ብራዚላዊው የእግር ኳስ ንጉስ ፔሌ በካንሰር ህመም ምክንያት ሆስፒታል ገብቶ በህክምና ሲረዳ የቆየ ቢሆንም ማገገም ባለመቻሉ ከዚህ አለም በሞት መለየቱን ወኪሉ ጆ ፍራጋ እና ቤተሰቦቹ በዛሬው ዕለት አረጋግጠዋል።

ፔሌ ከህዳር ወር ጀምሮ የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽንን ጨምሮ በተለያዩ በሽታዎች በደረሰበት ተደራራቢ ህመም ሆስፒታል ገብቶ የህክምና ዕርዳታ በማግኘት ላይ ነበር።

የሶስት ጊዜ የአለም ዋንጫ ባለድል እና በትክክለኛ ስሙ ኤድሰን አራንቴስ ዶ ናሲሜንቶ በመባልም የሚታወቀው የ82 ዓመቱ የእግር ኳስ ንጉሱ ፔሌ ለሞት ከዳረገው የካንሰር ህመም በተጨማሪ በልብ እና በኩላሊት ህመምም ይሠቃይ እንደነበረ ከቤተሰቡ የተገኘ መረጃ ያመለክታል ሲል አልጀዚራ አስነብቧል።

ፔሌ እ.ኤ.አ. ሴፕቴምበር 2021 ከሆዱ ላይ የዕጢ እብጠት ተወግዶለት እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው ህዳር 29 በሳኦ ፓውሎ በሚገኘው አልበርት አንስታይን ሆስፒታል ገብቶ ህክምናውን ሲከታተል እንደነበርም ታውቋል።

በብዙዎች ዘንድ እጅግ ባለተሰጥኦ የእግር ኳስ ተጫዋች ሆኖ ይታይ የነበረው ፔሌ እንደ አውሮፓዊያኑ ዘመን አቆጣጠር በ1958፣ በ1962 እና በ1970 ዓ.ም ሃገሩ ብራዚልን የዓለም ዋንጫ ባለድል ማድረግ ችሏል። በተሰለፈባቸው 92 ጨዋታዎችም 77 ያህል ጎሎችን በማስቆጠርም በዘመኑ የትውልድ ሀገሩ ብራዚል ወደር ያልተገኘለት ግብ አስቆጣሪም ነው።

በ22ኛው የኳታር ዓለም ዋንጫ የአርጀንቲና የአለም ዋንጫ አሸናፊነትን ተከትሎ ፔሌ ቡድኑ ዋንጫውን ሲያነሳ የሚያሳይ ምስል በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ለጥፎ ነበር።

በወቅቱም በአርጄንቲናዊው የቡድኑ ካፒቴን ሊዮኔል ሜሲ፣ በፈረንሳይ እያደገ የመጣው ኮከብ ኪሊያን ምባፔ እና የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚዎች የነበሩት ሞሮኮዎች እጅግ እንዳስደነቁት ጠቅሶ ነበር።

ዛሬ የምንጊዜም የእግርኳሱ ንጉስ ፔሌ ትዝታዎቹን ትቶልን አሸልቧል።

via ; AMNW

ማራዶና ከሞተ በሁዋላ በግል ታሪኩ ህትመት ላይ ” በገነት ከማራዶና ጋር ኩስ እንጫወታለን” ማለቱን እያነሱ ሚዲያዎች እየዘገቡ ነው።

Leave a Reply