“አየር ጤና ኪዳነምህረት ለምን ደወል እንደተደወለ አላወቅንም”ነዋሪዎች፤ አስተዳደሩ አስጠነቀቀ

“ደወል ሲደወል ሄድን። ምንም አልነበረም። ተመለስን ” ይላሉ በአካባቢ ከነበሩት መካከል። ለምን እንደመጡ ሲጠየቁ ” ቤተክርስቲያኒቱን ሊወሩ የተወገዙት ከኦሮሚያ ይመጣሉ ተብሎ ቀድሞ ተነግሮ ነበር” የሚል ምክንያት ይሰጣሉ።

ተባባሪ ዘጋቢያችን እስፍራው ዘግይቶ ቢደርስም አየር ጤና ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን ውስጥ ለመግባትም ሆነ ለመውጣት የተደረገ ጸብ፣ ግብግብ ወይም አንዳች ንትርክ እንዳልነበረ በስፍራው የነበሩ እንደገለጹለት ጠቁሟል።

ታዲያ ምንም ከሌለ የቤተ ክርስቲያን “የድረሱልን” ጥሪ ደወል ለምን ተደወለ? ለሚለው በግልጽ መልስ የሚሰጥ አካል እስካሁን አልተሰማም። ጉዳዩን ሃላፊነት ወስዶ ምን እንደተከሰተ፣ መቼና እንዴት እንደሆነ፣ ማን ምን አድርጎ ወይም ለማድረግ ሞክሮ “ድረሱልን” እንድተባለ ማስረጃ ወይም አስረጂ አቅርቦ ያስረዳ የለም። ድርጊቱ ግን መልኩን የቀየረ እንደሆነ ገልጾ አስተዳደሩ የማስጠንቀቂያና ማስገንዘቢያ መግለጫ አውጥቷል።

አየር ጤና ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን ደወል መደወሉን ተከትሎ ግን በስፋት በማህበራዊ ገጾች ቅሰቀሳ አዘል ” ተነስ” የሚሉ ጥሪዎች በስፋት ሲሰራጩ ነበር። የኦሮሚያ የጸጥታ ሃይል ያጀባቸው ሃይሎች እየመጡ እንደሆነ ጽፈው ሲበተኑ ታይቷል።

” … አየር ጤና ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን በቁጥር በርካታ ምዕመናን መገኘታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል።ምክንያቱ ደግሞ ደወል በመሰማቱ ነው ተብሏል።ደወሉ የተሰማው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ህገወጥ የተባለው አካል ወደ ስፍራው እየመጣ ነው የሚል በማስተላለፉ እንደሆነ ተሰምቷል።ይሄው ቡድን በኦሮሚያና ደቡብ ክልል የፀጥታ ሀይሎች ታጅቦ ወሊሶ ከተማ መግባቱ ታውቋል” የሚሉ ጽሁፎችም ሲሰራጩና ዜና ሆነው በቴሌግራም ሲበተኑ ነበር

በወቅታዊ ሁኔታ ዙርያ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ

ሰሞኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያጋጠመው ችግር በሰላማዊ መንገድ ፤ በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት ፤በስክነትና የቤተክርስቲያኗን ውስጣዊ አሰራር በተከተለ መንገድ እንደሚፈታ የከተማችን አስተዳደር ፅኑ እምነት አለው፡፡

የከተማ አስተዳደራችን በዚሁ ወቅት ያጋጠመውን ችግር አስመልክቶ በቤተክርስቲያኒቱ የታወጀው የፆምና የምህላ ስርዓት በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቀቅ ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

ሆኖም ግን በከተማችን አዲስ አበባ አዲስ የተሾሙ ጳጳሳትም ሆነ የተሻሩ ጳጳሳት እንደሌሉ እየታወቀ አዲስ የተሾሙ ጳጳሳት ወደቤተክርስቲያን እየመጡ ነው በሚል ሀሰተኛ መረጃ ግጭትና ሁከት ለመቀስቀስ ሙከራ እየተደረገ መሆኑን መረጃዎችና ማስረጃዎቻችን ያሳያሉ፡፡

See also  ለ"እጅ እንስጥ" የስልክ ጥያቄ መከላከያ " ምርጫው የእናንተ ነው" አለ፤ ሽሬ ነዋሪዎችና መከላከያ እየተነታረኩ ነው

ከዚህም በተጨማሪ የእምነት ጉዳይ ያልሆኑ ፖለቲካዊ አንድምታ ያላቸው ድርጊቶችና ንግግሮችም በስፋት በማሰራጨት በቤተክርስቲያኔ መከፋፈልና መለያየት መኖር የለበትም በሚል በቅንነት አማኙ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ወዳልሆነ የትርምስ አቅጣጫ ለመቀየርና ለርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለመጠቀም መሯሯጥ ይስተዋላል፡፡

በተለይም በተለያዩ ፅንፎች የሚገለፁ አደገኛ መልእክቶችን በታተሙ ወረቀቶችን በተለያዩ ቦታዎች በመለጠፍ ለማሰራጨት ጥረት እየተደረገ መሆኑን፤ እንዲሁም ጉዳዩን ቤተክርስቲያን ለአመፅ እንደጠራች በማስመሰል የክፋታቸውን ልክ የሚገልፁ መልእክቶችን በማህበራዊ ሚድያ በማሰራጨት ለዘመናት ተሳስሮና ተሳስቦ የኖረውን ማህበረሰብ ለመለያየትና እርስ በእርሱ ለማጋጨት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡

