ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው….!!!

ኢትዮጵያ በውስጥ ባንዳና በውጭ ባዳ የተከፈተባትን የተቀናጀ ሁለንተናዊ ጦርነት በድል አድራጊነት አልፋ ለዛሬ ትበቃ ዘንድ ከትግራይ ክልል የተገኙ ትግረኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያዊያንም ጭምር አኩሪ ተጋድሎ አድርገዋል።
በኢትዮጵያ ፍርስራሽ የምትገነባ ትግራይ እንድትኖር አንተባበርም ያሉ በእብሪት ለተወጠረው ሕወሓት አላስፈላጊ መስዋዕትነት የሚከፍል የትግራይ ወጣት መኖር የለበትም ብለው ለትግራይ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የታገሉ ከትግራይ ክልል የተገኙ የሕወሓት ተቃዋሚ ትግረኛ ተናጋሪዎችን በጦርነቱ ወቅት ማየት ችለናል።
እነዚህ ከትግራይ ክልል የተገኙ ትግረኛ ተናጋሪዎች የኢትዮጵያ የሕልውና ምሽግ በሆነው የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከመፈፀሙ በፊትና ጥቃቱን ተከትሎ ለ2 ዓመት ያህል በቆዬው ጦርነት በሕወሓት ሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳ በአለማቀፍ ማህበረሰብ በታገዘው የተቀናጀ የጀኖሳይድ የፕሮፖጋንዳ የጩኸት ዘመቻ እንኳን፣ ባለመረበሽ ለስሜታዊነት ቦታ ባለመስጠት በነገሮች ተገፍተው ወደብሔር ከረጢታቸው ሳይገቡ ስለኢትዮጵያ ሲሉ ከቃላት ባለፈ በገንዘባቸው በሞራል በእውቀታቸው በሚዲያ እና በተሰጣቸው የሕዝብና የመንግስት ኋላፊነትን በታማኝነትና በቁርጠኝነት በፅናት እስከመጨረሻው ቆመው ለኢትዮጵያ ታግለዋል። ኢትዮጵያ ሰው በፈለገችበት ወቅት ሰው ሆነው ተገኝተው በአርአያነት የሚጠቀስ አኩሪ ተጋድሎ ደማቅ ታሪክ ሰርተዋል።

ከእነዚህ በመንግስት መዋቅርና በብልፅግና ውስጥ በሕዝብና በመንግሥት የተሰጣቸውን ኋላፊነት በታማኝነትና በቁርጠኝነት ከፊት ተሰልፈው ኢትዮጵያን ለማሻገር እስከመጨረሻው በፅናት ቆመው ከታገሉት ከትግራይ ክልል ከተገኙት ትግረኛ ተናጋሪ ሐገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን መካከል የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም በላይ ቀዳሚውና ጎልተው የሚጠቀሱ ናቸው።

እንደ ዶ/ር አብርሃም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ምክትል ሹም የሆኑት አቶ ታዜር ከትግራይ ክልል ከተገኙ የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጆች መካከል ሳይጠቀሱ የሚታለፉ አይደሉም።

የጥርጣሬ መንፈስ በሰፈነበት የራስ ጥላ በሚሸሽበት በዛ የጨለማ ወቅት፥በተለይም ከአማራና ከኦሮሚያ ክልል በብልፅግና እና በመንግስት መዋቅር ውስጥ በኋላፊነት የተቀመጡ አንዳንድ አመራሮች በኢትዮጵያ ማሸነፍ በተጠረጠሩበት፣ በወያኔ አዲስ አበባ መግባት በአገር መፍረስ በአብይ ሐገር ጥሎ መሰደድ እርግጠኛ ሆነው ከሐገር ለመውጣት ሻንጣ ስለመሸከፍ በሚያስቡበት፤ ከሐገር ሳንወጣ ወያኔ አዲስ አበባ ከገባ በሚል የሚጠበቅባቸውን ከመስራት ይልቅ በሌሊት ወፍነት መንቀሳቀስን በመረጡበት፥ ወደሚዲያ በመውጣት ሕዝቡን ሞቢላይዝ እንዲያደርጉ የወያኔን ሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳ እንዲመክቱ ለኢትዮጵያ ድምፃቸውን ያሰሙ ዘንድ ተጠይቀው ስልካቸውን እያጠፉ በሚጠፉበትና በሚሸሸጉበት፥ ሕዝብና መንግስት በሰጣቸው ኋላፊነት የሚጠበቅባቸውን ከማድረግ ይልቅ በኋላፊነታቸው የሚያገኙትን መረጃ ለጠላት አሳልፈው በሚሰጡበት፣ የኢትዮጵያን ጦር በስነ ልቦና ለማዳከምና ለመበታተን ስለጦርነቱ የተዛባ የተሳሳተ መረጃ በሚለቁበት፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በአማራ ክልል ኢ መደበኛ ሃይል በማደራጀትና ከተደራጀ ጋር በመሰለፍ ከወያኔ ጋር ለመደራደር ቁጥር ሁለት ኢህአዴግን ለመፍጠር እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ወቅት ከትግራይ ክልል የተገኙት እነ ዶ/ር አብርሃም ግን በሁኔታው ተከፍተው ወደብሔር ከረጢት ለመግባት ሳይሞክሩ ከኢትዮጵያ ይልቅ በብሔራችን ለመሸሸግ ሕወሓትንም አናስቀድምም ብለው የኢትዮጵያን ሕልውና ለማስቀጠል ሉዓላዊነቷንና የግዛት አንድነቷን ለማስከበር እስከመጨረሻው በልበ ሙሉነት በታማኝነትና በቁርጠኝነት ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም በባንዳ የማይደበዝዝ በወርቅ ቀለም የሚፃፍ አኩሪ ተጋድሎና ታሪክ በመስራት ኢትዮጵያ ትሻገር ዘንድ ታሪካዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል ብዬ አምናለሁ።

See also  "በተካድኩ" ስሜት መከላከያ አማራ ክልልን ለቆ ሊወጣ ነው?

እነ ዶ/ር አብርሃም ኢትዮጵያን ሲመርጡ እኛ እያለን ኢትዮጵያ በባንዳና በባዳ የተቀናጀ ዘመቻ አትፈርስም ሲሉ በባንዳዎች በኩል ፈተናዎች እንደግለሰብ አልገጠማቸውም በባንዳዎች እንደባንዳ አልተቆጠሩም ማለት አይደለም። እንደባንዳ ተቆጥረው ብዙ ብዙ ዘመቻዎች ተከፍቶባቸዋል። በአያሌው ተፈትነዋል። ነገር ግን የገጠማቸውን ፈተና በፅናት ድል አድርገው ተሻግረዋል። ባንዳዎችን አሸንፈው ከኢትዮጵያ ጋር የከፍታ ጉዞ ጀምረዋል። ኢትዮጵያን መምረጥና ለኢትዮጵያ መቆምን እንደባንዳ እንዲቆጠር የሰሩ አሁንም የሚሰሩት ባንዳዎችና የባንዳ ባንዳዎችም ጦርነቱን በተመለከተ በተያዘ አቋምና ትግል ወደታሪክ የሚዛን ፍርድ ሳናሻግረው እነ ዶ/ር አብርሃም ቀድመው ወደመረጡትና ወደቆሙበት መስመር ወደኢትዮጵያ ይጠጉ ዘንድ በመጨረሻ ተሸንፈው እጅ ሰጥተዋል። የባንዳ መስመር ወዳሉት መስመር መግባት ጀምረዋል።

ስህተትን ማመንና ለማረም መሞከር አቅምንም አውቆ በልክ ለመኖር የእብሪትን መጨረሻ በመመርመር ወደትክክለኛው አብሮ ወደሚያኗኑረው መስመር በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ስር ለመመለስ ከልብ በመፀፀት የተጀመረውን የሕወሓት አንዳንድ አመራሮች አሁናዊ ሁኔታ በራሱ የሚያስደንቀው እንጅ የሚያስወቅሰው አይደለም። ነገር ግን ስለነበረው ጦርነት ሁኔታ የባንዳነትና የአርበኝነት የሕወሓት ትርጉም ግን ቦታ ሊሰጠው የሚችል አይደለም። የተሳሳተ ወይም የተገለበጠ የተዛነፈ ትርክት ሊስተካከል ግድ ይለዋል።

የነገ ጠንካራ አብሮነታችንን የምንገምደውና የምናዋህደው ኢትዮጵያዊነትንም በማይናወጥ በፅኑ አለት ላይ ልንገነባ የምንችለው አርበኛውን እንደባንዳ ባንዳውን እንደአርበኛ እንዲቆጠር በሚያደርጉ የተዛነፉ ወይም የተሳሳቱ ትርክቶች ሳይስተካከሉ ወይም እንዲፈጠሩ ለሰላም ሲባል በሚል ዕድል በመፍጠር ተባባሪ ወይም ባላዬና ባልሰማ ለማለፍ በመሞከር ሊሆን አይገባውም። ጦርነቱ ኦዲት ሳይደረግ ለሰላም ሲባል በሚል አመለካከት ብቻ የተፈጠሩና እየተፈጠሩ ያሉ የተሳሳቱ ወይም የተዛነፉ ትርክቶችን በማለባበስ ወይም ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ እንዲታሰብ በማስመሰል ለማለፍ የሚደረገው ሙከራ መዘዙ አደገኛ መሆኑ አያጠያይቅም። ከምንም በላይ ጦርነቱን ኦዲት ማድረግ የሚያስፈልገው ግለሰቦችን ለማጥቃት ወይም ለመኮነን ሳይሆን አገር የሚቆምበትን የትርክት ምሰሶን መርጦ ለመትከል ስለሚያስችል ነው።

