ብልጽግና አክራሪነትና በፖለቲካ ገበያ ትርፍ ለማግኘት በሚተጉ ላይ የጋራ አቋም መያዙን አስታወቀ

  • በፖለቲካ ገበያ ትርፍ ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት እና የአክራሪነት እንቅስቃሴን ለመታገል በየደረጃው ያለ አመራር የጋራ አቋም ይዟል

በፖለቲካ ገበያ ትርፍ ለማግኘት የሚደረገውን ጥረትና የአክራሪነት እንቅስቃሴን በመታገል የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ለማስቀጠል በየደረጃው ያለ አመራር የጋራ አቋም መያዙን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።

በከተማ አስተዳደሩ ከወረዳ ጀምሮ በተለያዩ የኃላፊነት እርከኖች የሚገኙ ከ1 ሺህ በላይ የሥራ ኃላፊዎች ለሁለት ቀናት የውይይት መድረክ አካሂደዋል።

የውይይቱን መጠናቀቅ ተከትሎ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ እና የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ መለሰ ዓለሙ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የመዲናዋ የሥራ ኃላፊዎች በመድረኩ አገራዊ እና ፖለቲካዊ የጸጥታ ሁኔታን በሚመለከት ጥልቅ ግምገማ በማካሄድ የጋራ ግንዛቤ በመያዝ የአፈጻጸም አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።

የሕዝብን ሰላም እና አንድነት በማጠናከር ለጋራ ልማት እና ተጠቃሚነት በትብብር ለመሥራት በከፍተኛ ኃላፊነት እና ቁርጠኝነት አቅጣጫ መቀመጡን አቶ ጃንጥራር ገልጸዋል።

የፖለቲካ ንግድ ተዋናዮች በተለይም ለአመራሩ ፈተና መሆናቸውን በመገንዘብ ለዚሁ የሚመጥን ምላሽ የሚሰጥ አመራር አስፈላጊ መሆኑም ታምኖበታል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የነበረችበትን ሁኔታ በቅጡ በመረዳት ችግሮችን ለመሻገር ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን የገለጹት ምክትል ከንቲባው፤ በሂደቱ በፈተና ውስጥ ስኬትን ማስመዝገብ የተቻለበት ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።

በዚህ ሂደት ችግሮችን በማለፍ የተመዘገቡ ውጤቶችን እንደ መልካም ተሞክሮ በመውሰድ በቀጣይ ለተሻለ ስኬት መዘጋጀት እንደሚገባ የጋራ አቋም ተወስዷል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ መለሰ ዓለሙ በበኩላቸው፣ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የአመራር ውይይት የሰላም እና የጸጥታ ችግሮችን በጋራ ታግሎ በማስወገድ ለዘላቂ ልማትና ብልጽግና ለመሥራት በጋራ መቆም የሚያስችል ግንዛቤ የተያዘበት መሆኑን ገልጸዋል።

የመዲናዋን ሰላም እና ደኅንነት በማደፍረስ ነዋሪዎቿን ስጋት ላይ የሚጥሉ ውስጣዊና ውጫዊ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ በመገንዘብ አመራሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትብብር መሥራት እንዳለበት መግባባት መፈጠሩን ተናግረዋል።

የመዲናዋ አመራሮች ለሰላምና ልማት እንቅፋት የሆኑ የጥፋት ዕቅዶችን በማክሸፍ እንዲሁም ሌብነት እና ብልሹ አሰራርን በመታገል ለሕዝብ አገልጋይነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ ለመሆን የጋራ አቋም መያዙን ገልጸዋል።

See also  የኤርትራ መንግሥት በእስራኤል በተፈጠረው ግጭት ሞሳድ ድጋፍ አድርጓል አለ ፤ ተመድ የኤርትራዊያንን በጅምላ መባረር ነቀፈ

የኢትዮጵያን ዕድገት እና የተጀመሩ ስኬታማ ተግባራትን በማስቀጠል የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በጋራ ተጋፍጦ ማለፍ እንደሚገባም በመድረኩ ተነስቷል።

በባህል፣ በብሔር እና በእምነት በተቆራኘው የመዲናዋ ነዋሪ መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለመመከት አመራሩ የጋራ አቋም መያዙ ተገልጿል።

በተለያዩ አጋጣሚዎች እና አቋራጭ መንገዶች የፖለቲካ ገበያ ትርፍ ለማግኘት የሚደረገውን የጥፋት እንቅስቃሴም በጋራ መታገል ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም የመዲናዋ አመራሮች የጥፋት እንቅስቃሴዎችን በመታገል የነዋሪዎችን የዕለት ተለት ችግር የሚፈቱ ተግባራትን በማከናወን ሌት ከቀን መትጋት እንዳለባቸው የጋራ አቋም ተወስዷል።

የኑሮ ጫናዎችን ለማቃለል የሚደረጉ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የዜጎችን ተጠቃሚነት እውን ማድረግ የአመራሩ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ እንደሚሆንም የጋራ መግባባት ላይ መደረሱ ተገልጿል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

Leave a Reply