Site icon ETHIOREVIEW

የሃረሪና ክልልና ድሬደዋ አስተዳደር ሃይማኖትን ተገን ያደረገ አፍራሽ እንቅስቃሴ አወገዙ

ሐረር በአለም አቀፍ ደረጃ በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ ትምህርት እና ባህል ድርጅት (ዩኒስኮ) እ.ኤ.አ በ2003/4 በሰላም ፣ በትብብር እና የአብሮነት ከተማነት አለም አቀፍ ሽልማት እና እውቅናን አግኝታለች፡፡

ይህም የተለያዩ እምነት ያላቸው ህዝቦች ለዘመናት በሰላም፣ በአብሮነት፣ በመቻቻል በጋራ የኖሩባት እና ዛሬም የሚኖሩባት ከተማ በመሆኗ የተቀዳጀችው ክብር እና እውቅና ነው፡፡

ሰሞኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያጋጠመው ችግር በሰላማዊ መንገድ፤ በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት፤ በስክነትና  የቤተክርስቲያኗን ውስጣዊ አሰራር በተከተለ መንገድ እንደሚፈታ የክልሉ መንግስት ፅኑ እምነት አለው፡፡

ችግሩ ከተፈጠረበት ግዜ ጀምሮ በክልላችን በሐይማኖት ተቋማትና በህዝብ ደህንነት ላይ ችግር እንዳይፈጠር ፍጹም ፍትሃዊ እና ገለልተኛ በመሆነ መልኩ ስንሰራ ቆይተናል።

ሆኖም ግን በሀገራችን በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች መካከል የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ ፍጹም ምእመናዊ በሆነ መልኩ የሚንቀሳቀሱ ምእመናኖች እንዳሉ ሆኖ ስውር የፖለቲካ ዓላማቸውን በሃይማኖት ሽፋን ለማስፈጸም የሚሞክሩ ኃይሎች እንዳሉ ይስተዋላል።

በኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረው ችግር ከሃይማኖት ጉዳይነት አልፎ እየተወሳሰበና በርካታ እኩይ ዓላማ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሚዲያዎችና የሽብር ሀይሎች ተቀናጅተው ሀገር ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

ይህንን ተከትሎ በሁለቱም ወገን የካቲት 5 ቀን የተጠራው ሰልፍ ለክልሉ ሰላምና በህዝብ ደህንነት ላይ ችግር የሚፈጥር በመሆኑ በመንግስት ያልተፈቀደ እንደሆነ እየገለጸን መንግስት ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ህገመንግስታዊ ተግባርና ኃለፊነቱን ለመወጣት በሚያደርገው እንቅሳቃሴ ሁሉ መላው የክልሉ ሕዝብ አሰፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደረ‍ደርግ የክልሉ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።

የሀረሪ ክልላዊ መንግስት የካቲት 3 ቀን 2015 ዓ.ም ሀረር

ከድሬዳዋ አስተዳደር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ

ኦቢኤን የካቲት 04/2015 – የድሬዳዋ አስተዳደር ሁሉም ኃይማኖቶች በሠላም፣ በፍቅር፣ በመከባበር እና በአብሮነት በጋራ የሚኖሩበት መሆኑ ይታወቃል፡፡

ሰሞኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያጋጠመው አለመግባባት በከፍተኛ ኃላፊነት ስሜት የቤተ-ክርስቲያኗን ውስጣዊ አሰራር በተከተለ ሠላማዊ መንገድ እንደሚፈታ የድሬዳዋ አስተዳደር የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል፤ እያበረከተም ይገኛል፡፡

በተጨማሪ የእምነት ተቋማት መጠናከር ለአስተዳደራችንም ሆነ ለሀገር አንድነትና እድገት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በማመን በቤተ-ክርስቲያኒቱ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በከተማችን የተከሄደውን መንፈሳዊ ጉባኤ እንዲሁም የታወጀው የፆምና ምህላ ሥርዓት በሠላም ተጀምሮ ያለአንዳች ችግር እንዲጠናቀቀቅ ያላሰለሰ ጥረት አድርጓል፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ የተፈጠረውን ችግር ሀሰተኛ መረጃና ውዥንብር በመፍጠርና ህዝቡን ወደ አላስፈላጊ ግጭትና ትርምስ ውስጥ እንዲገባ የተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ፅንፈኛ የፖለቲካ ኃሎች ተቀናጅተው ኢትዮጵያን በማዳከም ለማፍረስ አደገኛ መልእክቶችን በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ፡፡

በመሆኑም የአስተዳደራችን ነዋሪ የሀገሪቱ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል የዜጎችን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ያስተላለፈውን ውሳኔ በማስፈጸም ነዋሪው በአብሮነትና በጠንካራ ተሳትፎ በዘላቂነት ያስቀጠለውን የአስተዳደራችንን ሠላም ዛሬም እንደ ወትሮው ሁሉ ራሱን ከጥፋት ኃይሎች በማራቅ በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ የሠላም ባለቤት በመሆን ኃላፊነቱን ይወጣ ዘንድ የድሬዳዋ አስተዳደር ጥሪ ያቀርባል፡፡

በመጨረሻም በሁለቱም ወገኖች የካቲተ 5 ቀን የተጠራው ሠላማዊ ሰልፍ በአስተዳደሩ ሠላምና በህዝብ ደህንነት ላይ ችግር የሚፈጥር ስለሆነ በአስተዳደሩ ያልተፈቀደ መሆኑ ታውቆ የህግ የበላይነትን እንደሚረጋግጥ አጥብቀን እያሳወቅን የአስተዳደራችን ነዋሪ በተለይ ወጣቱ አንደ ወትሮው ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርግ የድሬዳዋ አስተዳደር ጥሪ ያቀርዳል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር

Exit mobile version