በወያኔ እብሪት የተጀመረው ጦርነት በትግራይ ሕዝብም ኦዲት ሊደረግ ይገባዋል። ወያኔ እንደ ድርጅት የትግራይ ሕዝብ እንደሕዝብ በየትኛውም መመዘኛ በጦርነቱ ያገኘው አንዳች ጥቅምና ትርፍ አለ ብዬ አላስብም። ከጦርነቱ በፊት የነበረው የወያኔ ቁመና የትግራይ ክልል ሁኔታና ከጦርነቱ በኋላ ያለው ፈፅሞ የሚገናኝ ነገር አይደለም። እብሪት በወለደው ጦርነት የተነሳ የትግራይ ወጣት እንደቅጠል ረገፈ፣ ከፍተኛ ንብረት ወደመ የትግራይ ሕዝብ በጦርነቱ ስነልቦናው እንዲጎዳ በሌሎች ኢትዮጵያዊያንም ዘንድ በጥርጣሬ እንዲታይ ሆነ እንጅ ያስገኘለት ጥቅም ስለመኖሩ የሚታየኝ ነገር የለም። ስለሆነም የትግራይ ሕዝብ ዳግሞ ለመሰል ሁኔታ እንዳይዳረግ በወያኔ እብሪት በተካሄደው ጦርነት ወያኔ እንደድርጅት የትግራይ ሕዝብም እንደሕዝብ ከዚህ ጦርነት ምን አተረፍን ወያኔ ወደጦርነት ባይገባ ኖሮ የሚቀርበት ምን ነበር? ብሎ ቆሞ መጠየቅ የሚቻል ከሆነ የትግራይ ሕዝብ ከገጠመው ሁኔታ በተሎ የመውጣት ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ጋር ያለው የወንድማማችነት ስሜትን እንደነበረው ሳይሆን ከዛም ያለፈ በቀላሉ መፍጠር ያስችለዋል። ዳግም በትግራይ ክልል ለሐዘን ወይም ለመከራ የሚተኮስ የጦርነት ድምፅ ሳይሆን ለደስታ የሚተኮሱ ርችቶችን

See also  እየተገኘ ያለውን ወታደራዊ ድል በፖለቲካዊ ስራ ማፅናት ያስፈልጋል!

ወደሚሰማበት ሁኔታ መቀየር ይቻላል። በኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ የተሰጠውንና የተፈጠረውን ዕድል በአግባቡ በጥንቃቄ መጠቀምም ያስፈልጋል።

በእብሪት እንደተፈጠረው የጦርነት ሁኔታ በጦርነቱ እንደታየው ስሜት በጦርነቱ እንደተመዘገበው አንፀባራቂ ወታደራዊ ድል አይደለም የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ለትግራይ ሕዝብም ሆነ ለሕወሓት አሁን ላይ እያሳየ የሚገኘው የወንድማማችነት ስሜት። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በድል አድራጊነት ወደመቀሌ ተጠግቶ መቀሌንም ለመያዝ የሚያስችል ዕቅድ አጠናቆ ሳለ የሰላም ድርድር በሚል ከፍፁም አሸናፊነት በመነጬ በይቅርታ መንፈስ ለወያኔ መሪዎችና ለተቀሩት አብረዋቸው ለመቆም ለሚሞክሩት ታጣቂዎቻቸው የወንድ በር የተሰጠው ቁጥሩ የማይናቅ የትግራይ ሕዝብ በተሳሳተ ፕሮፖጋንዳ የወያኔ መሪዎችን ከሚመለከትበት ሁኔታ ለነገ አብሮነትና ወንድማማችነት፣ለሁሉም በሁሉም የምትገነባውን ኢትዮጵያን ከመገንባት አንፃር እነሱን ደምስሶ መቀሌን ከመቆጣጠር ይሻላል በሚል እንደሆነ ይታመናል። ይህን ወርቃማ ዕድል በአግባቡ መጠቀም አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ።

በመጨረሻም ስለኢትዮጵያ ለኢትዮጵያ ታምነው ለአመኑበት ጉዳይ የሚከፈለውን ሁሉ ዋጋ ለመክፈል ከፊት ለተሰለፉ ኢትዮጵያን ባንዳም ሆነ ባዳ በጦርነት ሊያፈርሳት እንደማይችል በተግባር ላስመሰከሩ ለእነ ዶ/ር አብርሃምና ለመሰል ከትግራይ ክልል ለተገኙ ትግረኛ ተናጋሪዎች ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል። ይድረሳቸው።

ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መከበር ሲሉ የሚጠበቅባቸውን መስዋዕትነት ለከፈሉ በተለይም ለጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊታችን መልካም የገና በዓል እንዲሆንላችሁ ከልብ እመኛለሁ!

ፎቶው
ለዘመናት አገሩን የበይ ተመልካች አድርጎ በነበረው በኪነጥበብ ባለሙያዎች ሲወደስና ሲወቀስ በኖረው ነገር ግን በእኛ ትውልድ ታሪኩን በቀየረው የኋይል ማመንጫ ብቻ ሳይሆን የፅናት፣ የነፃነት፣ የአንድነታችን ማስተሳሰሪያ ዓርማችን የመደማመጥና የመተባበር ማሳያ ምልክታችን በሆነው በታላቁ የሕዳሴ ግድባችን ጉብኝት ላይ የተወሰደ ነው!

ሰላም ለኢትዮጵያችን!!

በቶማስ ጃጃው ቴሌግራም የተወሰደ

Leave a Reply