“የቅኝቶች ንግሥት”

ማሬን በመድረክ ላይ ስትዘፍን ያየኋት ዘጠነኛ ክፍል መማር የጀመርኩ ሰሞን ነው። ጊዜው  1988 ዓ.ም. ነው። ቦታው ደግሞ ደሴ፣ ሆጤ ትምህርት፣ አዳራሽ። በወቅቱ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይሁን ሬዲዮ ወይም በሁለቱም (?) እየተዘጋጀ ይተላለፍ የነበረ “ዝክረ ሰንበት” የሚባል  ዝግጅት (የጥያቄና መልስ ይመስለኛል)፣  እነ ደምሴ ዳምጤ ያሉበት፣ ቀረጻው የተካሔደው ውድድሩም ጭምር የተደረገው እኛ ትምህርት ነበር፤ሆጤ። በዝግጅቱ ሙዚቃዎቿን ካቀረቡት መካከል ትዝ የምትለኝ ማሪቱ ብቻ ናት፤ ካዘጋጆቹ ደግሞ ደምሴ ዳምጤ።

ከዚያች አጋጣሚ በኋላ በአካል መድረክ ላይ ስትዘፍን ታድሜ አላውቅም። ወይም ያገናኘን አጋጣሚ የለም። ይኹን እንጂ፣ ማሬን የቅርቤ ሰው ያህል አውቃታለሁ። ስለማውቃት ትናፍቀኛለች። በአጋጣሚም ይበሉት በሥራና በማኅበራዊ መሥተጋብ፤ የማሬ ጓደኞችና ወዳጆች፣ ለረጅም ዓመታት አብረዋት የሠሩ አርቲስቶች የእኔም ወዳጆችና ጓደኞች እንደቤተሰብም የሆን ጭምር አሉ። በተለያዩ አጋጣሚዎች ጨዋታ ሲነሳ ማሬም አብራ ትነሳለች። የጨዋታው አስኳል ትሆናለች። ለዚያውም በብዙ አጋጣሚ በተለያዩ ሰዎች ለብዙ ጊዜ።

ማሬ ጋር ያላቸውን ገጠመኝ፣የማሬን የዋህነትና የበዛ ሩህሩህነት፣ የማሬን ተጫዋችነት…..ወዘተ በተደጋጋሚ ስለሚነግሩኝ ማሬን በጣም አቅርበውልኛል። እናም በጣም የማውቃት ያህል ይሰማኛል።  ድጋሜ (በተደጋጋሚ) መድረክ ላይ ስትዘፍን መታደምን በመናፈቅ እንኳን ወደምትናፍቂያት አገርሽ በሰላም ገባሽ!

**
የክብር ዶ/ር ማሪቱ ለገሰን በተለይ ዛሬ ብዙዎች “የአምባሰሏ ንግሥት” ሲሏት አይቻለሁ። በሌላ ጊዜ ደግሞ ሌሎች ሰዎች “የባቲዋ ንግሥት” እያሉ ሲጠሯት መስማት የተለመደ ነው። አንዳንዴ የአምባሰሏ፣ አንዳንዴ የባቲዋ ንግሥት እየተባለች ትጠራለች።

ማሬ፣ እርግጥ ነው በአራቱም ቅኝቶች ትጫወታለች። በአራቱን ቅኝቶች በአንድ መድረክ ትጫወታለች። የትኛው ቅኝት የበለጠ ይቀናታል ወይም በጣም ትቀልጸዋለች የሚለውን መለየት እስከማይቻልበት ድረስ ኹሉም ለእሷ ገር ናቸው። ትችላቸዋለች። ትጠበብባቸዋለች። በአምባሰልም በባቲም በኹለቱም ”መንገሧ”  ለዚህ ይመስለኛል።ሰዎችም የአምባሰል ወይስ የባቲዋ ንግሥት የሚለውን መለየት የሚረሰቸው ለዚህ ይመስለኛል።

እኔ ግን እላለሁ እናም የሚመስለኝ፣ ማሬ የአምባሰልና የባቲ ቅኝቶች ብቻ ንግሥት ናት አልልም፤ አይመስለኝምም። ማሬ የአምባሰልና የባቲ ቅኝቶች ንግሥት እንደኾነቺው ኹሉ  ለ “አንቺ ሆዬ ለኔ (ሽሙንሙን)” እና “ትዝታ (ወሎ)” ቅኝቶችም እኩል ንግሥት ናት። ማሬ፣ በትዝታ (ወሎ) ቅኝትንም ብዙ ተጫውታለች። ብዙ ዘፈኖች አሏት። እንደሌሎቹ የነገሠቺባቸው። በ “አንቺ ሆዬ ለ’ኔ (ሽሙንሙን/ሸሞንሟናየዋ)”  ቅኝት’ማ  እኛም ሕጻን እያለን ሳይቀር አንቺ ሆዬ ለ’ኔን የምናውቀው በእሷ ዘፈን ይመስለኛል። በእሷ እየዘፈንን አድገናል፤ አንቺ ሆዬ ለ’ኔ ወይም ሽሙንሙን ቅኝቶች መሆን ወይም አለመሆናቸውን ሳናውቅ ጭምር የዘፈንናቸው ናቸው።

See also  የኳታር ዓለም ዋንጫ ያስተዋወቀው ጋኒም አል ሙፍታህ

“አንቺ ሆዬ ለ’ኔ የሚሏት ዘፈን፣
አምና ብር በላች ዘንድሮ ወይፈን፣
ደግሞ ለከርሞዋ ጥንድ በሬዋን።”

ወይም

“ሽሙንሙን ሽሙንሙን፣ ሽሙንሙን በልልኝ፣
የያዘኝ አባዜ፣ገለል እንዲልልኝ።”

እናም ባጭሩ ምን ለማለት ነው፤ ማሬ የአራቱም ቅኝቶች ንግሥት ናት። በብዙ ሥራዎቿና መድረኮች በአራቱንም ቅኝቶች በደንብ እና እኩል ሊባል በሚችል መልኩ ስትጫዎት የኖረች። አንዴ የባቲዋ ሌላ ጊዜ የአምባሰል እያልን ከምንጠራትም በአራቱም ቅኝኝቶች እኩል ነግሣባቸዋለችና “የቅኝቶች ንግሥት” ብትባልስ ባይ ነኝ? ምን ትላላችሁ?

እንኳን ሁሌም ወደምትናፍቂያት ወደ እናት አገርሽ በሰላም መጣሽ፣ የክብር ዶ/ር ማሪቱ ለገሰ፤

የቅኝቶችንግሥት! Wobishet mulat

Leave a Reply