በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ለሚገነቡ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያስፈልጋል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ለማስገንባት ላቀዳቸው የኃይል ማመንጫ፣ ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶች 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው የተቋሙ የስትራቴጂ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን ተሾመ የተቋሙ የሦስት ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ለውይይት ሲቀርብ እንደገለፁት አስር የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ከንፋስ እና ከፀሐይ ኃይል ለመገንባት ዕቅድ ተይዟል።

በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ተቋሙ አሁን የደረሰበትን 16 ሺህ ጊጋ ዋት ሰዓት የማመንጨት አቅም ወደ 27 ሺህ ጊጋ ዋት ሰዓት ከፍ ለማድረግ ማቀዱን ነው አቶ ወንድወሰን የገለፁት።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ አሰላ ንፋስ እና አሉቶ ጂኦተርማል ፕሮጀክቶች በዕቅዱ ታሳቢ በመደረጋቸው በቀጣይ ዓመታት ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ከፀሐይ ኃይል በዲቼቶ፣ ጋድ አንድ እና ሁለት፣ ወለንጪቲ እና ወራንሶ አካባቢዎች እንዲሁም ከንፋስ ኃይል በኢተያ፣ አይሻ አንድ እና ሦስት አካባቢዎች የአዳዲስ ፕሮጀክቶች ግንባታ በማከናወን የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመነጩ በመሪ ልማት ዕቅዱ መካተቱን ገልፀዋል።

የኃይል ማመንጫዎቹን ለመገንባት የግል ባለሃብቶች ተሳትፎ እንደሚጠበቅ የጠቆሙት አቶ ወንድወሰን አጠቃላይ የፋይናንስ ግምታቸው ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

በግሉ ዘርፍ ሊለሙ ከታቀዱት የንፋስ እና የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች ላይ ኃይል ለመግዛት የታሪፍ ዋጋ ክለሳ ተሰርቶ መጠናቀቁንም ነው አቶ ወንድወሰን ያብራሩት።

በቀጣይ ሦስት ዓመታት ከ3 ሺህ 8 መቶ ኪሎ ሜትር በላይ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ለመገንባት መታቀዱን የገለፁት ዳይሬክተሩ 61 አዳዲስ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን ለመገንባት መታቀዱን ጨምረው ተናግረዋል።

በ52 ነባር የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የአቅም የማሳደግ እና የማሻሻያ ሥራዎች ለማከናወን መታሰቡንም ነው አቶ ወንድወሰን ያብራሩት።

የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮቹን ለመገንባት ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የፋይናንስ ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን ከዚህ የፋይናንስ ወጪ ውስጥ 84 ነጥብ 1 ከመቶ የሚሆነውን ተቋሙ ከራሱ ገቢና ከአበዳሪ ባንኮች በሚያገኘው የብድርና ድጋፍ የሚሸፍን መሆኑን ገልፀዋል።

ከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ቀሪ 12 በመቶ የሚሆነውን የፋይናንስ ወጪ ይሸፍናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው ያስረዱት።

See also  የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ለዩኒቨርስቲ መውጫ ፈተና ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ የትምህርት ሚኒስቴር አሳሰበ

የሦስት ዓመት መሪ የልማት ዕቅዱን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም የተቋሙ ሠራተኞች እና የሥራ ኃላፊዎች ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የጠቀሱት አቶ ወንድወሰን ተቋሙ የሰው ኃይል አደረጃጀቱን ከማዘመን ጀምሮ የአስተሳሰብ ሪፎርሞችን በማከናወን ለዕቅዱ መሳካት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

(ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል)

Leave a Reply