የሸኔ ቡድን የሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎችን …

የሸኔ ቡድን የሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎችን ወደነበሩበት የማኅበረ-ኢኮኖሚና ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ የፌደራልና የክልሉን የጸጥታ ኃይል ባጣመረ ግብረ ኃይልና ኅብረተሰቡንም ባሳተፈ ሁሉንም አማራጭ ያካተተ ርምጃ እየተወሰደ ነው፡
➖የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ጥር 10 2015 በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫቸው ነው የሸኔ የሽብር ቡድን በኦሮሚያና አጎራባች አካባቢዎች በተለየ፣ እንደ ሀገርም በጠቅላላው የፈጠረውን የሰላም ሥጋት፣ ያስከተላቸውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች እንዲሁም ሥነ ልቦናዊ ስብራቶችን ለመግታት መንግሥት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ቅንጅታዊ ተግባር ላይ ነው ያሉት፡፡

የሽብር ቡድኑ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሕገ ወጥ ታጣቂዎችን በማሠማራትና በማቀናጀት፣ ከሌሎች የሥጋት ኃይሎች ጋር ጥምረት በመፍጠር፣ በንጹሐን ዜጎች ሕይወት፣ ሀብትና ንብረት፣ በመሠረተ ልማቶች ላይ የደቀነውን አደጋ ለመቀልበስ የተቀናጀ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንና መንግስት ለዚህ ችግር ፖለቲካዊና ሰላማዊ አማራጮች የመጀመሪያ ምርጫዎች መሆኑንም አንስተዋል።

ምንጊዜም ችግሮችን በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት መንግስት ቅድሚያ ይሰጣል ያሉት ዶክተር ለገሰ ከዚህ ቀደም ችግሩን በሰላም አማራጭ ለመፍታት መንግሥት ያደረገው ጥረት ያልተሳካው በዋናነት በሸኔ መሠረታዊ ችግር ምክንያት እንደሆነና ሸኔ የሰላም ጥሪውን ተቀብሎ እኩይ እንቅስቃሴውን እንዲያቆምና በዜጎች ላይ የሚያሰደርሰው ጥፋት እንዲያበቃ መላዉ ሕዝብ ግፊት ማድረግ እንዳለበትም ነው ያሳሰቡት።

ሸኔ በኦሮሞ ሕዝብ ስም የሚንቀሳቀስ ቢሆንም በዋነኛነት የሚያጠቃዉ ራሱን የኦሮሞን ሕዝብ ስለመሆኑ የጠቀሱት ሚኒስትሩ ቡድኑ የሚደገፈዉና የሚመራዉ ደግሞ ኢትዮጵያን ማዳከም በሚፈልጉ የዉስጥና የዉጭ ኃይሎችም ጭምር ነዉ ብለዋል፡፡
ሸኔ የኦሮሞ ሕዝብን መብትና ጥቅም መሠረት ያደረገ ዓላማ የለዉም ያሉት ሚኒስትሩ በሕዝቡ ግፊትና በለውጡ አመራር የተሳካው ሀገራዊ ምቹ የፖለቲካ ምኅዳር በሰላማዊ መንገድ ለሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ተዋንያን የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠሩንና የትጥቅ ትግል ለማድረግ የሚያስገድድ ነባራዊና ኅሊናዊ ሁኔታ አለመኖሩን መገንዘብ ይገባል ብለዋል፡፡

መንግሥት በየደረጃው ከሚገኙ አመራሮች፣ ከኅብረተሰቡ ከተወጣጡ አካላትና በየቀበሌው ከሕዝቡ ጋር በሰላም አማራጭ ዙሪያ ውይይቶችን እያደረገ እንደሚገኝና በተለያየ ምክንያት ወደ ሽብር ቡድኑ የተቀላቀሉ ወጣቶች በሰላም ለመንግሥት እጃቸውን ሰጥተው ተሐድሶ ወስደው ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑንና በዚህም በርካታ ወጣቶች ወደ ሰላማዊ ኑሯቸው እየተመለሱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሁኔታዎች ባልተቻሉበት አካባቢ የሽብር ቡድኑ በንጹሐን ዜጎች ሕይወት እንዲሁም በንብረትና በመሠረተ ልማት ላይ ጉዳትና ማስተጓጎል እያደረሰ ባለበት አካባቢ መንግስት የኃይል ርምጃ እየወሰደ እንደሆነና በርካታ የቡድኑ ታጣቂዎችና ሎጂስትክስ አቅራቢዎች ላይም ርምጃ ወስዷል ነው ያሉት፤ ዶክተር ለገሰ ቱሉ፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር፣ ጥር 10 2015

See also  "የጥፋት ሃይሎችና" ገንዘብ ተያዘ ፤ በቀናት ውስጥ ከ200 በላይ ሰርጎ ገቦች ተይዘዋል

Leave a Reply