የምስራቅ አፍሪቃ የጦር መኮንኖች አዲስ አበባ መከሩ፤ኢትዮጵያና ኡጋንዳ ስምምነታቸውን ለማጠናከር ወሰኑ

ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ ሠላምና መረጋጋት የምታደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክራ እንደምትቀጥል የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ተናገሩ። በአዲስ አበባ ላለፉት አምስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 31ኛው የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ዛሬ በተካሄደው የመከላከያና ጸጥታ ሚኒስትሮች ኮሚቴ ስብሰባ ተጠናቋል።

ዶክተር አብርሃም በላይ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የጸጥታ ሁኔታዎች በፍጥነት በሚቀያየርበት ምስራቅ አፍሪካ አካባቢ የተጠናከረ የጋራ ሃይል ያስፈልጋል። በቀጣናው የሚፈጠሩ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት፣ የጋራ አቅም ለመፍጠር፣ ተቋሙን ማጠናከርና መሰል ጉዳዮች ላይ የመከላከያና ጸጥታ ሚኒስትሮች ኮሚቴ ውይይት ማድረጉን አብራርተዋል።

ጠንካራ የተጠባባቂ ኃይል ተቋምን ለመፍጠር እስካሁን አባል ያልሆኑ አገራት አባል በሚሆኑባቸው ሁኔታዎች ላይም መመከሩን ጠቁመዋል። “የምስራቅ አፍሪካ ችግሮች መፈታት ያለባቸው በራሳችን ነው” ያሉት ዶክተር አብርሃም የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይልን በማጠናከር የሚፈጠሩ ችግሮችን በጋራ መፍታት እንደሚቻል ነው ያብራሩት።

ለዚህም ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ስታደርግ የነበረውን አስተዋጽኦ አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል። የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ጌታቸው ሽፈራው በበኩላቸው ስብሰባው ተቋሙን የበለጠ የሚያጠናክሩ ጠቃሚ ሃሳቦች እንደተነሱበት ገልጸዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል የተሟላ ግዳጅ ለመፈጸም የሚያስችል ቁመናን መገንባት መቻሉን ገልጸዋል። ጎን ለጎንም አባል አገራቱ በቀጣይ የፋይናንስ ድጋፋቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የ2022 ተጠባባቂ ኃይሉን በሊቀ-መንበርነት በመራችበት ወቅት ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወኗን አንስተዋል። ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ሊቀ-መንበርነቷን ለኬንያ አስረክባለች። የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ከተመሰረተ 20 ዓመታትን አስቆጥሯል።

በሌላ የትብብር ዜና ኢትዮጵያና ኡጋንዳ በመከላከያ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ የአገራቱ የመከላከያ ሚኒስትሮች ገለጹ። የሁለቱ አገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች በአዲስ አበባ በተካሄደው 31ኛው የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የመከላከያና ጸጥታ ሚኒስትሮች ኮሚቴ ስብሰባ ጎን ለጎን ከመከሩ በሁዋላ ነው አብረው ለመስራትና ግንኙነታቸውን ለማደስ መወሰናቸውን ያገለጹት።

በውይይታቸው ሁለቱ አገሮች በሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ ትብብራቸውን በማጠናከር በሁለትዮሽ እንዲሁም በቀጣናው መሥራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ መምክረዋል።

See also  የአሜሪካ መንግስት የጣለው የቪዛ ክልከላ የዓለም አቀፍን ህግ የጣሰ መሆኑን ምሁራን ገለጹ

የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ከውይይቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ ከኡጋንዳ ጋር በመከላከያ ዘርፍ በትብብር የሚሰሩበት ሥምምነት አለ ብለዋል። ሁለቱ አገራት ያደረጉትን ሥምምነት የበለጠ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መግባባታቸውን ገልጸዋል። አጠቃላይ ወታደራዊ ትብብርን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።

የኡጋንዳ መከላከያ ጉዳዮች ሚኒስትር ቪሲንቲ ሴቢቻ በበኩላቸው ኡጋንዳ በሰላምና ጸጥታ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር የበለጠ ማጠናከር ትፈልጋለች። ሁለቱ አገራት ቀደም ሲል የነበራቸውን የመከላከያ ሥምምነት ትብብር ማየትና መከለስ የውይይታቸው አንደኛው ጉዳይ እንደነበር ጠቁመዋል።

Leave a Reply