ከ997 ሚሊዮን ብር በላይ ከመመዝበሩ በፊት በጥቆማና በክትትል ዳነ

  • የ962 ከፍተኛ አመራሮች መረጃ ለምዝገባ በመለየት ከነዚህ ውስጥ 150 የሚሆኑ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች በዘንድሮ የዲጅታል አሠራር ተመዝግበዋል

የፌዴራል የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ባለፋት ስድስት ወራት ሊመዘበር የነበረ ከ998 ሚሊዮን ብር በላይ የሕዝብ ሀብት ማዳን መቻሉን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ የ2015 በጀት ዓመት የ6 ወራት አፈጻጸምና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫን የተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የኮሚሽኑ ሥራ አመራር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተስፋዬ ሻሜቦ፣ ባለፉት 6 ወራት በአገር አቀፍ ደረጃ የፀረ-ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ውጤታማ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ ኮሚሽኑ በተቋማዊ አቅም ግንባታ፣ የስነ-ምግባርና የሞራል እሴቶች ግንባታ፣ የሙስና ወንጀልንና ብልሹ አሠራርን መከላከል፣ የፀረ-ሙስና ትግሉ አጋዥ የሆኑ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን ገልፀዋል።

ለአብነትም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የሃብት ማሳወቅና ምዝገባ ሥርዓት መዘርጋት፣ የዜጐችን የሥነ-ምግባርና የሞራል እሴቶች ከመገንባት አንፃር የተሠሩ ሥራዎችን አብራርተዋል።

የሙስና መረጃን በመቀበል፣ በማደራጀት በመተንተንና በተገቢው መንገድ መፍትሄ እንዲያገኝ የማድረግ ሥራዎችም እየተሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይ በትልልቅ ግዥና ሽያጭ ላይ የሚስተዋል ሙስናን አስመልክቶ ጥቆማ ሲቀርብ ሂደቱን እንዲቆም በማድረግ ተጠያቂነት እንዲሰፍን የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል።

በዚህ መሠረት በኮሚሽኑ በተሠራ የአስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ በፌዴራልና በክልል በአጠቃላይ ባለፋት ስድስት ወራት ከ997 ሚሊዮን ብር በላይ ሊመዘበር የነበረ ሀብት ማዳን መቻሉን ገልፀዋል።

በበጀት ዓመቱ የመንግሥት ተሿሚዎችና የበላይ አመራሮች ላይ ግልፅነትና ተጠያቅነት እንዲኖር የሃብት ምዝገባ ከማድረግ አንፃር እየተሠሩ ያሉ ስራዎች ላይም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የ962 ከፍተኛ አመራሮች መረጃ ለምዝገባ በመለየት ከነዚህ ውስጥ 150 የሚሆኑ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች በዘንድሮ የዲጅታል አሠራር ስለመመዝገባቸው ተናግረዋል።

በአጠቃላይ በፌዴራል ተቋማት ከሚገኙ ከፍተኛ፣ መካከለኛ አመራሮችና ባለሙያዎች 23 ሺህ 290 የሚሆኑት ሀብታቸውን በዲጅታል አሠራር አስመዝግበዋል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ በፌዴራል 127 እና በክልል ደግሞ 398 ሀብት አስመዝጋቢዎችን የማረጋገጥ ሥራ ስለመከናወኑ ገልፀው፤ በድምሩ 525 ሀብት አስመዝጋቢዎችን የማረጋገጥ ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።

በቀጣይ የሙስና ሥጋት ጥናትን አጠናክሮ በማስቀጠል በጅምር ላይ የሚገኙ ጥናቶችን ማጠናቀቅና የሚሰጡ ምክረ ሃሳቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል።

See also  የ20/80ና 40/60 የቤት እድለኞች ከጥር አንድ ጀምሮ ውል መዋዋል ይጀምራሉ

በሙስና መከላከል የተሠሩ ሥራዎችን እና መረጃዎችን በማደራጀትና ለሕዝብና ለመንግስት ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘዴዎችን በመጠቀም የወጣቶችና ሕፃናትን እንዲሁም የዜጎችን ሥነ-ምግባር ለመገንባት የሚያግዙ ፕሮግራሞችን ተደራሽ እንደሚደረግም ጠቁመዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply