Site icon ETHIOREVIEW

የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ለዩኒቨርስቲ መውጫ ፈተና ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ የትምህርት ሚኒስቴር አሳሰበ

በመጪው ሀምሌ ወር ለሚሰጠው የዩኒቨርስቲ መውጫ ፈተና የፈተና ንድፈ ማሳያ / Blueprint / እና የፈተና ዝግጅት ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በመውጫ ፈተና ዙሪያ ከተማሪዎች ህብረት ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱም የመውጫ ፈተና በመጪው ሀምሌ ወር በኦንላይን ለሁሉም የመንግስትና የግል ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንደሚሰጥ ገልፀዋል።

ለሚሰጠው የመውጫ ፈተና ብቁ ለመሆንም ተማሪዎች በየዩኒቨርስቲዎቹ የሚሰጠውን የመጨረሻውን መንፈቅ ዓመት ፈተና መውሰድና የሚሰጡ ትምህርቶችን ማጠናቀቅ እንደሚገባም ሚኒስትር ዴኤታው አስገንዝበዋል፡፡

ለፈተናው በሁሉም የትምህርት መስኮች ላይ የተመረጡ የትምህርት ዓይነቶች የብቃት ልየታ ተደርጎላቸው ዩኒቨርስቲዎች እንዲያውቁት መደረጉን የጠቆሙት ዶክተር ሳሙኤል፣ በአሁኑ ወቅትም የፈተና ንድፈ ማሳያና / Blueprint / የፈተና ዝግጅት ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም ተማሪዎች በቀሪዎቹ አምስት ወራት ተገቢውን ዝግጅት በማድረግ ራሳቸውን ለፈተናው ብቁ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙ የተማሪዎች ህብረት ተወካዮችም ወደ ዩኒቨርስቲዎቻቸው ሲመለሱ ተማሪዎች ለፈተናው በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡

በውይይቱም ከሁሉም ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንቶች መገኘታቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

Via OBN

Exit mobile version