አዲስ አበባና ዙሪያዋን በሽብር ለማናወጥ ተዳራጅቶ ሲንቀሳቅስ የነበረ ሃይል ከነትጥቁ ተያዘ

በአዲስ አበባ ከተማና በዙሪያው ሽብር፣ ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ፀረ-ሰላም ኃይሎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ገለጸ።

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ቀደም ሲል በአደረገው ግምገማ ስጋቶችን በመለየት በአዲስ አበባ ከተማና ዙሪያው በአካሄደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን የተያዙ የተጠርጣሪዎች እና የጦር መሣሪዎችን የምርመራ ውጤት በቀጣይ ለኅብረተሰቡ እንደሚያሳውቅ ቃል መግባቱ ይታወቃል።

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል እየተወሰደ ባለው የተቀናጀ ህጋዊ እርምጃ ተሸሽገው አዲስ አበባ ከተማ በመግባት የሽብር ጥቃት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 107 የአሸባሪው ሸኔ ቡድን አባላት ለጥቃት ከሚጠቀሙባቸው የጦር መሣሪያዎችና ከተለያዩ የፀጥታ መዋቅር አልባሳት ጋር በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

በተመሳሳይ የጽንፈኛ ፋኖ ቡድን አንዳንድ የፖሊቲካ ፓርቲዎችን እንደ ሽፋን በመጠቀም የአዲስ አበባ ከተማን የሽብርና የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ ሐሰተኛ መታወቂያዎች በመያዝ እና በትምህርት ቤቶች የተነሱ አንዳንድ ጥያቄዎችን አቅጣጫ በማሳት ለእኩይ ዓላማ በመጠቀም የከተማውን ህዝብ በብሄር ለማጋጨት እና ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር እንዲሁም የተለያዩ በትጥቅ የታገዘ ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 109 የቡድኑ አባላት ከሚጠቀሙባቸው የጦር መሣሪያዎችና ከተለያዩ የፀጥታ መዋቅር አልባሳት ጋር በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

በሌላ በኩል ተደራጅተው በጦር መሣሪያና በድምጽ አልባ የስለት መሣሪያዎች በመታገዝ በሰዎች ላይ ጉዳት በማድረስ ዘረፋ በመፈፀም ኅብረተሰቡን ስጋት ውስጥ የጣሉና ያማረሩ 155 ተጠርጣሪዎች ከዘረፏቸው እና ሲጠቀሙባቸው ከነበሩ መሣሪያዎች ጋር ከነ-ግብረ አበሮቻቸው በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን ግብረ-ኃይሉ ገልጿል።

በአጠቃላይ የአዲስ አበባ ከተማን እና ዙሪያውን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ግብረ-ኃይሉ ከህዝቡ ጋር ተቀናጅቶ በአካሄደው ኦፕሬሽን 371 ተጠርጣሪዎችን ለሽብር ካዘጋጁት የጦር መሣሪያ እና ከዘረፏቸው ንብረቶች ጋር በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን ገልጿል።

ከተጠርጣሪዎቹም ሚስጥራዊ ሰነዶች፣ ሐሰተኛ መታወቂያዎች፣ የክላሽንኮቭ ጠመንጃዎች፣ ቦንቦች፣ ሽጉጦች፣ በርካታ ጥይቶችና የተለያዩ የፀጥታ መዋቅር አልባሳት እንዲሁም ለእኩይ ዓላማቸው ማስፈፀሚያ የሚጠቀሙበት ገንዘብ፣ የዘረፉት ተሽከርካሪዎችና የተለያዩ ንብረቶች በኤግዚቢትነት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታውቋል፡፡

See also  የአሜሪካ ዜጎች አሁኑኑ ዩክሬንን ለቀው እንዲወጡ ጆ ባይደን አሳሰቡ

የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብ-ኃይል ኅብረተሰቡ እስከአሁን ለአደረገው ቀና ትብብር ምስጋና እያቀረበ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኅብረተሰብ ክፍል አደባባይ ወጥቶ ለሚያከበረው የጥምቀት በዓል በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች በርካታ የፀጥታ አካላት አሰማርቶ በዓሉ በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጿል።

የጥምቀት በዓል በተለይ በአዲስ አበባ በርከት ያለ ህዝብ እና ከተለያዩ ዓለም ሀገራት የሚመጡ ቱሪስቶች የሚታደሙበት በመሆኑ የእምነቱ ተከታዮች እና ከተማው ነዋሪዎች በተለየ ሁኔታ ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር ተቀራርበው እንዲሠሩ ጥሪውን አቅርቧል።

መላው ሕዝብ ፀረ-ሰላም ኃይሎች የሚያደርሱትን ጥፋት በውል ተገንዝቦ እንደተለመደው ሁሉ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ በማድረግ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ሰላሙን የሚያደፈርሱ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች እንዲሁም በስልክ ቁጥር 011-1-11-01-11፣ 251115-52-63-03፣ 251115-52-40-77፣ 251115-54-36-78 እና 251115-54-36-81 በፍጥነት ጥቆማ መስጠትና በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች መረጃውን በአካል ማድረስ እንደሚቻል እያሳወቀ በዓሉ የሰላምና የፍቅር እንዲሆን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ከልብ ተመኝቷል፡፡

Leave a Reply