• በሚዲያ እኩል ድምጽ የተነፈጉ የአካባቢው ተወላጆች ቅሬታቸውን ገለጹ፤ በዚህ ከቀጠለ የከፋው ይመጣል ይላሉ

አብዛኞች ከጎጃም እንደተነሱ የሚናገርላቸው የአማራ ታጣቂዎች ናቸው። ሌሎች ” ስማቸውን ፋኖ ያስባሉ የአማራ ልዩ ሃይል” ይሏቸዋል። ከጎጃም ከሚዋሰነውን ቀበሌ ጀምሮ ለነቀምት ጥቂት ሲቀር ድፍን ምስራቅ ወለጋን በቁጥጥራቸው ስር አውለውት ነበር። መከላከያ እነዚህን አካባቢዎች ነው እንዳጸዳቸው የተመለከተው። ነዋሪዎች “የአማራ ታጣቂዎች በነበሩበት ወቅት የፈጸሙት በደል በነጻና ገለልተኛ ሃይል ሊጣራ ይገባል” ሲሉ ይጠይቃሉ።

በጎጃም ከአማራ ክልል ከሚዋሰነው ጉተን ተነስተው ጊዳ፣ ኪረሙ፣ ኢባንቲ የመሳሰሉ ከተሞችን ሙሉ በሙሉ ይዘው ነበር። ከተሞቹንም ሲይዙ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያ ፈጽመዋል። ዝርፊያ አከናውነዋል። ኪረሙ ላይ የሸኔ ሃይል ገጥሟቸው በሁለቱም ላይ ጉዳት ደርሶ ሸኔ መጨረሻ ላይ ሲያፈፍግ ኪረሙን ሙሉ በሙሉ ሲቆጣጠሩ የፈጸሙትን ገለልተኛ አካላት እንዲያጣራ ለአብነት ቦታ ጠቅሰው ይጠይቃሉ።

ከሻምቡ አስራ ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምተገኘውን ሰቀላና በዛው አቅጣጫ ጀርጀጋ፣ ጃርቴ፣ አሞሩ የሚባሉትን አካባቢዎች መነሻቸውን ጎጃም ያደረጉ የአማራ ታጣቂዎች ሙሉ ሙሉ በወረራ ተቆጣጥረው ይዘው እንደነበር ያወሱ እንዳሉት የመከላከያ ሃይል አምስት ቀን አካባቢ በፈጀ ኦፕሬሽን አሁን ላይ አካባቢዎቹን ነጻ ማድረጉን አስታውቀዋል። ለምን አካባቢዎቹን መውረር እንዳስፈለገ እንደማይገባቸውም አስረድተዋል።

በወለጋ ቄለም በንጹሃን አማራ ነዋሪዎች ላይ ዘር ለይቶ የሚፈጸመውን ግድያ እንደሚያወግዙ፣ ፍጹም ትክክል እንዳልሆነ የሚናገሩት ንጽሃን ስም እየጠቀሱ ቤተሰቦቻቸው እንደተገደሉባቸው፣ ንብረታቸው እንደተጋዘና እንዲህ ያለው ወረራ ለወደፊት ይባስ እልህ ውስጥ የሚያጋባ እንደሆነ ገልጸዋል። “እኛም ተቆርቋሪ አለን። እኛ ላይ የደረሰው ለሌሎች እንደሚባለው ይፋ ቢሆን … ምን ሊከተል እንደሚችል አስቡት” ሲሉም ያስጠነቅቃሉ።

” ፋኖ” በሚል ስም ራሱን የሚጠራው ይህ አካል ኪረሙን ሲቆጣጠር የክልሉን ልዩ ሃይል መሳሪያ በማስፈታት ከፍተኛ ዝርፊያና የመብት ጥሰት እንደፈጸመባቸው ያመለከቱ፣ ክልላቸው እንዲያስታጥቃቸው፣ ራሳቸውን ለመከላከል እንዲያደራጃቸው ይህን ካላደረገ ይህን ማድረግ ለሚችሉ ሃላፊነቱን እንዲሰጥ እየጠየቁ ነው። ይሁን እንጂ አሁን ላይ መከላከያ ሰራዊት ገብቶ አካባቢውን ጸጥ እንዳደረገው፣ ሊያንገራገሩ በሞከሩ ላይ ክንዱን ማሳረፉንም አመልክተዋል።

በኦሮሚያ ክልል በብዛት አማራዎች ይኖሩባታል በምትባለው ሃሮ መከላከያ ኪረሙን ከተቆጣጠረ በሁዋላ በተደረገ አሰሳ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የአማራ ታጣቂዎች ተተኳሽ፣ የተዘረፈ ንብረትና ብር፣ እንዲሁም የመንግስት ንብረቶች ደብቀው እንደተገኘባቸው ነዋሪዎች ምስል አስደግፈው ለዝግጅት ክፍሉ ልከዋል። ዳግም ወደዛ ቤተክርስቲያን ለአምልኮ መሄድ እንደሚከብዳቸውም አመልክተዋል።

