ኦርቶዶክስ “የሕዝብ ቀይ መስመር”- ፖለቲካ የኦርቶዶክስ ቀይ መስመር

አገር ነች። ታሪክ ነች። ቅርስ ናት። እምነት ሳይለይ የሁሉም ንብረት ናት። ማን ቢባል መልሱ ኦርቶዶክስ!! ይህቺን ታላቅ ቅርስ ተንከባክቦ መያዝ፣ መጠበቅና ለትወልድ ማስተላለፍ የሁሉም ወገን ፈንታ ነው። የግድ አማኝ መሆን አያስፈልግም። ስለዚህ ይህቺን ቤተ ክርስቲያን መንካት ቀይ መስመር ነው።

ትልቅነቷ ይህን ያህል እንደሆነ ከታመነ፣ የሁሉም ንብረትና ታሪክ የታጨቀባት ተቋም መሆኗን ቀድመው መሪዎቿ ማወቅና መረዳት ግዴታቸው ነው። እንዲህ ያለ ታላቅ ተቋም የሚመሩ ካድሬነትን ደርበው፣ የፖለቲከኞች ዋሻ ሆነው መኖር አይቻላቸውም። ይህ ደግሞ ለራሷ ኦርቶዶክስ ቀይ መስመሯ ነው። ይህ ማለት ቤተክርስቲያን ሃላፊነቷ ግዙፍ መሆኑን፣ የተለያየ ፍላጎትና ዝንባሌ ያላቸውን አቅፍ ስለምትሄድ አጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ግዴታዋ ነው ማለት ነው።

ሁለት ቀይ መስመሮች ሊሰመሩ እንደሚገባ የጥሞናው ሰፈር ነዋሪዎች ሰዎች ናቸው የሚያሳስቡት። አንድ መስመር አስምሮ ሌላውን መተው አሁን ለተፈጠረው ቀውስ መፍትሄ እንደማይሆንም ይናገራሉ። መስመሮቹም ከላይ እንደተባለው ኦርቶዶክስን መንካት የሕዝብ ቀይ መስመር እንደሆነ ሁሉ፣ ኦርቶዶክስም ፖለቲካ ውስጥ መግባቷ ህዝብ ያሰመረላትን የዕምነት ቀይ መስመር መጣስ መሆኑንን መረዳት እንደሚገባት ያስረዳሉ።

ኦርቶዶክስ ታሪክ፣ ትውፊት፣ የኢትዮጵያ ምሳሌና ሚስጥር ናት። ቢያንስ እንደ ተቋም የየትኛውም ዕምነት ተከታዮች የሚንከባከቧትም ለዚሁ ነው። ይህ እውነት ቤተክርስቲያኒቱን ዘመን አሻግሯታል። ይህ አንድነቷ አኑሯት፣ እኛንም እንደ አገር አኑሮናል። ስለዚህ የዕምነት ደረጃው ልዩነት ካልሆነ በቀር ለኦርቶዶክስ አንድ ወገን ብቻውን ተነስቶ ልዩ ተቆርቋሪና ባለቤት ሊሆን እንደማይችልም በርካቶች መረጃ የሚጠቅሱበት ጉዳይ ነው።

አሁን ላይ በስሜት፣ ባለመረዳት፣ በማወቅና በራስ ፍላጎት በመመራት ከየአቅጣጫው የሚወጡ መረጃዎችና ” የክተት” ጥሪዎች ግራ የሚያጋባቸው አብዛኞች፣ ስለ ሁለቱ ቀይ መስመሮች የሚናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገረፍ አድረገው ባለፉት ሶስት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ተንተርሰው ነው። እሳቸው ባይሉትም በየቦታው የሚነገር ሃቅ ነው። “ስርቆት፣ ፖለቲካና የዘር ልዩነት” ወሯታል። በቅርቡ በነበረው የህግ ማስከበር ዘመቻ ቅዱስነታቸው፣ አቡነ ማቲያስ ዘርና ደም ቆጥረው ከውጭ ሚዲያዎችና አስተባባሪዎች ጋር ተናበው ለዓለም ያስተላለፉት “ኢትዮጵያን እነቁ” የሚል ጥሪ ታሪክ የማይረሳው ምስክር እንደሆነ መካድ አይቻልም።

