የተፈራው የጦርነቱ ጣጣ ” ተጋሩዎች ዊልቸር ይዛቹህ ኑ”

የተፈራው የጦርነቱ ዜናዎች ብቅ ብቅ እያሉ ነው። ሆድ አስፍቶ፣ ጥርስን ነክሶ ሃቁን መቀበልም ግድ ነው። እውነትን የሚናፍቁና ለወደፊት ትውልድ የሚቀኑ በታሪክነት እስኪሰድሩት ድረስ እየተሸራረፉ የሚወጡትን መረጃዎች መስማትና ማየት ግድ ይሆናል። እየሆነም ያለው ይኸው ነው።

በአገራችን ወዳጆቹ እንዳሉት “የትህነግን ቆሞ ቀርና ካርቶን ራስነት” ድግስ አድርገው የጦርነቱን ዘግናኝ ውጤት በሰበርና በልዩ ዜና እንዲሆም በጥንቅቄ መልዕክት፣ “ዛሬ ምን አለ” እንዲሁም የትህነግ ውዳሴ አውራጅ ሚዲያዎች ከነጮቹ መርዛማ አጀንዳ ጋር አዋህደው በማጫጫስ እንደ ጠንቋይ ሃድራው የሞቀላቸው ኪሳቸውን ከሰው ነበስ አስበልጠው እንዴት አየሩን ያጥኑት እንደነበር መቼውንም የሚዛነጋ አይሆንም። ለአገርና ለህዝብ ከበሬታ ያላቸውን ሳያካትት ማለት ነው።

ጦርነትን ለትርፍ ሲገለገሉበት የነበሩ ቢያንስ ዛሬም አልተማሩም። ለመስማት በሚዘገንን ቁጥር የሰው ህይወት መጥፋቱን ከዛም ከዚህም እየተሰማ ባለበት በዚህ ወቅትም ጦርነትን ይጠምቃሉ። ልጆቻቸውን በሙቅ ዕቅፋቸው ይዘው፣ ደሃን እያስጨረሱ ኪሳቸውን ይሳበጡ “ጠገብን፣፤ በቃን” ለማለት ባይደፍሩም “ይብቃችሁ፤ እኛ በቃን” የሚሉ ወገኖችንም በሚፈለገው ደረጃ ማግኘት አልተቻለ።

” በዩቲዩብ ማታ ማታ ስለፈልፍ ልጆቼ ተሳቀቁብኝ። እየደነገጡ ተቸገርኩኝ። በዚህ ከቀጠልኩ ልጆቼ ችግር ይገጥማቸዋል። ቤት መከራየት አለብኝ” በማለት ዲሲ ምድር ቤት ጊዚያዊ የዕልቂት መጠንሰሻ ስቱዲዮ የተከራየ እናውቃአለን። ይህ ሰው በካድሬነት፣ በተቃዋሚነት፣ አስከሬን መስሎ ፎቶ በማሰራጨት በልመና ወዘተ. የተካነ የቀበሮ ባህታዊ ነው። “በሬ ካኮላሸው” እንዲሉ ዛሬም ይህ ሁሉ ደርሶ ማታታ ማታ ያለማቋረጥ ” የፍየል ወጠጤ” እያለ እልቂት ይጎስማል። ኤባክህን ይብቃህ” የሚል ቤተሰብ፣ ሚስትና ወዳጅ አጥቶ በንጽሃን ደም ቀደም ሲል በካድሬነት፣ አሁን ደግሞ በአንቂነት ስም ለጋ ወጣቶችን ለመማገድ ብሄር ይቆጥራል።

“ምን ፈልገህና በየትኛው ብቃትህ አገር ለመምራት እንደምትቋምጥ የተረዳህ ሰው አይደለህምና አቁም። ልክህንና ድርሳንህን እወቅ፣ መቆሚያህንና መቋሚያህን ለይ።” የሚሉ ባለመብዛታቸው ወይም “አዋቂ ቸልተኞች” በመብዛታቸው ቀጥሎበታል። እንደሱ ካድሬ የነበረው ፍጹም ብርሃኔ ለትግራይ ህጻናት ክራንች ዊልቼር ሲማጸን፣ ይህ ድንዙዝ አሁን የግደል ተጋደል አታሞ እየመታ ነው። “ከፍጹም ጥሪ ተማር” የሚሉ ሊበዙ ይገባል።

