አፍሪካ የፓን አፍሪካኒዝምን የወጣት መሪዎች ጉባኤ እንዲኖራት ኢትዮጵያ አሳብ አቀረበች፤ የፓን አፍሪካኒዝም ፎረምን ሊያካሂድ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 8/2015 የአፍሪካ ኅብረት ፓን አፍሪካኒዝምን ማጠናከር የሚያስችል የወጣት መሪዎች ጉባኤ ሊኖረው ይገባል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ። የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የፓን አፍሪካኒዝም ፎረምን ሊያካሂድ እንደሆነ ተገለጸ።

ኢትዮጵያ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በነበረችበት አጋጣሚ በብዙ መድረኮች ከጎኗ በመቆም አጋርነታቸውን ላሳዩ አፍሪካዊያንም ምስጋና አቅርበዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፤ ዛሬ በተጀመረው 42ኛው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ ላይ በመገኘት ንግግር አድርገዋል።

በንግግራቸውም የአፍሪካ አገራትና የአፍሪካ ኅብረት እንዲሁም አጋር አካላት በኢትዮጵያ በዘላቂነት ግጭት ለማቆም ለተደረሰው ሥምምነት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በተለይም ደግሞ አንዳንድ አካላት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ሲያሳድሩ በባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ ጭምር አፍሪካዊያን ከኢትዮጵያ ጋር በመሰለፍ አጋርነታቸውን ማሳየታቸውን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ ባሳለፈቻቸው የፈተና ጊዜያት ከአፍሪካ ኅብረትና ከአፍሪካዊያን ያገኘነው ድጋፍ አኩርቶናል፤ በአፍሪካ ላይ ያለንን እምነትም እጅጉን አጠናክሮታል ብለዋል።

በተለይም ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋቂ ማኅማት፣ ለቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ እንዲሁም ለቀድሞ ኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ምስጋና አቅርበዋል።

በመንግሥትና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የሠላም ሥምምነት “ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ መስጠት የሚለውን የኅብረቱ ቁልፍ መርህ ገቢራዊ በማድረግ ትልቅ ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የሠላም ሥምምነቱ አሁን ላይ በተለያዩ የትግበራ ደረጃ ላይ መሆኑን ጠቁመው የሰብዓዊ ድጋፍ በማቅረብ በግጭቱ የተቋረጡ አገልግሎቶችን መልሶ በማስጀመር አመርቂ ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቅሰዋል።

ጎን ለጎንም ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በመሆን የሠላም ሂደቱ የአፈጻጸም ትግበራ በመልካም ደረጃ ላይ መሆኑን ገልጸው በተለይም ትጥቅ በመፍታትና ወደ ማኅበረሰቡ በመቀላቀል አበረታች ውጤት እየተገኘ ነው ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ተቋም ጋር በጋራ ያደረጉትን ጥናት ተከትሎ ያቀረቡትን ምክረ-ሃሳብ በመቀበል እየተገበረች ነው ብለዋል።

በተለይም ደግሞ ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚኒስትሮች የጋራ ግብረ-ሃይል በማቋቋም እየሰራች መሆኑን ገልጸው እንዲያም ሆኖ የተ.መ.ድ የሰብዓዊ ተቋም ይህንን የኢትዮጵያ ጥረት ወደ ጎን ማለቱ ተቀባይነት እንደሌለው ነው ያስረዱት።

See also  የኢትዮጵያን ችግር በውጪ ጣልቃ ገብነት መፍታት እንደማይቻል የአሜሪካ የቀድሞ አምባሳደሮች አሳሰቡ

የአፍሪካ የሰብዓዊና የሰዎች መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማጣራት የተናጠል ቡድን ማቋቋሙ ኢትዮጵያ የተመድ አቻ ተቋም ጋር በመሆን የምታካሂደውን ጥረት የሚያቃልል ነውም ብለዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን በጋራ ጥናት ይካሄድ የሚለውን የኢትዮጵያን ጥያቄ ውድቅ ያደረገ መሆኑን ጠቁመው በሠላም ሥምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ በሽግግር ፍትህ ላይ ብሔራዊ ምክክር እያደረገች ያለውን ጥረትም ያላገናዘበ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም አፍሪካዊያን አስካሁን የሚያደርጉትን አጋርነት አሁንም በድጋሚ እንዲያሳዩ ጠይቀዋል።

ያለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ቁም ነገሮችን ተምረናል ያሉት አቶ ደመቀ ሰላም ለማረጋገጥ ውስጣዊ ጉዳዮችን በራስ መምራትና በወጣቶች የፓን አፍሪካኒዝም ጽንሰ ሃሳብ ማስረጽ ያስፈልጋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ፓን አፍሪካኒዝም ለአፍሪካ አንድነትና ምጣኔ ሃብታዊ አድገት ወሳኝ ነው ብላ ታምናለች ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፤ በተለይም በአፍሪካ የጥይት ድምጽ እንዳይሰማ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት አፍሪካዊያን በባለቤትነት መምራት አለባቸው ብለዋል።

በተለይም የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና የደህነነት የፖለሲ ማዕቀፎችን በአግባቡ በመጠቀም በአህጉሪቱ የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮች ዘላቂ እልባት መስጠት ይገባል ብለዋል።

ይህንን ከግምት በማስገባት ኢትዮጵያ ባሳለፍነው የፈረንጆች ዓመት ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ወጣቶች በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤዎች ላይ እንዲመክሩ ማድረጓን ገልጸዋል።

በመሆኑም የአፍሪካ ኅብረት በአህጉሪቱ ፓን አፍሪከኒዝምን ለማጠናከር የሚያስችል ዓመታዊ የወጣት መሪዎች ጉባኤ ማስተናገድ አለባት በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። ይህም የወደፊት የአፍሪካ ኅብረት ሥራዎችን ከወጣቶች ጋር ለማሰናሰልና የፓን አፍሪካኒዝም መርሆዎችን ለማስቀጠል ያስችላል ብለዋል። ወጣቶች የሚሰሯቸው ሥራዎች በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር እንዲካሄድና የአፍሪካ አንድነት እንዲሁም ምጣኔ ሃብታዊ አድገት እንዲኖር ያስችላል ነው ያሉት።

የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የፓን አፍሪካኒዝም ፎረምን ሊያካሂድ ነው

የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የመጀመሪያ የሆነውን የፓን አፍሪካኒዝም ፎረም ሊያካሂድ ነው። የተቋሙ ርዕሰ አካዳሚ ዶክተር ምህረት ደበበ እና ምክትሎቻቸው ይህንኑ ሁነት በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸውም የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የመጀመሪያ የሆነውን ፎረም የፊታችን እሁድ ለማካሄድ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

See also  ከ30 በላይ ኤምባሲዎች እንደሚዘጉ ፍንጭ ተሰጠ

የፎረሙ ዋነኛ ዓላማ የፓን አፍሪካኒዝምን ንቅናቄ ዳግም ለማነቃቃት ያለመ መሆኑ የገለጹት ዶክተር ምህረት ዘመናዊ የቀኝ አገዛዝ እሳቤን መታገልና የአፍሪካን ሁለንተናዊ ለውጥ ለማሳካት ያግዛል ብለዋል። በፎረሙ የአረንጓዴ አሻራ ልምድና ተሞክሮ የሚቀርብ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአሕጉሪቷ ሕዝቦች የእውቀት ማእከል ለመሆን እየሰራ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ምህረት የአሁኑ ፎረም መዘጋጀትም የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል። በፎረም ላይ በርካታ የአፍሪካ አገራት መሪዎች፣ የአህጉሪቱ ምሁራንን ጨምሮ ከ300 በላይ ተሳታፊዎች እንደሚኖሩ ይጠበቃል። የፓን አፍሪካኒዝም ፎረምን ከአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን በየዓመቱ የማካሄድ ዕቅድ እንዳለም ታውቋል።

ዜናው የኢዜአ ነው

Leave a Reply