የዓድዋን ድል “በተከፈለው ዋጋ ልክ እየተከበረ ነው ብለን አናምንም”

የዓድዋን ድል በአል የድሉን ታላቅነት በሚመጥን መልኩ ለማክበር ዝግጅት መጀመሩን የተቋቋመው ኮሚቴ አሥታወቀ።

ኮሚቴው የተቋቋመው ከመከላከያ ሚኒስቴር ከባህል እና ስፖርት ሚንስቴር እንዲሁም ለበአሉ በድምቀት መከበር አስተዋፅኦ ያበረክታሉ ተብለው እምነት ከተጣለባቸው አካላት ነው።

በመሆኑም በአሉን በተደራጀ እና በተቀናጀ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅቱን ለማሠናዳት ታሳቢ ተደርጎ የተቋቋመው ኮሚቴ በዛሬው እለት በመከላከያ ዋና መሥሪያ ቤት መግለጫ ሰጥቷል።

የባህል እና ስፖርት ሚንስትሩ አቶ ቀጀላ መርዳሳ የአድዋ ድል በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ በጣሊያን ቅኝ ገዥዎች እና ለነፃነት በታገሉት የኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል በአድዋ ተራራ እና አካባቢው በተደረገ ጦርነት ከየአቅጣጫው የመጡ የኢትዮጵያ ህዝቦች ጠላትን ድባቅ በመምታት አንፀባራቂ ድል የተጎናፀፋበት እና የአፍሪካዊያንን የትግል ታሪክ የቀየረ ታላቅ በዓል ነው ብለዋል።

የአድዋ ድል በቀላሉ የተገኘ ሳይሆን በርካታ የኢትዮጵያ ጀግኖች የህይወት መስዋዕትነት ከፍለው ለእኛ ለልጆቻቸው የሰጡን ዘመን ተሻጋሪ ታሪካችን ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ይሁን እንጅ ይኸው ታላቅ በዓል እስካሁን ድረስ ትኩረት ተሰጥቶት በተከፈለው ዋጋ ልክ እየተከበረ ነው ብለን አናምንም ዘማች አሰልፈው በጀግንነት መርተው በጦርነቱ ላይ የወደቁ ጀግኖች አልተዘመረላቸውም አልተነገረላቸውም ነው ያሉት።

የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በበኩላቸው የአድዋ ድል እንደማንኛውም የአውደ ውጊያ ድሎች በውጊያ የተገኘ ብቻ ሳይሆን ዘመንም ወንዝም ተሻጋሪ ሚስጢረ ብዙ ድል ነው ፤መገፋትን የሚጠሉ እና ነፃነትን አብዝተው የሚሹ አባቶቻችን የአካል እና የህይወት መስዋዕትነት ከፍለው ለእኛ ለልጆቻቸው በክብር ያስረኩብን ታላቅ ታሪክ ነው ብለዋል።

በአሉ በተመዘገበው ድል ልክ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከበረ ባለመሆኑ የድሉን ታላቅነት እና ሀያልነት አጉልቶ በሚያሳይ መልኩ ለማክበር ኮሚቴ ተዋቅሮ ሥራ መጀመሩንም አስታውቀዋል።

በበአሉ ዕለት 21 ጊዜ መድፍ እንደሚተኮስ፣ ጀግና አርበኞቻችንን ለማስተወስ ከጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር ጋር በጋራ በመሆን በዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ አደባባይ የአበባ ጉንጉን እንደሚቀመጥ፣ በዘመን መካከል እየተፈተነች ፈተናውን አልፋ በፅናት የቆመችውን ኢትዮጵያ በክብር የተረከበው የኢፊዴሪ መከላከያ ሰራዊት እግረኛ ጦር ወደ አድዋ ሲሄዱ ጀግና አባቶቻችን የተሻገሩትን የአድዋ ድልድይ ወትሮ ዝግጁነቱን በአሟላ ሞራል ሲሻገር የሚያሳይ በመጨረሻም የበአሉ ፍፃሜ በመስቀል አደባባይ እንደሚሆን ኮሎኔል ጌትነት ተናግረዋል።

See also  በኤሌክትሪክ የብረት ማማዎች ላይ በተፈጸመ ስርቆት የ100 ሚሊዮን ብር ኪሳራ

የአድዋ ድል በአል የግለሰብ ሳይሆን የህዝብ እና የሀገር በመሆኑ የተወሰኑ ቡድኖች እና ግለሰቦች የፖለቲካ ማስፈፀሚያ ሊሆን አይገባም። ከአላማው ውጭ በአላስፈላጊ ፍላጎቶች እንዳይጠለፍ በተደራጀ እና በተማከለ ደረጃ ይመራል፣ የአንድነታችን ፈተናዎች እና ስጋቶች አንዱ ማስወገጃ መንገድ አድርገን እንጠቀምበታለን እንጅ ማባባሻ እንዲሆን በፍፁም አንፈቅድም፣ ድሉን የጋራችን አድርገን ልናስቀጥል ይገባል ብለዋል።

ብርሀን እንዳየሁ
ፎቶግራፍ ምስጋናው ከበደ

Leave a Reply