“በለው፣ ስበረው፣ ጀግና፣ ጥይት የማይነካህ …እያሉ ምክንያቱና ውጤቱ በውል በማይታወቅ ጉዳይ ወጣቱን ሲማግዱ የነበሩ ምን ይሉ ይሆን?” በሚል ከሰላም አማራጭ ስምምነቱ በሁዋላ በርካቶች የካድሬን ባህሪ ባለመረዳት በጉጉት ይጠብቁ ነበር። አንድ የማህበራዊ ሚዲያ አስተያየት ሰጪ ” አትጓጉ፤ ተቃቅፈው ሌላ ትርክት ያሰማሉ። ካድሬ ጸጸት ብሎ ነገር አያውቅም” ሲሉ በድፍረት ጽፈዋል።

ካድሬ ካድሬ ነው። እንደ ጌታቸውና ደብረጽዮን ያሉ ካድሬዎች ይሉኝታ የላቸውም። እዚህም ሰፈር ቢሆን በቀድሞው ጥብቆ ብልጽግና እያሉ የሚጫወቱ ውርጃዎች አሉ።አሜሪካ ቁጭ ብለው የሚሰብኩትን የሚተነትኑት ትናንት የትህነግ ባሪያ የነበሩ ካድሬዎች ተመሳሳይ ናቸው። ትንናንት ሲሉት የነበረው በፊልም ማስረጃ ፊታቸው እየታየ አያፍሩም። አይደነግጡም። መጽሃፉ እንደሚለው ደርቀዋል። የሰውነት ማእዛቸውና መለኪያቸው ተኗል።

See also  የአለማችን ግዙፉ የሩሲያ ኒዩክለር ተሸካሚ ሚሳኤል ምን ተአምር የማሳየት አቅም ያለው ይመስላችኋል ?

ትናንት ከትህነግ በላይ ትህነግ ሆነው ህዝብ ላይ ሲተፉ የነበሩ ዛሬ ተቃዋሚ መስለው ጦርነትን በየገጹ ይሰብካሉ። ከምናየው ይልቅ እነሱን እንድናምን የሰዎች ደረጃ መዳቢ ሲሆኑ አይጨንቃቸውም። ስሙን ሊጠሩት እንኳን የማይገባቸውን ሰው አጨቅይተው እነሱን የተሻለ አድርገው ሲያሳዩ አይቀፋቸውም። በደም በተጨማለቀ ማንነታቸው በቅርብ ለምኪያውቃቸው ህብረትሰብ እንደሚያወሩ እንኳን ለመረዳት በማይችሉበት ደረጃ ልቡናቸው ተዘግቷል። እኒህ ድፍኖች አንዱ ሲበላሽባቸው ሌላ እየፈበረኩ ሊያጋድሉ እንደ ጅብ ለሊት ለሊት ሳያሰልሱ ይጮሃሉ። ጉንፋን፣ ኮሮና፣ ተላላፊ በሽታ አይዛቸውም። “ቀለብ ሰፋሪ ደንቆሮ” ስለኮለኮሉ ኑሮን ለማሸነፍ ከቤት ሰማይወጡ ወደፊት በግፍ ብዛት ከሚሰብራቸው ደም ብዛትና ስኳር ውጭ አንዳች የማይነካቸው ቅምጦች ናቸው። ታዲያ ከሁሉም በላይ እነዚህን እየሰማ የሚነጉደውና መሃረቡን የሚፈታው ደነቋቁርቶች ያስገርማሉ ቢባል፣ የደንቃሉ ተብሎ ቢከተብ ምን ሃሰት አለው?

ትናንት ልጆቹ በአደባባይ ግምባራቸው እየተለየ በአልሞ ተኳሽ እንዲፈርስ ተደርጎ ሲጨፍጨፉ ፣ አንተ አስከሬን ታቅፈህ፣ እናት እጎዳና ላይ የተዘረረውን የልጇአስከሬን ላይ ተኝታ ስታነባ፣ ህዝብ “ጨረሱን ” እያለ እንባ ሲራጭ ” ሌቦች ናቸው” በማለት ደረቱን ገልብጦ በልጆቻችን አስከሬን የፖለቲካ ታማኝነቱን ለማረጋገጥ ሲተፋ ለነበረ ካድሬ ማታ ማታ ግብር ማስገባት እጅግ አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን ወራዳነትም አይደለም? ከዛም በላይ በግፍ በተደፉት ልጆቻን ደም ላይ የመደነስና የመማማል ያህል አይሆንም?