በሁለቱ ክልሎች መካከል ከፍተኛ መቃቃር እንደነበር ሲገለጽ ጉዳዩ ከአንድ ወገን ብቻ ይዘገብ ስለነበር ገለልተኛ ወገኖች እንዲስቱ መደረጉን ያመለከቱ የአካባቢ ነዋሪዎች፣ ከጎጃም የሚነሱና በክልሉ ወረራ የሚያደርጉትን አካላት ክልሉ “እጁ ካለበት እንዲሰበስብ፣ እጁ ከሌለበት ህግ እንዲያስከብርና ክልሉን አልፈው በመውጣት ዘረፋ የሚያካሂዱትን፣ ነብስ የሚያጠፉትን እንዲያስቆም” አሳስበዋል። በጎጃም በኩል የድንበር ጥያቄም ሆነ ክርከር እንደሌለ በማስታወስ ድርጊቱን በአብሮነት የሚያምኑ የአማራ ክልል ተወላጆችም ለወደፊት መዘዙ የከፋ መሆኑንን በማስላት እንዲያወግዙ ጠይቀዋል።

በኦሮሚያ ሸኔ በርካታ የአማራ ተወላጅ የሆኑ፣ ነገር ግን ለዓመታት በሰላም ሲኖሩ የነበሩ ላይ የፈጸመንና ወደፊትም ዕድሉን ካገኘ ሊፈጽም የሚችለውን ጥቃት በተመሳሳይ ማውገዝ ከሁሉም ኦሮሞ እንደሚጠበቅ ያስታወሱት እነዚሁ ወገኖች ” ድፍን ምስራቅ ወለጋን ለነቀምት 120 ኪሎ ሜትር አስኪቀር ወሮ መዝረፍና ንጽሃንን መግደል ሌሎች መፍትሄ አይመጣም፣ ከዚህ ዘራፊ ሃይል ጋር ያላችሁ ሃብታሞችም እጃችሁን ሰብስቡ” ብለዋል። በስምም ጠቅሰዋል።

መንግስት “የአማራና የኦሮሞ ሸኔ” ሲል በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አማካይነት ይፋ መናገሩ “አማራ ሸኔ አይደለም” በሚል ቁጣ ማሰማታቸውን እነዚህ ወገኖች ” ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው። ከጎጃም የሚነሳ ሽፍታ ራሱን ፋኖ እያለ ከሸኔ ያልተናነሰ ወንጀል እየፈጸመ ነመሆኑንን ክልሉም አይክደውም” ብለዋል። አይይዘውም እንዲህ ያለው አካሄድና ወረራ ትህነግንና አማራ ክልልን የት እንዳደረሰቸው ማስታወስ አግባብ እንደሆነ አመልክተዋል።

“የጊዳና ከረሙ ህዝብ እጅግ ሰላማዊና ሰው ወዳድ፣ በዘር የማያስብ እንደሆነ በአካባቢው የቅባት ዕህል ነግደው ለዛሬ የበቁት ባለሃብቱ በላይ ክንዴ ምስክር ናቸው” የሚሉ የአካባቢው ተወላጆች ” እሳቸውም ሆኑ ሌሎች ባለሃብቶች ከክላላቸው፣ በተለይም ከአካባቢያቸው የሚነሱ ታጣቂ ወራሪዎችን በማስታገስና በማውገዝ በኩል ሚና ይኑራችሁ” ሲሉ በደፈናው አስታውቀዋል።

መንግስት መከላከያን አሰልፎ ጥብቅ እርምጃ እየወሰደ እንደሆነ ተሰምቷል። የሁለቱም ክልል ነዋሪዎች በዚህ አግባብ ከስምምነት መድረሳቸው ይፋ ሆኗል። መከላከያ ሸኔን እያሳደደ በምዕራብ የሱዳን ድንበር የመጨረሻ ከተማ የሆነችውን ቤጊን ይዟል። ከዛም አልፎ ከሃይለስላሴ ዘመን ጀምሮ የኦነግ ነጻ ይዞታ የሆነውን አንፌሎ የሚባለውን ሳራማ አካባቢ እየተቆጣጠረ መሆኑ ተሰምቷል። ስፍራው ለሱዳን 60 ኪ.ሜትር ርቀት ያለው ሲሆን፣ ሱዳን ድንበሯን እንደማትፈቅድ ገልጻ በቅርቡ በፈረመችው መሰረት በቀጣይ የሸኔ ዕጣ ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ መገመት የማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል።

