ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት መፍጠር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ትልቁ ሥራ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲሱ ገዥ ማሞ ምኅረቱ “የተረጋጋ የዋጋ እና የውጭ ምንዛሪ ተመን እንዲሁም ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት መፍጠር” ቅድሚያ የሚሰጣቸው ሥራዎች እንደሚሆኑ ተናገሩ። የብሔራዊው ባንክ ገዥ ባለፉት ስድስት ወራት ምግብ ነክ የዋጋ ንረት ከ38 በመቶ ወደ 32 በመቶ ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል። ምግብ ነክ ባልሆኑ ሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ንረት በአንጻሩ በስድስት ወራት 6 በመቶ ማደጉን አስረድተዋል።

የዋና ንረትን መታገል እና የዋጋ መረጋጋትን መፍጠር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ትልቁ ሥራ እንደሚሆን በትላንትናው ዕለት በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ ከሚገኙ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ገልጸዋል።

አቶ ማሞ ጥር 12 ቀን 2015 “ገንዘብ የማተምና የማሠራጨት፣ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ማስተዳደር፣ የገንዘብ ፖሊሲ የማውጣትና የመተግበር” ኃላፊነት የተሰጠውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በገዥነት እንዲመሩ ከተሾሙ በኋላ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን አንገብጋቢ ጉዳዮች በይፋ ሲያብራሩ የመጀመሪያቸው ነው።

የብሔራዊ ባንክ ገዥነት ሥልጣኑን ከይናገር ደሴ የተረከቡት የ44 ዓመቱ ጎልማሳ ማሞ ምኅረቱ ከሚጠብቋቸው አንገብጋቢ የቤት ሥራዎች መካከል አንዱ የዋጋ ንረትን መቆጣጠር እንደሆነ የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ይስማማሉ።

የተረጋጋ ዋጋ ለዕድገት መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታ መሆኑን የገለጹት የብሔራዊ ባንክ ገዥ “የዋጋ መረጋጋት፤ የውጭ ምንዛሪ መረጋጋት” እንዲሁም የፋይናንስ ሥርዓቱ ጤናማ፣ የተረጋጋ እና ተደራሽ መሆን “የብሔራዊ ባንክ ቁልፍ የትኩረት ጉዳዮች ይሆናሉ” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለውጭ ዕዳ ክፍያ ከፍተኛ ወጪ እንደምታወጣ የገለጹት አቶ ማሞ “የውጭ ዕዳውን ለመቀነስ፤ የውጭ ግኝታችንን ለማሻሻል” እና ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ለማጠናቀቅ ዕቅድ እንዳላቸው አስረድተዋል።

አቶ ማሞ የብሔራዊው ባንክ ገዢን ቢሮ ከመረከባቸው በፊት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነበሩ። ይኸ ግዙፍ ኩባንያ ከመመሥረቱ በፊት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የምጣኔ ሐብት ፖሊሲ አማካሪ እና ዋና የንግድ ተደራዳሪ ሆነው ሰርተዋል።

See also  የምርጫው ውጤትን በማስመልከት፣ እንኳን ደስ አላችሁ!

Leave a Reply