“ጥምቀትና መተጫጨት”

የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ሥነሥርዓቱም ባሻገር ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊና ባህላዊ ክዋኔዎች የሚስተናገዱበት ነው።

እናም ጥምቀትን ተከትሎ ተውቦና አምሮ የበዓሉ ድምቀት ኾኖ መዋል ሁነቱ የሚፈቅደው ጉዳይ ነው።
“የኔ ውድ፣ አምሮብሻል፣ አምሮብሃል “ለመባል ከሥነ-ልቦና እስከ አለባበስ ልቆ ለመታየት የማይደረግ ዝግጅት የለም።

“የጥምቀት እለት ያልኾነ ቀሚስ ይበጣጠስ” በሚል ሀገረኛ ብሂል ያለው  ወቅቱ የፈቀደውን እየገዙ በአዳዲስ  ፋሽን ልብስ  ተውቦ መውጣት።

ያልቻለው ደግሞ ያለውን አጥቦ ጽድት ብሎ መታየትን ይሻል። ይህ ሁሉ ዝግጅት ታዲያ በተላይም በወጣቶች ዘንድ  ከማማርና በዓሉን ተውቦ ከማሳለፍ የተሻገረ ዓላማ  አለው።

አምራና ተውባ የመጣች ቆነጃጅት፣ ቆንጆ ፍለጋ አይኑ ከሚንከራተት ጎረምሳ ልብ ውስጥ ለመግባት ስውር እሽቅድድሞሽን ታደርጋለች።

የጥምቀት በዓል “የትዳር አጋርን ለራስ ሸልሞ የመመለስ”  አጋጣሚን የሚፈጥር ሁነት እንደኾነ የአንዳንድ እድለኞችን ታሪክ በምስክርነት የሚጠቀስ ነው።

እናም ጥምቀት አንዱ የመተጫጫ መድረክ በመኾን አገልግሏል፣ እያገለገለም ነው። ሎሚ ደግሞ የ”ተፈልገሻል” መልእክተኛ በመኾን ሚናዋን ትወጣለች።

በዚሁ ጉዳይ ላይ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎቹ የ77 ዓመት አዛውንት ደሳለኝ አወቀ   እና ወጣት እድላዊት ገብሬ የጥምቀት ገጠመኞቻቸውን አውግተውናል።

አዛውንቱ እንደነገሩን በጥምቀት በዓል የሚታየው በሎሚ ውርዋሮ የመተጫጨት ጉዳይ የረዥም ጊዜ ታሪክ ያለው ነው።

“እኔም በጉብዝና ዘመኔ “በየዓመቱ ከበርካታ ቆነጃጅቶች ደረት ላይ ሎሚ አሳርፊያለሁ ይሉናል። ሎሚ ወርውሬ የፍቅር ጥያቄየን በተለያየ ጊዜ አድርሸ ነበር፣ ይሁንና የተወረወረችው ሎሚ ከሳቅ ከጨዋታው በቀር ለቁምነገር በቅታ እጮኛን መጠቅለል አላስቻለችኝም ይላሉ።

የሳቸው አይሳካ እንጂ በዚህ የጥምቀት እለት የሎሚ ውርዋሮ ለቁም ነገር የበቃ ትዳር የተመሰረተ እንደሚያውቁ ነው የነገሩን።

“የሎሚ ውርወራ የራሱ ሥነሥርዓት አለው” የሚሉት አዛውንቱ ደሳለኝ በጥምቀት ተውባ የመጣችን ቆንጆ ተመልክቶ ቀልቡ የተሰረቀ ወጣት በያዘው ሎሚ ወርውሮ ደረቷንና አካባቢው ይመታል።

በዚህን ጊዜ ቆንጅት ሎሚውን አንስታ የወረወረላትን ሸበላ በአጽንኦት ትምለከታለች።

ከወደደችው  የተወረወረላትን ሎሚ መልሳ በመወርወር ትመታዋለች፣ አሊያም ሎሚዋን  ያዝ አድርጋ በአፍንጨዋ ታሸታትና ይሁንታዋን ትገልጽለታለች።

ከዚያም እድለኞች ናቸውና ትውውቃቸውን ለቤተሰብ ተናግረው በወግ በማእረጉ እንደ ሀገሬው ባህል ይሞሸራሉ ሲሉ አስረድተውናል።

See also  ትህነግ ወደ"መቆላመጥ ፖለቲካ" አደገ፤ "መልካም ጎረቤት ያስፈልገናል" ደብረጽዮን

ሌላዋ የጥምቀት ገጠመኟን የነገረችን ወጣት እድላዊት ገብሬ ይህ የጥምቀት እለት ሎሚ ወርውሮ የፍቅር አጋርን “ለራስ የመሸለም” ባህል ዛሬም ድረስ እንደቀጠለ ማሳያ ነው።

እድለኛዋ’ እድላዊት የጥምቀት እለት የተወረወረላትን ሎሚ አላባከነችም።

“ከጎረምሶቹ መካከል የተወረወረው አይኔ ድንገት ከአንድ ወንዳወንድ ሸበላ ልጅ ላይ አረፈ” ትላለች ወጣቷ።
“እሱም ትኩረቴን አወቀና አይኑን ከኔ አላራቀም፣ እድሉን ተጠቅሞ እሽታዬን ማግኘት ፈለገ፣ ሎሚ ወደ እኔ ተወረወረ ቀለምኳትና ሎሚዋን ማባከን አልፈለኩም እሽታዬን ገለጽኩለት” ትላለች።

በዚህ ሁኔታ የተፈጠረ ትውውቅ ዛሬ ላይ  በፍቅር የአብሮነት ጊዚያቸውን እያሳለፉ  አራት ዓመት እንደሞላቸው ነው ያጫወተችን።

ለጥምቀት አቅም በፈቀደ ተውቦና አምሮ መውጣት ጥሩ ነው የምትለዋ ወጣት እድላዊት አጋጣሚውን ተጠቅሞ የትዳር አጋርን ማፈላለግ፣ በወግ በባህሉም ለቁም ነገር ማብቃት ይገባል ባይናት።
መልካም የጥምቀት በዓል !
   አሚኮ

Leave a Reply