በዛሬውም እለት በኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ አየር ጤና ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን አዳዲስ የተሾሙ ጳጳሳት እየመጡ ነው ቤተክርስቲያናችንን ሊነጥቁን ነው በሚል፤ ስልክ ተደውሎ ተነግሮናል በሚል ሀሰተኛ መረጃ ውዥንብር በመፍጠርና ሰዎች ወደ ግጭትና ትርምስ ውስጥ እንዲገቡ ሙከራ ተደርጓል፡፡

ይህም ተግባር በተቀናጀና በተናበበ የሚድያ ዘመቻ ከቤተክርስቲያን ደውል መደወል ጀምሮ በተለያዩ የሚድያ አውታሮች ጉዳዩን ለማቀጣጠልና ይህንንም በመላው ከተማይቱ በሌሎችም ደብሮች በተመሳሳይ መንገድ ለመፈፀም እና ህብረተሰቡን ውዥንብር እና ግጭት ውስጥ ለመክተት ዝግጅት መኖሩን መረጃዎች አመላክተዋል፡፡ ከዚያም አልፎ ግጭት ወደ ትምህርት ቤቶችም ለማስፋፋት የተለያዩ ሙከራዎች መኖራቸውም ምልክቶች ታይተዋል፡፡

ስለሆነም አሁናዊ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያጋጠመው አዳዲስ ጳጳሶች ሹመት በአዲስ አበባ ሃገረ ስብከትና ደብሮች ውስጥ ያለመሆኑ እየታወቀ ፤ ሆነ ተብሎ ግጭት ለመፍጠር እና የግጭት አውድማውን አዲስ አበባን ለማድረግ የሚደረጉ ጥሪዎች የተሳሳቱ ፤ አግባብነት የሌላቸው ናቸው፡፡

በመሆኑም የከተማችን ነዋሪዎች በአብሮነትና ጠንካራ ተሳትፎ በዘላቂነት ያስቀጠለውን የከተማችንን ሰላም ዛሬም እንደ ወትሮው ሁሉ ራሱን ከጥፋት ሃይሎች በመነጠልና ለሁከት ጠሪዎች ምላሽ ባለመስጠት ሁሉም ነገር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ በማድረግ የሰላም ባለቤት በመሆን ሃላፊነቱን ይወጣ ዘንድ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

አሁንም ቢሆን የከተማ አስተዳደሩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያጋጠመውን ችግር በቤተክርስቲያቱ የውስጥ አሰራርና ስርዓት ፤በሰከነ መንገድ እንደምትፈታ እምነታችን ጠንካራ ነው፡፡

በዚህ አጋጣሚ የከተማ አስተዳደራችንም ቤተክርስቲያኒቷ ለምታደርገው ሰላማዊ እንቅስቃሴ ሁሉ የተለመደውን ድጋፋችንን አጠናክረን የምንቀጥል መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡

See also  ሁለት ህፃናትን ይዛ የተሰወረችው የቤት ሰራተኛ ከነግብረ-አበሮቿ በቁጥጥር ስር ዋለች

ይህንን በመተላለፍ በሃይማኖት ሽፋን ዘልቆ የቆየውን የከተማዋን ሰላምና ደህንነት ወደ ሁከት አውድማነት ለመቀየር የሚደረገውን ማንኛውንም ጥረት የከተማ አስተዳደሩ ፈፅሞ የማይታገስና የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ያለበትን ሃላፊነት በመወጣት የህግ የበላይነትን እንደሚረጋግጥና በጥፋት ሃይሎች ላይ ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስድ አጥብቀን እናሳውቃለን፡፡

ከሰላም እንጂ ከሁከት የሚያተርፍ የለም!! ካቲት 2/2015 ዓ/ም አዲስ አበባ

“በአየር ጤና ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን የተከሰተ አዲስ ነገር የለም!” የአ/አበባ ፖሊስ

ዛሬ የካቲት 2 ቀን 2015 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ወደ አየር ጤና ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን አዲስ አስተዳዳሪዎች እየመጡ ነው በሚል የተሳሳተ መረጃ የቤተ ክርስቲያኗን ደወል በማሰማት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአካባቢው ማህበረሰብ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃው እንደደረሰው ከፌዴራል ፖሊስ እና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በቦታው ፈጥኖ የደረሰ ሲሆን የቤተ ክርስቲያኗ ደወል ከመደወሉ በስተቀር የተፈጠረ አዲስ ነገር እንደሌለ በማረጋገጥ አካባቢውን እና ህብረተሰቡን የማረጋጋት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ በተሳሳተ መረጃ መጠነ ሰፊ ጉዳቶችን ሊያሥከትሉ የሚችሉ ዱላን ጨምሮ በርካታ ድምፅ አልባ መሳሪዎች ወደ ቦታው ይዞ በመምጣት ከፍተኛ ብጥብጥ ለማስነሳት ሙከራ የተደረገ ቢሆንም የፀጥታ ሃይሉ በሆደ ሰፊነት አልፎታል፡፡

ወቅታዊ ሁኔታን እንደምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በተከታታይ ቀናት በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የታዩ ህገ ወጥ ተግባራትን የፀጥታ ሃይሉ በትዕግስት ማለፉን ያስታወሰው የአዲስ አበባ ፖሊስ፤ ሆን ብሎ የህዝብ እልቂት እንዲፈጠር እና በተሳሳተ መረጃ ህብረተሰቡ ወደ ግጭት እንዲገባ ቅስቀሳ እና ግፊት የሚያደርጉ ግለሰቦችን ዳግመኛ እንደማይታገስ እና የከተማዋን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አሳስቧል፡፡

ህብረተሰቡ በተሳሳተ መረጃ ሰላምና ደህንነትን ከሚያውኩ ግለሰቦች ራሱን እና አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ የፀጥታ ሃይሉ የሚያከናውነውን የማረጋጋት ተግባር በመደገፍ ተባባሪ እንዲሆንም የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡

Leave a Reply