በኦርቶዶክስ ቤት ለተነሳው ቀውስ ዋና ቁልፍ ጉዳዮች ካድሬነት፣ ሌብነት፣ ዘረኝነት የፈለፈሏቸው በሽታዎች ውጤት ነው። በሌሎች እምነት ቤቶችም ተመሳሳይ ቸግር ቢኖርም አሁን ላይ በተቋም ደረጃ ጎልቶ የወጣውና የታየው ኦርቶዶክስ በመሆኑ ትክረት ሳበ እንጂ ካዝናቸው በብር የታጨቀ አጭበርባሪ ነብያት፣ ተንባዮች፣ የተደራጁ መተተኞች፣ ዘይት ቸርቻሪዎች ጥቂት አይደሉም።

ችግሩ በውይይት እንዲፈታ ጥሪ የሚያቀርቡ ወገኖችን ማብጠልጠልና መፈርጅ ምርቃትን የሚያሰጥ ጉዳይ የሆነበት ይህ ችግር ለምን? እንዴት? በእነማን አማካይነት? ምን ተፈልጎ፣ ወዘተ ሊነሳ ቻለ? የሚል የሰከነ ጥያቄ አይቅርብበትም። ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን የሚያክል ታሪካዊ ዕምነት እዚህ ጣጣ ውስጥ የገባው ዛሬ? የቆየ ችግር ድምር? ልዩ ፍላጎት? ስልጣን? ምን……? ሳይጠየቅ አብዛኛው ሕዝብ ባይሆንም በማህበራዊ ገጾች የልዩ ፍልጎትና፣ የፍላጎት ማስፈጸሚያ ሆኖ ” አትነሳም ወይ” የሚል ክተት እየታወጀ ነው።

ስለ ኦርቶዶክስ ወቅታዊ ሁኔታ ብዙ ማለት ቢቻልም፣ ጥንቃቄ መምረጡ እጅግ አግባብ እንደሆነ የሚመክሩና የሚያስጠነቅቁ መንግስትን መጠነኛ ጥያቄ እየጠየቁት ነው። ኦርቶዶክስ በውስጧ መንፈሳዊነትን ቀብራ የካድሬዎች መሰባሰቢያና የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ መሆኗ ያሳዘናቸው፣ በዚህ በሽታ ላይ ሌብነት ታክሎበት ነገሩን እንዳፈነዳው ያምናሉ። የደህንነት ጉዳይና ኢኮኖሚ አጀንዳዎች ችግሩን እንዳፈነዱት በመግለጽ ጥያቄ የሚጠይቁ ወገኖች

ከፖለቲካ አኳያ

  • መንግስት እጅህ አለበት እየተባለ ስለሆነ እጁ ከሌለበት ህዝብ በነጻ ህሊና እንዲፈርድ ንጽህናውን ያሳይ፣ ራሱን ይግለጥ።
  • መንግስት እጁ ላይ ያለውን መረጃ ለምን ለሕዝብ ይፋ አያደርግም? መረጃው በቅርቡ ጊዳ፣ ኪረሙ፣ አገምሳ ሃሮና አካባቢውን በቅርቡ የመከላከያ ሃይል ሳይቆጣጠር ምን ተፈጥሮ እንደነበር፣ መከላከያ አካባቢውን በሃይል እርምጃ ካጸዳ በሁዋላ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ህዝብ ጠቁሞ ምን ተገኘ? ሁሉም ሲሆን በፊልም ሲቀረጽ ነበርና መንግስት ይህን መረጃ ለህዝብ ቢያሳይ፣ መረጃው ሕዝብ በምን ያህል ደረጃ ዕምነትን የፖለቲካ ዓላማ ማራመጃ እንዳደረገው ያሳይልና። የመደባበቁ ጊዜ ማብቃት ስለሚገባው ጭምር፤
  • ኦርቶዶክስ ብቻ ሳትሆን የተለያዩ ቤተ ክርስቲያኖች የአመጽ መተግባሪያ መሳሪያ ማከማቻ፣ የመረጃ መቀያየሪያ አውድና መመሸጊያ ሆነው ሲያገለግሉ እንደነበር፣ አንዳንዶቹ ጭልጥ ያሉ የፖለቲካ ጫካዎች እንደነበሩ የታውሳል። በቅርቡ በትግራይ የተለያዩ ቤተክርስቲያኖች ውስጥ መሳሪያ ተቀብሮ ሲወጣና ሲጋዝ፣ ፖለቲከኞችም ምሽግ አድርገዋት እንደታየው በምስራቅ ወለጋ እነማን ይህን፣ የትኛው ቦታና ቤተክርስቲአን ውስጥ ሲያከናውኑ እንደነበር ለሕዝብ እንዲገለጽ መንግስት መውሰን ይገባዋል። ይህ ሲሆን ህዝብ ሚዛኑንን ይጠብቃል። ሲሉ ጥያቄ አቅራቢዎቹ ይናገራሉ።
  • ለደህንነት ተቋሙ በሚያስቸግር መልኩ የሚካሄዱ ህግን ያልተከተሉ ተግብራት ማን፣ እንዴትና ለምን አደረጋቸው? የሚለው በይፋ በህዝብ ንብረት፣ ህይወት፣ የመኖር ዋስትና ሳይቀር የደረሰውን ኪሳራ ከቤተ ክህነት ስውር አደረጃጀትና ከፖለቲካ ግብ አንጻር ይፋ ይገለጽ። ይህን የሚያነሱ ክፍሎች ከ1992 ዓም ጀምሮ የሆነው ለህዝብ እንዲቀርብ፣ ሕዝብ ራሱ ለህዝብ እንዲናገር፣ በ1992 የመገናኛ መሳሪያዎች በምስራቅ ወለጋ ተነቃቅለው በፍተሻ የት እንደተገኙ ህዝብ ምስክርነቱን እንዲሰጥ ይደረግ፤
  • መንግስት ራሱም ራሱን መርምሮ ራሱን እንዲያርቅ፣ አርቆም በገሃድ ይቅርታ መጠየቅና በሚገባው ጉዳይ ሁሉ ይቅርታ እንዲጠይቅ፣ ጥያቄ ተነስቷል።

ከኢኮኖሚ አንጻር

  • ኦርቶዶክስ እጅግ ሃብታም፣ በርካታ የገቢ ምንጭ ያላት፣ መዕመናኖቿ እጃቸውን የሚዘረጉላት ናት። ቤተክርስቲያኗ በገንዘብ ብቻ በርካታ ቢሊዮን አላት። ግብር ከፋይ ያልሆነችው ኦርቶዶክስ በተደጋጋሚ ለሌብነት መጋለጧ በመረጃ ሳይቀር የሚቀርብባት ናት። አሁን ላይ ባሉ መረጃዎች ቤተ ክርስቲያኒቷ የግል ባንኮች ምስረታ ውስጥ ተሳታፊ ሆናለች። በአሃዝ መግለጽ ባይቻልም በግርድፍ መረጃ ቤተክርስቲያኒቷ አዲስ በሚቋቋሙ የብሄርና ክልል ተኮር ባንክች ውስጥ ሃብቷን ማከማቸቷ ቅሬታ ማስነሳቱን የሚያውቁ ገሃድ መረጃ ለህዝብ መቅርብ አለበት እያሉ ነው።
  • የአክሲዮን ግዢዎች በመዋቅርና በአካባቢያዊነት ስሜት መሰራቱን የሚያረጋግጥ ስሌት መንግስት እጅ ስላለ ያቅርብ፤
  • በገጠር ያሉ ቤተክርስቲያኖች በቂ ገቢ ስለሌላቸው? በነዚህ አድባራት የተመደቡ ቄሶች ጥለው እንደሚሄዱና ህዝብ አገልጋይ በማጣት ከፍሎ ዓመታዊ ንግሶችን እንደሚያከናውን ሰፊ መረጃ ስላለ፣ ደብሮቹም በተደረገ ጥናት የተለዩ በመሆናቸው ለህዝብ ይፋ ይሁኑ፤
  • በቅርቡ ሻምቡ አካባቢ (የደብሩን ስም መጥቀስ ባለማስፈለጉ ነው) ዓመታዊ ንግስ ሲያከብሩ ቀዳሽ አጥተው ከጎጃም ሰማኒያ ሺህ ብር ከፍለው በዓሉን እንዳከበሩ መረጃና ማሳያ አለና ለህዝብ ይቅረብ፤

