ዐቃቤ ህግ ከባባድ የሙስና ወንጀሎች ላይ ክስ አንደሚመሰረት አስታወቀ፤ ባለሃብቶች አሉበት

የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ ጀነራል ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከመሬት ወረራ ፣ከፍትህና ፀጥታ፣ ከፋይናንስ እንዲሁም ከገቢ ዘርፍ አኳያ በ197 መዝገቦች ላይ ክስ መመስረቱን ሲያስታውቅ፣ከባባድ የሙስና ወንጀሎች ላይ ክስ አንደሚመሰረትም “ዋናው ትኩረቴ” ሲል ተናግሯል። ይፋ ባይደረግም ከፍተኛ ብድር ያለባቸውና በተጭበረበረ የብድር ሰነድ ከፍተኛ ብር የተበደሩ ላይ ማጣራት ሲደረግ እንደነበር የሚያውቁ ጉዳይ ሌባ ባለሃብቶች ላይ ያነጣተረ አነደሆነ ገልጸዋል።

አየር በአየር በንክኪ ከፍተኛ ብድ የወሰዱና የማይከፍሉ፣ የወሰዱትን ብድር የማይከፍሉ ላይ “በወሰዱት ገንዘብ ምን ሰሩ” በሚል ካቀረቡት መርረጃ ጋር በማመሳከር የኢኮኖሚ ደህንነት ያዘጋጀው ምርመራ ተደራጅቶ ክስ ለመመስረት ዝግጅቱ መተናቀቁን ነው ኢትዮ12 የሰማችው።

በሌብነት ላይ ዘመቻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በተደጋጋሚ ይፋ መሆኑንን ተከትሎ ስጋት የገባቸው ክፍሎች እዛና እዚህ እያሉ ታጣቂዎችን በማደረጃትና በገንዘብ በመደገፍ አመጽ ውስጥ መግባታቸውም ሲገለጽ ነበር። ይህ የሌብነት ሰንሰለት አገሪቱ እንዳትረጋጋ ሴራ አምራቾችን እየቀለበ ህዝቡን በማሰላቸት፣ በኢኮኖሚ ሻጥር ኑሮን በማናር መንግስትን ለማላሸቅ እንደሚሰራ የሚደረገውን ክትትል የሚያውቁ እየገለጹ ነው።

አቃቤ ህግ የሚከተለውን ዜና በገጹ ለጥፏል።

በኢ.ፌ.ድ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ ጀነራል ባለፉት 6 ወራት ከባድና ወቅታዊ በሆኑ የሙስና ወንጀሎች ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግና በምርመራ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ከፍትህ ዘርፍ ሙስና፣ ከመሬት ወረራ፣ ከባንኮች ብድር አስተዳደርና ገንዘብ ምዝበራ ጋር በተያያዘ በ197 መዝገቦች ላይ ክስ መመስረቱ የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር ጀነራል የሆኑት አቶ ገብሩ ገበየሁ ገለጹ፡፡

እንደ አቶ ገብሩ ገለጻ ከጉቦ፣ ሀሰተኛ ሰነዶችን ከማዘጋጀትና ከመጠቀም እንዲሁም በአደራ የተረከቡትን የመንግስት ንብረት ለግል ጥቅም ከማዋል ጋር በተያያዘ በተፈጸሙ ወንጀሎች ጭምር ክስ መመስረቱን እና ከ197 መዝገቦች ውስጥም በ28ቱ ላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ማስተላለፉን በ26ቱ መዝገቦች 44 ተከሳሾች ጥፋተኛ መባላቸውን በ2 መዝገቦችም 3 ተከሳሾች በነጻ መሰናበታቸውን ተገልጧል፡፡

የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል የፌደራል መንግስቱን የሙስና ወንጀል ህጎች ተፈፃሚነት በማረጋገጥ፣ ወንጀልን በመከላከል፣ የፍትህ አገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና ፍትሀዊ በማድረግ፣የሕዝብ ዓመኔታን ያተረፈ የፍትህ አገልግሎት በመስጠት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 የተቋቋመው የቀድሞው የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የአሁኑ የኢ.ፌ.ድ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር ዋነኛ የስራ ክፍል ነው ሲሉም የዳይሬክቶሬቱን ተግባር ጠቁመዋል፡፡

See also  "አፍሪካ ኒውክለር ሀይል መገንባት አለባት"

ባለፉት 6 ወራትም ከመሬት ወረራ፣ ከካሳ ክፍያና ከመንግስት ቤት ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች (በተለይም በቦሌ፣ ንፋስ ስልክና ለሚኩራ ክፍለ ከተሞች) በተሰራው የህግ ማስከበር ስራ ከ100 በላይ ተከሳሾችን የያዙ ከ10 በላይ መዝገቦች ምርመራቸው ተጠናቆ ክስ መስርተናል ያሉት ዳይሬክተር ጀነራሉ ሌሎች ከ50 በላይ መዛግብት በምርመራ ሂደት ላይ እንደሚገኙ በመግለጫቸው ላይ አንስተዋል፡፡

ከ14ኛ ዙር የኮንደሚኒየም እጣ አወጣጥ ጋር ተያይዞ በተፈፀሙ የማጭበርበር ወንጀሎች ላይ እንዲሁም የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተም ከመሬትና የመንግስት ቤት አግልግሎት ጋር በተያያዘ እስከ 3.5 ሚሊየን ብር ድረስ ጉቦ ጠይቀው በተቀበሉ የመሬት አስተዳደር ሰራተኞችና ተባባሪዎቻቸው ላይ በከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱን የተናገሩት አቶ ገብሩ፤ የአርሶ አደር እና የአርሶ አደር ልጅ እንደሆኑ በማስመሰል በ23 ካርታ መብት በመፍጠር 7754 ካ.ሜ የሆነ የመንግስት መሬት በህገ-ወጥ መንገድ በሰጡና በወሰዱ የለሚ ኩራ ክ/ከተማ አመራሮች፣ ሠራተኞችና ተጠቃሚዎች በድምሩ 43 ተከሳሾች ላይ ምርመራ ተጠናቆ ክስ መመስረቱንም አክለው ተናግረዋል፡፡

