ለተከሳሽ ደውለው ስለሁኔታው ሲናገሩ በሌሎች ሰዎች እጅ እንደወደቁና የእሱ ሰዎች ባለመሆናቸው እንዲያመልጡ ሲነግራቸው 3ቱም ለማምለጥ ሲሞክሩ ግለሰቦቹ በያዙት መሳሪያ ሲተኩሱ ሳላህ ዑመር አህመድ የተባለውን ሟች የቀኝ እግር ጉልበቱ ላይ በመምታት ብዙ ደም ስለፈሰሰው ህይወቱ ያለፈ በመሆኑ ተከሳሽ በፈፀመው ሰዎችን ድንበር የማሻገር ወንጀል በዋና ወንጀል አድራጊነት ሶስት ተደራራቢ ክሶች እንደተመሰረቱበት የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ላይ ተመላክቷል፡፡

See also  እንዲገለጥልን የልዩ ሃሎችን መሟሟት ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አካሄድ ጋር እንሳፋው!

ተከሳሽ ክሱ በፍርድ ቤት ተነቦለት የወንጀል ድርጊቱን አልፈጸምኩም በማለት ክዶ የተከራከረ ሲሆን ከሳሽ ዐቃቤ ህግ በበኩሉ የወንጀሉን መፈጸም ያስረዱልኛል ያላቸውን ማስረጃ ለችሎቱ እንዲሰማ አድርጓል፡፡

ችሎቱም ዐቃቤ ህግ ምስክሮቹን ማሰማቱን ተከትሎ ተከሳሽን የዐቃቤ ህግን ማስረጃ እንዲያስተባብል ብይን የሰጠ ሲሆን ተከሳሽ ወንጀሉን አለመፈጸሜን ያስረዱልኛል ያላቸውን የመከላከያ ምስክሮች አቅርቦ ቢያሰማም የቀረበበትን ክስ እና ማስረጃ ያላስተባበለ በመሆኑ በቀረበበት 3 ክሶች የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎበት በ15 ዓመት ጽኑ እስራትና በ105 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ሲል ውሳኔውን አስተላልፏል፡፡

Leave a Reply