ከመብት አንጻር

ሕዝብ በመረጠው ቋንቋ የመማር፣ የመሰልጠን፣ የመዳኘት፣ የመስራት መብት ስላለው፣ ይህ ህገመንግስታዊ መብት በመሆኑ ከዚህ አንጻር ቤተክርስቲያን የቀረበላትን ጥያቄ በአግባቡ ማስተናገዷ በመረጃ፣ በቁጥር ተደግፎ ጥያቄ ከሚያቀርቡት ወገኖች ብዛት አንጻር አጣርቶ የሚያቀርብ ገለልተኛ አካል ተቋቁሞ ለህዝብ ይፋ ያድርግ፤

ይህ ከየአቅጣጫው ብዣታን ሊያጠሩ የሚችሉ ጉዳዮች እንደሆኑ ከሚነሱት ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው። ቤተክርስቲያን ፖለቲካ ውስጥ መግባቷ የኖረው ባህሏ ቢሆንም፣ አሁን ” በቃ” ሊባልና መንፈሳዊ ተልዕኮዋ ላይ ልታተኩር እንደሚገባ የሚቀበሉ ” የመጽጃ ዘመኗ ሊሆን ይችላልም” እያሉ ነው። ሕዝብ የተቀደሰች ቤተክርስቲያን እንዲኖረው ስለሚፈልግና ስለሚመኝ፣ የቤተክርስቲያኗ ተቆርቋሪና ባለቤት የሆነውን ህዝብ ለማገልገል የዕምነት አባቶች በንስሃ ወደ አምላካቸው ተመልሰው ዕርቅ እንዲያወርዱ ሁሉም ወገን ጫና ሊያደርግ እንደሚገባው በርካቶች ይናገራሉ።

አማራ፣ኦሮሞ ወይም ጋሞጎፋ ወይም ደቡብ ሳይባል የቤተክርስቲያኗ ልጆች ናቸውና በመፈስ አስተሳስሮ መምራት የሚያስችል አቅምን በማጠናከር፣ ፈሪሃ አምላክ ያላቸውን አገልጋዮች በማፍራት፣ ቤተክርስቲያኗ ያላትን ሃብትም በአግባቡ በመጠቀም፣ በተለይም የካድሬ ባህሪ ያላቸውን በማረቅ የማጽዳት ስራ በመስራት ታሪክን፣ ስምንና ሰማያዊ ሃላፊነትን ለመወጣት ጥረት ቢደረግ የሚበጅ እንደሆነ በስፋት እየተገለጸ ነው።

ከዚህ በዘለለ ውዝግብ ተከትሎ ” ግዝት” ተላልፎ “እንነሳ” የሚለው ጥሪ አሳሳቢ ብቻ ሳይሆን አደገኛም ነው። ማን ማን ላይ ነው የሜሳው? ጥሪው ማን ማን እንደሚነሳ፣ ተነስቶ ምን እንደሚያደርግ የለየ አይደለም። ከሁሉም በላይ የትህነግ አማራና አፋርን ሲወር “ህግ ይከበርልን” የሚል ጥሪ ሲቀርብ ኢትዮጵያ ላይ ዓለም እንዲዘምት በገሃድ ጥሪ ያቀረቡ ጳጳስ የሚያቀርቡትን ጥሪ ረጋ ብሎ መመርመር እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ እነዚሁ ወገኖች ይመክራሉ።

ዛሬ ህግ እንዲከበር የሚቀርበው ጥያቄ ” ጥያቄ ማቅረብ አይቻልም” የሚል ነው ወይስ ምን? ህግ ይከበር ብለው ሲያቀርቡ ከላይ ለተነሱት ጉዳዮች መልስ አዘጋጅተው ነው? ወይስ በምን መንፈስ? የተቃውሞ ሰልፍ እንዲጠራ ሲጠየቅ፣ የሚቃወሙ ቢኖሩና ችግር ቢፈጠር ማን ሊጠየቅ ነው? ጳጳሱን ተከትለው በተለይ “አክቲቪስት” ነን የሚሉ “ዕምነትህንና ቤተክርስቲያንህን ጠብቅ” የሚል ክተት እያሰሙ መሆኑ፣ ይህንኑ ክተት በስሜት ሰዎች ማሰራጨታቸው፣ ስጋቱን ከፍ ያደርገዋል።

