ዜና አፍሪካ ህብረት – አውሮፓ ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና እውን መሆን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገለጹ፤

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት አምባሳደሮች ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና እውን መሆን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገለጹ። በአዲስ አበባ በተጀመረው 42ኛው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ ላይ የተገኙ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት አምባሳደሮችን የአፍሪካን ነፃ የንግድ ቀጣናን በማስመልከት ለኢዜአ ተናግረዋል።

አምባሳደሮቹ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ለአህጉሪቱ የምጣኔ ሃብት እድገት፣ ለልማት፣ እድገትና ብልጽግና የጎላ ጠቀሜታ አለው ብለዋል። በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ሐንስ ሄንሪክ፤ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ከስዊድን የቀጣናዊ ትስስር ጋር አብሮ የሚሄድ በመሆኑ ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።

አፍሪካ በምጣኔ ሃብት እድገት፣ በንግድና በምርት ያላት አቅም ትልቅ መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደሩ ነጻ የንግድ ቀጣናው ይህን በማጠናከር ፋይዳው የጎላ ይሆናልም ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ኪራ ስሚዝ፤ የአፍሪካ ተቋማትን መደገፍና ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው በአህጉሩ የንግድ ውህደትን በመፍጠር ለእድገት አስተዋጽኦ ያለውን አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል። የንግድ ቀጣና ስምምነቱ የታለመለትን አላማ እንዲያሳካ ዴንማርክ በአፍሪካ ህብረት በኩል ድጋፍ እንደምታደርግም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን አዎር፤ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት በንግድ ትስስር ያስመዘገቡትን ውጤት በማስታወስ አፍሪካም በነጻ የንግድ ቀጣና ትስስሩ ያስቀመጠውን ግብ እንደሚያሳካ እምነታቸውን ገልጸዋል። የንግድ ትስስሩ አውን መሆን የምጣኔ ሃብት፣ ፖለቲካና ማህበራዊ ትስስርን የሚያጠናከር መሆኑንም ተናግረዋል።

የአፍረካ ነጻ የንግድ ቀጣናን ለመፍጠር የተጀመረውን ጥረት ለማካካት የመሰረተ ልማትና ክህሎትን ማዳበርና አሰራሮችን ማበጀት ይገባልም ብለዋል። የዘንድሮው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ “የአፍሪካን ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራ ማፋጠን” በሚል መሪ ሀሳብ የፊታችን ቅዳሜና እሑድ ይካሄዳል።

የአፍሪካ ድምፅ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ጎልቶ እንዲሰማ የአውሮፓ ሕብረትና የስፔን ፅኑ ፍላጎት ነው – ጆሴ ማኑኤል አልባሬስ ቡይኖ

አዲስ አበባ የካቲት 8/2015(ኢዜአ)፦የአፍሪካ ድምፅ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ጎልቶ እንዲሰማ የአውሮፓ ሕብረትና የስፔን ፅኑ ፍላጎት መሆኑን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆሴ ማኑኤል አልባሬስ ቡይኖ ገለጹ።

See also  50 ሀገራት በሱዳን ያሉ ዜጎቻቸውን በኢትዮጵያ በኩል እንዲወጡ ይፋዊ ጥያቄ አቀረቡ

በ42ኛው የአፍረካ ሕብረት የስራ አስፈፃሚዎች ስብሰባ ንግግር ያደረጉት የስፔን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ የአውሮፓ ሕብረት አባል የሆነችው ስፔን ከአፍሪካ ጋር መልክዓ ምድራዊ ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት እንዳላት ጠቅሰዋል።

ዓለም እየተጋፈጠች ያለችውን ሉላዊ ፈተናዎች በድል ለመወጣት በጋራ መስራት አስገዳጅ መሆኑን ገልፀው፣ ስፔንና አውሮፓ ህብረት ትብብራቸውን ያጠናክራሉ ብለዋል።