የደርግ መንግስትን ለመገልበጥ ተሞክሮ በከሸፈውና ምርጥ የሚባሉት የኢትዮጵያ ጀነራሎች ባለቁበት እንዲከሽፍ ተደርጎ በተቀነባበረው መፈንቅለ መንግስት እጃቸው አለበት በሚል የሚከሰሱት ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ፣ ከኢሳቱ ሲሳይ አጌና ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ መፈንቅለ መንግስት ሲታሰብና ሱዳን ድረስ በመሄድ ግንኙነት ያደርጉ እንደነበርና እውቂያው እንዳላቸው አምነው መናገራቸው ይታወሳል። እኚሁ ሰው “የጎጃም ድንበር ወለጋን አልፎ ነው” በማለት መናገራቸው አይዘነጋም። የዛ ስሌት ይሁን የሌላ ድፍን በሚባል ደረጃ ከጎጃም የተነሳ አማራ ታጣቂ ሃይል ወሮ ይዞ መቆየቱ በየትኛውም አግባብ ተቀባይነት እንደሌለው፣ ለየትናውም ዓይነት ጥፋት ማካካሽ ተደርጎ ሊወሰድ እንደማይችል፣ ይህ ከቀጠለ በኦሮሚያ በኩል በይፋ አቋም እንደሚያዝበት ቁርጥ ውሳኔ ከተያዘ በሁዋላ ነው ሁለቱ ክልሎች በአመራር ደረጃ ግልጽ ያላደረጉትን ስምምነት ያደረጉት።

ይህንኑ ተከትሎ ጉተን ላይ መከላከያ ላይ ተኩስ ከፍተው መጠነኛ ጉዳት ያደረሱት ሳይቀሩ እርምጃ እየተወሰደ የማጽዳት ስራው ወደ መጠናቀቁ መድረሱን፣ ይሁን እንጂ ይኸው ዘራፊ ሃይል እያደፈጠ ጥቃት ለማድረግ እንደሚሞክር ለማወቅ ተችሏል።

ሰሞኑንን የመንግስት መግፈናኛዎች እንዳሉት የብልጽግና ኦሮሞና አማራ ባለስልጣኖች በዝግ መክረው ልዩነታቸውን ማስተካከላቸውን መግለጻቸው አይዘነጋም። ይህን የሰሙ እንዳሉት በሁለቱ የአንድ ድርጅት አካላት ውስጥ በየጊዜ የሚፈጠረው አለመግባባት ለሌሎች አሰልቺ ስለሆነ የኦሮሚያ ብልጽግና ከቀሪዎቹ ጋር ሆኖ አማራ ብልጽግናን ሊያገል የሚችልበት አግባብ ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት ያላቸው አሉ። እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት ጎንደር፣ ወሎ፣ ሸዋ በዚህ የዝርፊያ ጉዳይ ውስጥና ወረራ ውስጥ የሚሳተፉ አለመሆናቸውና ዘራፊዎችና ወራሪዎቹ ከጎጃም የሚነሱ፣ በዛው የሚደራጁ፣ እዛው ድጋፍ የሚደርገላቸው መሆናቸው ሊሎች ጉዳዩ ከማይመለከታቸው አካላት ጋር በደቦ ልዩነት ውስጥ መግባቱ አስፈላጊ እንዳልሆነ መከራከሪያ የሚያቀርቡ እንዳሉም ተጠቁሟል።

ጎጃም ውስጥ እንደ ዘመነ ካሴ በይፋ ብር እየተሰበሰበላቸው ኢመደበኛ ሃይል ሲያሰለጥኑንና ሲያስመርቁ እንደነበር የሚታወስ ነው። ክልሉ የህግ ማስከበርና ህገወጥ ኢመደበኛ አካሄዶችን ለመቆጣጠር ሲነሳ በከፍተኛ ደረጃ የሚዲያ ዘመቻ ተከፍቶበት እንደነበር ይታወሳል። ይህ ዘመን ካሴ ይመራዋል የሚባለው ኢመደበኛ ሃይል፣ በጦርነቱ ወቅት ወሎ ሄዶ ዘርፎ መመለሱን የወሎ ፋኖ ዋና ተጠሪዎች ማናገራቸው አይዘነጋም።

በጎጃም ውስን አካባቢ ያሉና “በትህነግ ስር አሃብት የሰበሰቡ ናቸው” የሚባሉ ላይ የፌደራል መንግስት ጥብቅ ምረመራና መጀመሩን ገልጸን መዘገባችን ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “የአማራና የኦሮሞ ሸኔ ” ሲሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በግብር ተመሳሳይ ወንጀለኞች መሆናቸውን ሲያስታውቁ፣ ከነዚህ ጀርባ የሆኑ ራሳቸውን እንዲመለከቱ ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው።

የአምራ ክልል ትክክለኛ ፋኖዎች ጥቃትን የማይወዱ፣ በዝርፊያ የማይታሙ፣ ሚዲያ የሚባል ነገር የማይወዱ፣ አገራቸውን የሚያከብሩና ከምንም በላይ የዓላማ ጽናታቸውና ስርዓታቸው ጥብቅ የሆነ፣ አገር በተወረረች ጊዜ ዋጋ የከፈሉ ናቸው። “በፋኖ ስም የሚነግዱ የመሸታ ቤት ዱርዬዎችን እውቅና አንሰጥም” ሲሉ ድርጊቱ ያናደዳቸው መናገራቸው ይታወሳል።

Leave a Reply