መከላከያ የማጓጉዝ ስራውን ሲያከናውን

ትህነግ ያስረከባቸውን መሳሪያዎችን መከላከያ ማጓጓዝ ጀመረ፤ ባንኮች በሙሉ አቅማቸው ይሰራሉ

ህወሓት ያስረከባቸውን መሳሪያዎች እና ተሽከርካሪዎችን የማንቀሳቀስ ሥራ መጀመሩን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አስታወቀ፡፡ በፌዴራል መንግሥትና በህወሓት አመራሮች መካከል ደቡብ አፍሪካ እና ኬንያ ላይ በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሠረት÷ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የተረከባቸው የተለያዩ ተሽከርካሪዎችና የጦር መሳሪያዎች ከቦታው መንቀሳቀስ ጀምረዋል።

ጥር 2 ቀን 2015 ዓ.ም ከመቀሌ 36 ኪሎ ሜትር ርቀት ከሚገኘው አጉላ ካምፕ የአፍሪካ ሕብረት ወታደራዊ ታዛቢዎች በተገኙበት÷ ህወሓት ያስረከባቸው መሳሪያዎች፣ ተሽከርካሪዎች እንዲሁም ተተኳሾች ወደ ተዘጋጀላቸው ቦታ በኮንቮይ እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡

በኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የሎጄስቲክስ ዋና መምሪያ ኮሎኔል ነጋ መንገሻ÷ “በተደረሠው ስምምነት መሠረት ወታደራዊ ንብረቶቹን ተረከብን ከቦታው በማንሳት ወደ ተዘጋጀው ቦታ ጉዞ ጀምረናል” ብለዋል፡፡

በቀጠናው የተሰማራው ሰራዊት አመራር ሌተናል ኮሎኔል አለሜ ታደለ በበኩላቸው÷ “ተቋማችን የሰጠንን ትዕዛዝ በሚገባ ተገንዝበን ከህወሓት አመራሮች ጋር በመነጋገር ተሽከርካሪዎችን እና መሳሪያዎችን በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ መሰረት ተረክበን ለመከላከያ ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ አስረክበናል” ብለዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ንብረቶቹን የማጓጓዝ ሥራም ተጀምሯል ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተመሳሳይ ዜና በትግራይ ባንኮች በሙሉ ሃይላቸው እንዲሰሩ የሚፈለገው የገንዘብ መጠንና ሎጅስቲክ እየተንቀሳቀሰ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድም በረራውን በመጨመር አገልግሎት እንዲሰጥ በተሰጠ መመሪያ መሰረት አገልግሎቱ እንደሚሰፋ ታውቋል። በትግራይ ትምህርት ቤቶችና የህክምና ተቋማት፣አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና አምራች ኢንደስትሪዎች ወደ ስራ እንዲገቡ ርብርብ እንደሚደረግም ታውቋል። መሶበ ሲሚንቶ ስራ መጀመሩ ይታወሳል።

See also  የአዋሽ-ወልዲያ-ሀራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክትን ሥራ እንቅስቃሴ መጀመሩን ኮርፖሬሽን አስታወቀ

Leave a Reply