የልማት ተነሺ ሳይሆኑ እንደሆኑ በማስመሰል በህገ-ወጥ መንገድ 11 የኮንደሚኒየም ቤቶችን ወስደዉ በሸጡ የቤቶች አስተዳደር አመራሮች፣ ሠራተኞችና ደላሎች በድምሩ 24 ተከሳሾች ላይ ፤በቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ 02 በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት የይዞታ መጠኑ 1122 ካ.ሜ የሆነውን ስም ለማዞር አገልግሎት ከጠየቁት ግለሰብ ላይ 3.5 ሚሊዮን ብር በመጠየቅ 1.5 ሚሊዮን ብር በተቀበሉ የቂርቆስ ክ/ከተማ መሬት አስተዳደር የመሬት ዝግጅት ባለሙያ እና ግብረአበሮቹ ላይ ምርመራዎቹ ተጠናቀው በሁለቱም ጉዳዮች ላይ ክስ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ እንዲሁም ከቤተመንግስት ግንባታ (በተለምዶ ጫካ ፕሮጀክት እየተባለ የሚጠራ) ልማት ጋር ተያይዞ የልማት ተነሺ በማስመሰል ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ በከፈሉና የካሳዉ ተጠቃሚ በሆኑ ተጠራጣሪዎች ላይ መዝገብ ተከፍቶ ምርመራ እየተደረገ ይገኛል ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ከፍትህና ፀጥታ ዘርፍ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ስልጣን ተገን በማድረግ የባለሀብቶችን እና ድርጅቶቻቸውን የባንክ ሂሳብ አስቀድሞ በማጥናትና መረጃዎችን በመውሰድ በማስፈራራት ከባለሀብቶቹ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ብሮች ገንዘብ እንዲከፍሉ በመጠየቅ የማይከፍሉ ከሆነ ደግሞ የፋይናንስ እንቅስቃሴያቸውን በተመለከተ ምርመራ አድርጎ ጉዳዩን ለፖሊስ የሚያስተላልፍ መሆኑን በመናገር ከባለሀብቶች በርካታ ሚሊዮን ብሮችን በመቀበል ለግል ጥቅማቸው ባዋሉ የፋይናንስ ደህንነት ሰራተኞች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱን እንዲሁም በተያያዙ ጉዳዮች ላይ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ዳይሬክተር ጀነራሉ አውስተዋል፡፡

See also  ዐቢይ አህመድ ለከፍተኛ የመንግስት ሃላፊነት ቦታዎች ሹመቶች ሰጡ

ከፋይናንስ ዘርፍ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተም በህይወት የሌሉና ውጪ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በባንክ ያላቸውን ለረጅም ጊዜ ሳይንቀሳቀስ የቆየ ሂሳብ ደንበኞቹ እንዳሉና እንደቀረቡ በማስመሰል፣ሀሰተኛ ቼኮችን፣ ውክልናዎችን፣ መታወቂያዎችን፣ ሲፒኦዎችን በመጠቀምና የይለፍ ቃል ስርቆት በመፈፀም በተለያዩ ባንኮች ውስጥ የሚገኝ ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ አጭበርብረው በወሰዱ የባንክ ሰራተኞች፣ ግለሰቦችና ተባባሪዎቻቸው ላይ ምርመራ ተጣርቶ አብዛኞቹ ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክሶች መመስረቱን በመግለጫው ላይ ተመላክቷል፡፡

ከገቢ ዘርፍ ጋር ተያይዞ የተሰሩ ስራዎችን በተመለከተም ምንም አይነት የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ሳይኖራቸው ከውጭ ሀገራት የውጭ ሀገር ገንዘብ ይዘው እንደመጡ በማስመሰል ገንዘቡን እያሳወቁ/ዲክላራሽን ሰነድ ላይ በመመዝገብ በሀገር ውስጥ በህገ- ወጥ መንገድ የተገኘን የውጭ ሀገር ገንዘብ ህጋዊ በማድረግ ከ5ሚሊዮን ዶላር በላይ መንግስትን ጥቅም ባሳጡ 39 የጉሙሩክ ኮሚሽን ቦሌ ኤርፖርት ቅ/ፅ/ቤት ሰራተኞችና ግለሰቦች ላይ ላይ ምርመራ ተጠናቆ ተከሳሾችን የመያዝና የክስ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ እንዚህና በርካታ ተግባራት መከናዎናቸውን አቶ ገብሩ ተናግረዋል፡፡

ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ ወንጀሎችን አስመልክቶ ኤልሻዳይ የልማት ተራድኦ ድርጅት እና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በፈፀሙት በሌሎች ተረጂዎች ስም ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የሆነ የእርዳታ እህል፣ ቁሳቁስና ገንዘብ በመውሰድ ለግል ጥቅማቸው ባዋሉ 13 ተከሳሾች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀልና ህገ-ወጥ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ክስ ተመስርቷል ሲሉ ዳይሬክተር ጀነራሉ የገለጹ ሲሆን ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በተፈጸሙ በርካታ ወንጀሎች ላይ ክስ መመስረቱንና በምርመራ ሂደት ላይ ያሉ ጉዳዮችም መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ 6 ወራትም የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል በከባባድ የሙስና ጉዳዮች እና በሌሎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ እንደሚሰራ ተናግረው መግለጫቸውን ቋጭተዋል፡፡

Leave a Reply