ስፔን የአትላንቲክ ውቅያኖስ እና የሜዲትራኒያን ባህር አዋሳኝ አገር በመሆኗ አህጉር አቀፍ ንግድ እንዲሳለጥ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ትስስር እንደምታጠናክር ገልፀዋል።

አፍሪካና ስፔን የጋራ ታሪክና የወደፊት ዓላማ እንዳላቸው የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣናን ጨምሮ አህጉራዊ ትስስር እንዲጠናከር ጽኑ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ስፔን የጋራ ተጠቃሚነት ላይ በተመሰረተ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ መሰረት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል። የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካ የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲመሩ እና የ2063 የልማት አጀንዳዎች እንዲሳኩ ከአፍሪካ ጎን ትቆማለች ነው ያሉት። በሌላ በኩል የአፍሪካ አገራት ነፃነትና ጥቅማቸው እንዲረጋገጥ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ የአፍሪካ ድምፅ ተሰሚነት እንዲያገኝ እንደምትደግፍም ገልፀዋል።

በአጠቃላይ በአፍሪካ ኢንቨስትመንት፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በምግብ ዋስትና እና ሁሉን አቀፍ ትብብር ማረጋገጥ ላይ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገልፀዋል።

የአፍሪካ ስራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ እና የሴኔጋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሳታ ቶል ሳል በበኩላቸው አፍሪካ በመከባበርና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነቷን እያጠያከረች መሆኑን ገልፀዋል።

በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት የእርስ በርስ ንግድ ግብይትን በማሳለጥ ለአህጉሪቱ ለማምረቻው ዘርፍ ዕድገትና ለመሰረት ልማት መስፋፋት ትልቅ ዕድል መሆኑን አብራርተው ለተግባራዊነቱም በትብብር መስራት ይጠይቃል ብለዋል።።

በአፍሪካ ኅብረት ሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ የኅብረቱ የተለያዩ ተቋማትና አደረጃጀቶች ምርጫ ይጠበቃል

በአፍሪካ ኅብረት ሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ የኅብረቱ የተለያዩ ተቋማትና አደረጃጀቶች ምርጫ ይጠበቃል ። 42ኛው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ዛሬ በኅብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ተጀምሯል። በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ የኅብረቱ አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ተወካዮች ይሳተፋሉ።

See also  ኦሮሚያ በወረዳዎች፣ከተሞችና ዞኖች ስር ነቀል ለውጥ አደረገ

በስብሰባው ላይ እየተሳተፉ ከሚገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መካከል የሶማሊያ፣ ናይጄሪያ፣ ኮሞሮስ፣ ታንዛንያ፣ ኢስዋቲኒ፣ ሴራሊዮን፣ ኮትዲቭዋር፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ዚምባቡዌና ማሊ ይገኙበታል።

የምክር ቤቱ ስብሰባ የአፍሪካ ኅብረት ቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ በጥር ወር 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ባደረገው 45ኛ መደበኛ ስብሰባ የተወያየባቸው አጀንዳዎች ላይ ይወያያል።

ከውይይቱ በተጨማሪ በምክር ቤቱ ስብሰባ ከፍተኛ ትኩረት ከሚያገኙ ጉዳዮች መካከል በአፍሪካ ኅብረት ሥር የሚገኙ የተለያዩ ተቋማትና አደረጃጀቶች የሚካሄዱ ምርጫዎች መሆናቸውን ኅብረቱ ገልጿል።

ምክር ቤቱ የአፍሪካ ሰብአዊና የሕዝቦች መብቶች ፍርድ ቤት ሁለት ዳኞች፣ የአፍሪካ ኅብረት የፀረ-ሙስና አማካሪ ቦርድ ስድስት አባላትና ለአፍሪካ ኅብረት የአስተዳደር ጉዳዮች ችሎት ሦስት ዳኞችን ይመርጣል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ኅብረት የውጭ ኦዲተሮች ቦርድ ለሁለት ዓመት የሚያገለግል የአንድ አባል ምርጫ እንደሚያከናውን ኅብረቱ ገልጿል።

42ኛው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት እስከ ነገ ይቆያል።

Leave a Reply