በ1997 ድምጻቸውን የተሰረቁ “ለምን” በማለታቸው በመለስ ዜናዊ ትዕዛዝ በቀይ መለዮ ለባሾች የተፈጸመ የዘመናችን የአንድ አስርት አመት ታሪክ እንዴትና ስለምን ይረሳል? ሰፈሩ በቆመበት ልጅ ግንባሩን ተመቶ ወደቀ። እናት እንደ ንስር አሞራ ተወርውራ የልጆችን አስከሬን ስታገላብጥ፣ በነጠላዋ ደሙን ለታቆም ስትወራጭ እሷንም ደገሟት። እናትና ልጅ በአጋዚ በደቂቃዎች ልዩነት በጥይት ተደፉ። ይህ የሆነው የዛሬ መቶ ዓመት አይደለም። ሆስፒታሎች የደም ጎርፍ ሆኑ። ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች ኮሪደሮቻቸው የዋይታ ሰፈር ሆኑ። የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ ራስደስታና ሚኒሊክን የማየት ዕድል አግኝቷል።

ዛሬ ማታ ማታ ሳያሰልስ 360 እያለ መርዝ የሚረጨው ትንሹ በረከት ኤርሚያስ ለገሰ፣ እነዚህን በግፍ የተደፉ ዜጎች ነበር ” ሌቦች፣ ባንክ ሲዘርፉ …” ብሎ ደማቸው ላይ የሌብነት ማህተብ ሲያትም የነበረው። ይህ በንጹሃን ደም ላይ ሲሳለቅና ሲተፋ የነበረ ሰው እንዴትና በምን መስፈርት፣ በየትኛው የሞራል ልዕልና ዛሬ ኢትዮጵያዊ መስሎ ሊያተራምሰን ይደፍራል? አንዱ ካድሬ ህሊና ቢስ፣ የደረቅ ነብስ ያለው፣ ሞራል የሚባል ያልፈጠረበት፣ ልቡናው የተዘጋና ሃፍረትና መሳቀቅ የሚባል ነገር የማያውቅ፣ ዝም ብሎ …. አይነት ፍጡር ስለሆነ ሲሆን፣ ሌላው ምክንያት ሰሚው ዝም ብሎ የሚፈስ ቀትረ ቀላል፣ ዝም ብሎ መሃረቡን የሚፈታ መደዴ፣ ዝም ብሎ የሚሞላ በርሜል በመሆኑ ነዎኦ ሰሚ ስል ሰምቶ የሚከተለው ለማለት ነው።

ሌልውም አዲስ አበባ ወጣቶችን ሲመለምል የነበረ ካድሬ አይኑን በበረኪና አጥቦ ሲያጭበረብርህ መረዳት የማትችሉትስ “ምንድን ሆናችሁ ነው? ለመሆኑ እንዲህ አይነቶቹ እናንተ ምንድ ናችሁ? ምን እንዲሆን ነው የምትፈልጉትና ኪሳችሁን የምታራግፉት? ስለምን ነው የትናቱን የማታስቡት?” ከጦርነቱ በሁዋላ የሚሰሙትን ዘግናኝና ልብ ሰባሪ ዜናዎች ስትሰሙ እጃችሁ እንዳለበት አስቡ። ነገሩ ትግራይ ላይ ብቻ አያበቃም። አያያዙና ፍላጎቱ ሌላ ነው። ይህን ሁሉ በችርቻሮና በደርዘን ስፖንሰር የምታደርጉ፣ ሚድያ ከፍታችሁ ኢትዮጵያ ላይ መርዝ የምታስረጩ …. ዋ !! የዛኔ

የጦርነት አታሞ ሲመቱ የነበሩ፣ ጦርነቱን እንደ አክሽን ፊልም ሲተርኩና ነዳጅ ሲጨምሩ የነበሩ፣ ይህንን ሁሉ ሲያደርጉ ኪሳቸውን እያሳበጡ የነበሩ፣ በፍጹም እብደት ሲከንፉ የነበሩ፣ እብደታቸውን ዕውን ለማድረግ የጥላቻና የማጋደያ መርዝ ሲረጩና ሲያከፋፍሉ የነበሩ፣ በየቀኑ፣ በየሰዓቱ እብሪት ሲረጩና በደመነፍስ በተከታዮቻቸው አበባ ሲረጭላቸው የነበሩ፣ አዲስ አበባ ለመግባት መንገድ ሲያማርጡ የነበሩ፣ በምንም ምክንያት እርቅ የሚባል ነገር ሊኖር እንደማይችል ታብየው ሲያናፉ የነበሩ… አለቆች፣ ጀሌዎች፣ አድማቂዎች፣ ተቀጣሪና ተላላኪዎች፣ ተከፋዮችና አጎብዳጆች… ሁሉም ከዚህም ከዚያም ውጤቱን በድሃ እልቂት ደመደሙት። ደሃ አካለ ጎዶሎ አድርገው ለሌላ የስልጣን ዘመናቸው መማማል ጀመሩ። አይ ካድሬዎች። ደግሞ አቅፈው ይስሟቸዋል። አቅፈው ስመዋቸው አብረው ለትዝታ ፎቶ ይነሳሉ። በዕብሪት አመድ ካደረጓቸው ጎን ቆመው ፊልም ይቀረጻሉ። ዞረው ደግሞ ” ወብድሜን አጣሁ፣ እናቴን አጣሁ” ብለው ያለሳሉ። ከዚህ በላይ ምን ድንዛዜ አለ? እዛው “ወንድሜን አምጣ” እንዳይለው ለሌሎች መናገሩ፣ ይህንኑም ሚዲያዎች መቧጨቃቸው ነገሩን አንገት የሚያስደፋ ያደርገዋል።

