“የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በበጀት ዓመቱ 7.5 በመቶ እንደሚያድግ ይጠበቃል” የፕላንና ልማት ሚኒስቴር

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዘንድሮ በ7 ነጥብ 5 በመቶ እድገት የሚመዘግብበት መሆኑን የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም እንደሚያመላክት ተጠቆመ።

የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ተካሂዷል።

በመድረኩም የበጀት ዓመቱ የስድስት ወራት ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚና የዘርፎች አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።

ሪፖርቱን ያቀረቡት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ÷ በ2014 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 6 ነጥብ 4 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን አስታውሰዋል።

በዘንድሮው በጀት ዓመት ደግሞ በ7 ነጥብ 5 በመቶ እድገት የሚመዘገብበት መሆኑን የስድስት ወራት አፈፃፀሙን መነሻ በማድረግ አብራርተዋል።

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካቾች የተመዘገቡት ውጤቶች ደግሞ ይመዘገባል ተብሎ ለተቀመጠው እድገት እውን መሆን አመላካች ስለመሆናቸው አብራርተዋል።

የግብርናው ዘርፍ እድገቱን በማስቀጠል ረገድ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ሴክተር መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ዘርፉ ባለፉት ስድስት ወራት የ6 ነጥብ 7 በመቶ እድገት አስመዝግቧል ብለዋል።

የግብርና ዘርፍ የወጪ ንግድን በመደገፍ ለኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ሚና እያበረከተ መሆኑንም ገልጸዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በውስጣዊ ችግሮችና ውጫዊ ጫናዎች ከፍተኛ ፈተና ገጥሞት የነበረው የኢንዱስትሪ ዘርፍም ዘንድሮ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቡን ተናግረዋል።

ዘርፉ ባለፉት ስድስት ወራት በርካታ ፈተናዎችን ተቋቁሞ የ8 ነጥብ 2 በመቶ እድገት ማስመዝገቡንም ገልጸዋል።

ከታክስና ታክስ ካልሆኑ ምንጮች የሚገኘው የአገር ውስጥ ገቢም ከፍተኛ አፈጻጻም ካስመዘገቡት መካከል ይጠቀሳል ብለዋል።

በስድስት ወራት ከታክስና ታክስ ካልሆኑ ምንጮች 222 ቢሊዮን ብር የአገር ውስጥ ገቢ መገኘቱን ጠቁመው፤ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር የ28 ነጥብ 9 በመቶ እድገት እንዳለው ተናግረዋል።

የወጪ ንግድ አፈጻጸም መጠነኛ ቅናሽ ቢያሳይም ከዘርፉ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰው አፈጻጸሙ ከእቅዱ ጋር ሲነጻጸር 77 በመቶ መሆኑንም ዶክተር ፍጹም አብራርተዋል።

በዓለም ገበያ ያለው የምርቶች ዋጋ ተገማች አለመሆን፤ የህገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ መስፋፋት፤ በንግድ ሰንሰለቱ ያሉ ማነቆዎችና ሌሎች ተያያዠ ችግሮች የወጪ ንግድ ዘርፍ ፈተናዎች መሆናቸውንም አስረድተዋል።

See also  በማይጠብሪ ግንባር በጠላት ላይ ከባድ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ ደረሰ - ስትራቴጂክ ቦታዎችን ለቀቀ

በበጀት ዓመቱ አጋማሽ 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን ጠቅሰው፤ ይህም በተለይ የኢንዱስትሪ ዘርፉን በማነቃቃት ረገድ ከፍተኛ ሚና ያበረክታል ነው ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት በአገር አቀፍ ደረጃ በአጠቃላይ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩንም ጨምረው መግለጸቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የበጀት አመቱን የስራ ክንውን በተመለከተ በየሩብ ዓመቱ የአፈፃፀም ግምገማ የሚካሄድ መሆኑ ይታወቃል።

በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Leave a Reply