ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመረጃ ኪነ ሙያ ዘርፍ ያሰለጠናቸውን ባለሙያዎች አስመረቀ

በብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሥር የሚገኘው ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመረጃ ኪነሙያ ዘርፍ ያሰለጠናቸውን ባለሙያዎች ዛሬ አስመርቋል፡፡

ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የመረጃ ኪነ ሙያ ሰልጣኞችን ባስመረቀበት መርሃግብር ላይ የተገኙት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ታዜር ገ/እግዚአብሔር፤ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በሪፎርም ስራ ውስጥ የሚገኝ መሆኑን አስታውሰው ሀገርን የሚመጥንና ብሔራዊ ጥቅምናት ደኅንነትን የሚያስክብር የሰው ሃይል በማብቃት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በየትኛውም አካባቢ የሚሰማሩ የመረጃ ሰራተኞች በስራው አለም የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች ሁሉ ተቋቁመው ሀገራቸው ከእነሱ የምትጠብቅባቸውን የሀገር ጥቅምና ደኅንነት የማስከበር አስተዋጽዖ ለመወጣት መዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዘዳንት አቶ ወንደሰን ካሳ ባደረጉት ንግግር፤ የደረስንብት ዘመን በአስገራሚ ፍጥንት መረጃዎች የሚለዋወጡበት ጊዜ በመሆኑ የመረጃ ሁኔታዎችን በመረዳት የደኅንነት ስጋቶችን የሚያስቀር የሰው ኃይል ማብቃት ግድ ይላል ብለዋል።

በመሆኑም የሀገርን ጥቅም የሚያስከብር ከሙስና ራሱን ያፀደና ለማናኛውም ግዳጅ ዝግጁ ሆነ የሰው ኃይል ከማፍራት አንፃር ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ለተቋሙ የውስጥ አቅም ከመገንባት አልፎ፣ ለባለድርሻ አካላት እንዲሁም ለአቻ ተቋማት ብቁ ባለሙያዎችን በየጊዜው በማሰልጠን ላይ እንደሚገኘ ተናግረዋል።

በቅርቡ ከተለያዩ ክልሎችና የፌደራል ተቋማት የተመለመሉ ባለሙያዎችን በመረጃ ኪነሙያ አጫጭር ስልጠና እየሰጠ ማስመረቁን ያስታወሱት ፕሬዘዳንቱ ዪኒቭርሲቲ ኮሌጁ የሚያወጣቸው ተመራቂዎች በመረጃ ኪነ ሙያ የተካኑ፤ ሙስናን የሚፀየፉ የሀገር ፍቅር ያላቸው እና ለህብረተሰብ አገልግሎት የሚተጉ መሆናቸውን ከፀጥታና ደኀንነት ተቋማት እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማት የተገኙ ግብረ መልሶች እንደሚጠቁሙ አስታውቀዋል።

በውጭ መረጃ ስምሪት መስክ አዲስ ሲለበስ አዘጋጅቶ የመረጃ ኪነ ሙያ ሰልጣኞችን ሲያስመርቅ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም በመረጃና ደኅንነት ላይ ያተኮሩ የተለያዩ የስልጠና ፕሮግራሞችን ነድፎ ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን አብራርተዋል።

ተመራቂ ሰልጣኞች በበኩላቸው በቀሰሙት የንድፈ ሀሳብና የተግባር ልምምድ ስልጠና የሀገርና ሕዝባቸውን ደኅንነትና ጥቅም ለመጠበቅ የሚሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በብሔራዊ መረጃና ደኀንነት አገልግሎት ስር የሚገኘው የብሔራዊ መረጃና ደኀንነት ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በአሁኑ ወቅት በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ በርካታ ተማሪዎችን ከተለያዩ ተቀማት ተቀብሎ በመረጃ ኪነ ሙያ እያስተማረ ያለ ብቸኛው የሀገሪቱ የትምህርት ተቋም መሆኑን አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ለኢፕድ በላካው መረጃ አመልክቷል።

Leave a Reply