See also  መንግስት የሰላም ስምምነቱን መሰረት በማድረግ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተገበረ ነው

“በአጭር ጊዜ ጠቅ ጠቅ አድርገን እንጨርሰዋለን፤ ጊዜ እንዲወስድ አንፈልግም” እያለ የቅዠት ትንተና ሲሰጥ የነበረው የዳንኤል ብርሃኔ (እስካሁን የት እንዳለ ድምጹ አልተሰማም) ወንድም ፍጹም ብርሃኔ አሳዛኝ ጥሪ ማስተላለፉ ከላይ የተባለውን የሚያጸና ነው። የጦርነቱ ውጤት ሲሰላ ከንቱ ሞትና አካለ ጎዶሎ መሆን እንደሆነ እየነገረን ነው። ” ይልቁኑ ዊልቼር አምጡ” ማለቱ ትርጉሙ ከቢድ ነው። ለትግራይ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም አካባቢዎች።

“ከውጪ አገር ወደ አገር ቤት የምትመጡ ተጋሩዎች ከቻላችሁ አንድ ዊልቼር ይዛችሁ እንድትመጡ እማፀናችኋለሁ ፤ የበርካታ ወጣቶችን ተስፋ ታለመልማላችሁ” ሲል ነው በትግርኛ ጥሪውን ያቀረበው። የፍጹም ጥሪ አግባብነት ያለውና ለጊዜውም ቢሆን ወደ ቀልቡ መመለሱን የሚያመላክትና ሌሎች ወደ ቀልባቸው እንዲመለሱ የሚገፋ መልዕክት ሆኖ ተገኝቷል። ፍጹም የቀድሞ ቀረርቶውን አስቦ ከራሱ ጋር እልህ ሳይጋባ፣ ወቅታዊ እውነታውን ተረድቶ ይህን ማለቱ በሌሎች አካባቢም ተመሳሳይ ችግር እያለ እዛ ላይ ማተኮር ትተው “አካኪ ዘራፍ እያሉ የጦርነት እስክስታ ለሚመቱ ትምህርት የሚሰጥም ይሆናል።

አንዳንዶች ትግራይ ምድር ላይ ምን እንደሆነ አሁንም ያልገባቸው ” ከብልጽግና ጋር ሆነን ሻዕቢያን እንውጋ፣ እሱ አይሆንም ከሻዕቢያ ጋር ሆነን ኢትዮጵያን እንውጋ” እያሉ በሃሳብ እየባጠጡ ነው። እንሱ የሚደናቆሩትን ዕልቂት ጠማቂዎች ወግዱ በማለት ፍጹም ላቀረበው ጥያቄ ኢትዮጵያዊያን ምላሽ ሊሰጥ ግድ ነው። መሬት ላይ እየተንደባለላችሁ ፊልም ስትሰሩ የነበራችሁ፣ በአንድ ሌሊት በሚሊዮን ስታዋጡ የከረማችሁ አሁን ዊልቸር ለማስገባት ተሟሟቱ። ይህ የወቅቱ ጥያቄ ነው። ይህ ቢያንስ በራሳችሁ ብር ላወደማችሁት ምድርና ” ግፋ በለው” እያላችሁ ላስጨረሳችሁት ወጣት ቢያንስ ሽርፍራፊ ምህረት ያሰጣችኋል።

“እናቴን አላገኘኋትም!”