አንዳንዶች ህዝብ ለክተት ሲጠራና አዋጅ ሲታወጅለት የት የት ለሚገኙትን ቤተክርስቲያናት ይሆን? ይህን ለይተው እንደሆነ ግልጽ ቢያደርጉት ያቀዱትን ደም ማፋሰስ ዕውን ቢያደርግም፣ መጠኑንን ይቀንሰዋል በሚል ከወዲሁ ሃዘናቸውን የሚገልጹ አሉ።


ኦርቶዶክስ ታሪክ፣ ትውፊት፣ የኢትዮጵያ ምሳሌና ሚስጥር ናት። ቢያንስ እንደ ተቋም የየትኛውም ዕምነት ተከታዮች ይንከባከቧታል። ይህ እውነት ዘመን አሻግሯታል። ይህ አንድነቷ አኑሯት፣ አኑሮናል። ስለዚህ አንዱ ተነስቶ ልዩ ተቆርቋሪና ባለቤት ሆኖ ጎራ በመለየት መሸለሉ ውጤቱ ሃዘን ላይ ከሚጥለን በስተቀር አንዳችም መላካም ውጤት አያጎናጽፈንም።
መነጋገርና፣ አምላክን ፈርቶ ሰላም ማውረድ እንጂ ስውር ፋልጎትን ለማሳካት ምዕመኑን ማዥጎርጎር ቢበቃ ደግ ነው። ሰላማዊ ሰልፉም፣ ተቃውሞውም፣ ሁሉም የሰው ልጅ ለካድሬዎች ሲባል እንዳይቀጥፍ ያስፈራል። ካድሬ የሃይማኖት መሪዎችን አምኖ ደረቱን የሚሰጥ አማኝ ከተገኘ ለማለት ነው።

በመጨረሻ

ትህነግ ወረራ ከመጀመሩ በፊት ዘመቻውን በማን ላይ ጀምሮ፣ በማን ላይ አጠንክሮ፣ በማን ላይ አጠንጥኖ እንደነበር ማስታወስ ግድ ነው። ወረራ ሊጀምር ሲል “አሁን ስም የማጥፋቱን ሂደት ጨርሰናል” ብሎ መገምገሙም አይረሳም። ዛሬም ይህ የቤተክርስቲያን ቀውስ ሲነሳ ቀድሞ ስሙ እየተለሸ ያለው ማን ነው? የዚህን ዘመቻ የሚመራው ከየትኛው ወገን ነው? ልክ ጦርነቱ ሲጀመር እንደሆነው ” ሰላማዊ ሰልፍ፣ አመጽ ውጡ” ያለ ማን ነው? ነገ የተሰበሰበ መሳሪያ ዳግም ተሰራጭቶ መበላት እንዳይመጣ መጠንቀቅ ደግ ነው። አብይ አህመድን መጥላት፣ ማውገዝ፣ ከስልጣን ለማስወገድ መረባረብ የመረጡ እንዳሉ ሁሉ፣ በፌስ ቡክ የማይጮሁ ደጋፊዎችም እንዳሉ ማመን አግባብ ነው። የተቃውሞ ሰልፍ እንዲኖር የሚታሰበውን ያህል፣ ጎን ለጎን ሌላው ወገንም ሊሰለፍ እንደሚችል ማሰብ ጠቃሚ ነው። ከሁሉም በላይ ግን ማን እየገፋ ወደ እሳት እንደሚከት መረዳት ጥበብ ነው። የተፈጠረውን ችግር እንደ አምላክ ባህሪዎች አይቶ በሆደ ሰፊነት ለማረም ጊዜ መውሰዱ አሁንም ተመራጭ ይሆናል። ኢትዮጵያ የተሰራችበትን መርዛማ ፖለቲካ ባለመረዳት ክንድን ለማሳየት መጣደፍ ሌላ ጉልበተኞችን እንዳያስነሳ ጥበብ ይቅደም። አስተዋዮች ወደ አደባባይ ወጥታችሁ መላ ፈልጉ። በ”ግፋ በለው” ዘላቂ መፍትሄ ሳይሆን ዘላቂ ቁርሾ ከማበጀት መዳን አይቻልምና!!

እኚህን አባት ስሙዋቸው
https://youtu.be/518JzKiD4iI

Leave a Reply