“መከላከያ ነገ መቀለን በይፋ ይረከባል፤ ህገ መንግስታዊ ሃላፊነቱን ይጀምራል”

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ህገ መንግስታዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ከሃሙስ ጀምሮ መቀለ እንደሚገባና የኢትዮጵያ አየር መንገድም የተለመደ አገልግሎቱን እንደሚጀምር የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የደህንነት አማካሪ አቶ ሬድዋን ሁሴን አመልክተዋል።

አቶ ሬድዋን የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት መቀለ ደርሰው ከተመለሱ በሁዋላ በተከታታይ ባሰራጩት የቲውተር መልዕክታቸው እንዳሉት፣ የመከላከያ ሰራዊት ህገመንግስታዊ ሃላፊነቱን ለመተግበር መቀለ የሚዘልቀው በናይሮቢ በተደረገው ሁለተኛ ውይይት መሰረት ነው።

ከናይሮቢው ሁለተኛ ስምምነት አንድ ቀን ቀደም ብሎ የመንግስት ኮሙኒኬሽን መስሪያ ቤት ” የመቀለ ህዝብ ደህንነት ሊረጋገጥ ይገባል” ሲል በፓትሮል የተደገፈ ዘረፋ ህዝቡን ማማረሩን ጠቅሶ አስፈላጊ ያለውን እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል አስጠንቅቆ ነበር።

የመከላከያ ሰራዊት ባልገባባቸው ጥቂት አካባቢዎች መቀለን ጨምሮ የተደራጁ ሌቦች ህዝቡን እያወኩ በመሆኑ ጥሪ እየቀረበለት እንደሆነ ያመለከተው የመንግስት መግለጫ፣ “ስምምነቱ አደጋ ሊገጥመው ነው?” የሚል ስጋት አሳድሮ ነበር። ይሁን እንጂ መንግስት ይህን ባለ ሃያ አራት ሰዓት ባልሞላ ጊዜ በናይሮቢ ስምምነት መደረሱን ለማረጋገጥ መቻሉን፣ ይህንኑም አስቀድመን ጽፈን እንደነበር ይታወሳል።

ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴዋና ተግባርዋ እየተመለሰች ያለችው ትግራይ የተለያዩ አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ እየተሰራ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ መደበኛ በረራውን ነገ እንደሚጀምር እውን ሆኗል።

የኤሌክትሪክ ሃይል ሙሉ በሙሉ ከዋናው ሃይል ጋር ተገናኝቶ ያለቀ ሲሆን ስልክና ኢንተርኔትም ለማስጀመር የወደመውን ከአንድ ሺኅ ኪሎሜትር በላይ ርዝመት ያለው መስመር የመጠገኑ ስራ ከሰማኒያ በመቶ በላይ ተገባዷል።

የተጎዱ የማምረቻ ተቋማትና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችን ዳግም ለማስጀመር ጥናት የተጀመረ ሲሆን ይህንኑ ለማድረግ የበጀትና የሰው ሃይል ምደባ ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።

አቶ ጌታቸው የሰሙ ጅማሬ ማስረገጫ የማዕዘን ድንጋይ ያሉት የመንግስት ባለስልጣናት ጉብኝት ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ እንዲል መተማመንን ለማሳደግና ከቀደመው የ”ሴራ” ፖለቲካና ቂም በቀል አካሄድ ትምህርት የቀሰመ እንዲሆን በርካታ አስተያየት እየተሰጠ ነው።

See also  የምስራቅ አፍሪካ ወታደራዊ የመረጃ ተቋማት ሽብርተኝነትን በጋራ ለመከላከልና ለማጥፋት ተስማሙ

በተለይ በኢትዮጵያዊያን ዘንዳ እምነት ያጣው ትህነግ ከዚህ መሰሉ ሴራ የማምረትና የክፋት አካሄድ ራሱን በማቀብ፣ ያለ አንዳች መሰረታዊ አጀንዳና ምክንያት የትግራይን፣ የማራን፣ የአፋርን ህዝብ ለመከራ መዳረጉን አምኖ፣ ድፍን ኢትዮጵያን ማወኩንና ማሰቃየቱ ገምግሞ የጎዳውን የህብረተሰብ ክፍል ለመካስ መስራት እንደሚገባው፣ ዳግም ጦርነትን አማራጭ አድርጎ እንዳያስብ፣ ሌሎችም ቢሆኑ ትህነግን በሚከሱበት ጉዳይ ራሳቸውን ሳይከቱ የመቻቻልና የቀደመውን አብሮነት ከማስፈን አንጻር በሆደ ሰፊነት እንዲንቀሳቀሱ ምራቅ የዋጡ እየመከሩ ነው።

ዶክተር ደብረ ጽዮን እንዳሉት የትህነግ ታጣቂዎች ሲተቀሙበት የነበረ ከባድ መሳሪያና ወታደሮች ወደ አንድ አካባቢ የተሰበሰቡ ሲሆን መከላከያ እንደሚረከባቸው ይፋ ሆኗል። አቶ ሬድዋንም በተመሳሳይ ይህንኑ አረጋግጠዋል።

Leave a Reply