አሠልጣኝ ኃይለ ኢያሱ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ዩጂን – ኦሬገን ላይ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፕዮና በሴቶች አሥር ሺህ ሜትር የተሰለፈችው አትሌት ለተሰንበት ግደይ አሰልጣኝ ኃይለ ኢያሱ ከሁለት ዓመት መለያየት በኋላ ዛሬ ከቤተሰቦቹ ጋራ መተያየቱን እና እናቱን ግን እንዳላገኛቸው ገልጿል። “ሰላም ያመጡ ሰዎችን አመሰግናቸዋለሁ። ወደ ሀገሬ በመምጣቴም ደግሞ በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ። ሆኖም እናትና ሀገር አንድ ናቸው። ባጋጠመው ሊሆን በማይገባው ሁኔታ በመድኃኒት እጦት ምክንያት ሕይወቷ ማለፉን ነግረውኛል” ሲል እያነባ ስሜቱን ለቢቢሲ ነበር የገለጸው። ቢቢሲ ለተቀጠረበት ዓላማ ጦርነቱን ሲያነድና ሲቆሰቁስ የነበረ፣ የትግራይ ወጣቶች እንዲነሱ ወስዋሽ መረጃ ከሙያው አፈልግጦ ሲበትን እንዳልነበር፣ ዛሬ ለቅሶና ሲቆሰቁሰው የነበረው ጦርነት ያስከተለውን ማህበራዊ ወለምታ ማስተጋባት ጀምሯል።

See also  የአማራና የትግራይ ህዝብ ወደ ሰላማዊ ግንኙነት

ዶክተር ደብረፅዮን ስለ ደራርቱ ቱሉ ምን አለ ?

በመቀሌ በተካሄደው የአትሌቶች ውይይይ ላይ ክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሆኑት ዶ/ር ደብረጽዮን ” ከሁሉም በፊት በራሴና በትግራይ ህዝብ ስም ደራርቱን ላመሠግን እወዳለሁ ፤ ከዚህ ቀደም ወደ ጦርነት እንዳንገባ ወደ’ኔ እየደወለች ነገሩ የከፋ ደረጃ እንዳይደርስ እባካችሁ ለህዝባችሁ ስትሉ ሁለታችሁም ተሸነፉ ስትል ስለሰላም ያላትን ፅኑ አቋም ስታንፀባርቅ ነበር” ሲሉ ተናግረዋል። ልባቸው በእብሪት በተሞላበት ወቅት ” ውጊያው አልቋል፣ እጃችሁን ስጡ” ሲሉና ” እኛ ስለማ ነን ሰላም የሌለባቸው ቦታ ሂዱ…” በሚል ዕርቅ የገፉት ሰውዬ ይህን ሲሉ ” ደብረጽዮን ይህን አሉ” እያሉ እንደ ትልቅ መሪና አሳበ ያለው ሰው ሲቀባበሉት ማየት ዓሳፋሪ ነው።

” ተሸንፈናል፤ ሽንፈታችንን ግን አሳምሩልን” ብሎ በጌቶቻቸው አማካይነት ከሞት የተረፈው የትህነግ መሪ ” ደራርቱ በችግራችን ወቅት ከጎናችን የነበረች የሰላም ሰው በመሆኗ ደግሜ ደጋግሜ አመሠግናታለሁ ፤ ከትግራይ አትሌቶች ጎን እንደ እናት በመሆን ብርታት የሆነቻቸው ደራርቱ የትግራይ አትሌቶች በችግር ውስጥም ሁነው በአለም አደባባይ የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ ከፍ ማድረግ በመቻላቸው ክብር ይገባቸዋል ፤ የፅናትም ተምሳሌቶች ናቸው።” ሲሉ ያለ አንዳች አፍረት መናገራቸው ለወደፊት ካድሬን የምርጫ ዋዜማ ካልሆነ በስተቀር በየትኛውም አግባብ ማመን እንደማይቻል ማረጋገጫ ንግግር ከመሆን የዘለለ አይሆንም።

ዛሬ ላይ በመናበብ የሚሰሩ የአማራና የኦሮሞ ጽነፈኞችን የሚደግፉ በተመሳሳይ ዊልቼር ከመለመን ወደሁዋላ እንደማይሉ መታመን አለበት። ምክንያቱም እነዚህ ጽነፈኞች ከትህነግ በላይ መሳሪያ፣ ጦር፣ የፖለቲካ ሃይል፣ አደረጃጀት፣ ሃብት፣ … የላቸውም። ኢትዮጵያ መከላከያው ባዶ ቤት ሆኖ፣ የስለላ ተቋሟ ፈርሶ፣ ፖሊስ አልባ ሆና ትህነግን ከትክታዋለች። ትዕቢቱን አስተንፍሳ ለማኝ አድርገዋለች። እናንተ ከትህነግ አንጻር ኢምንት ናችሁና ነገ በተመሳሳይ ዊልቼር ከመለመን፣ ወጣቱን ከማስጨረስ ተቆጠቡ። አቁሙ። ትግላችሁን የሰለጠን አድርጉ።

ተጻፈ ከበላይነህ ደበል

Leave a Reply