ከ400 በላይ ተጠርጣሪ ሌቦች በድንገተኛ ኦፕሬሽን ተያዙ

ሰሞኑን በተከናወኑ የኦፕሬሽን ስራዎች ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ በርካታ የተሰረቁ ንብረቶች እና ከ400 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡በከተማዋ የሚስውተዋሉ የወንጀል ስጋቶችን ለመቀነስ ልዩ ዕቅድ አውጥቶ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ገልጿል፡፡ፖሊስ እጅ ከፍንጅ የተያዙ መሳሪያዎችንና ንብረቶችን ዜናውን ባሰራጨበት ማህበራዊ ገጹ ላይ አኑሯል።

በከተማችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለህብረተሰቡ ስጋት እየሆኑ የመጡ ልዩ ልዩ ወንጀሎች እና ሌሎች የጸጥታ ስጋቶች ላይ የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ከተማዋን ከወንጀል ስጋት የፀዳች ለማድረግ የአዲስ አበባ ፖሊስ ልዩ ዕቅድ አውጥቶ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የተቋሙ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዘርፍ ሃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ሃሰን ነጋሽ ተናግረዋል፡፡

ከህብረተሰቡ በተገኙ ጥቆማዎች እና ፖሊስ ባደረገው ጥናት መነሻነት ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ ወንጀሎችን በመለየትና እና እነዚህ ወንጀሎች የሚፈፀሙባቸው አካባቢዎች ላይ በግልፅ እና በስውር እንዲሁም በቋሚና በተንቀሳቃሽ የሰው ሃይል ጥበቃ በማድረግ የመከላከል ተግባራትን ከማከናወን ባሻገር የኦፕሬሽን ስራዎችን በመስራት ውጤት ማስመዝገብ እንደተቻለ ምክትል ኮሚሽነር ሃሰን ነጋሽ አስረድተዋል።

በቀጥታ ወንጀሉን ከሚፈፅሙት ተጠርጣሪዎች ባሻገር በዘረፋና በስርቆት የተገኙ ንብረቶችን የሚቀበሉትን ግለሰቦች በጥናት በመለየት በእነሱ ላይ ጭምር የኦፕሬሽን ስራው መከናወኑን የጠቀሱት ምክትል ኮሚሽነር ሃሰን ነጋሽ በዚህ ልዩ ዕቅድ በተሰሩ ስራዎች ለወንጀል መፈፀሚያነት ሲውሉ የነበሩ እና የተሰረቁ ተሽከርካሪዎች፣ በርካታ የተሽከርካሪ መለዋወጫ ዕቃዎች፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ የግንባታ ዕቃዎች፣ የመሰረተ ልማት ግብዓቶች ፣ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች፣ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች እና ሌሎች ንብረቶች በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል፡፡ ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ የልዩ ዕቅድ ትግበራው እየተፈፀመ እና በእስካሁኑ ሂደትም 438 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝ ምክትል ኮሚሽነር ሃሰን ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ወንጀል በከተማችን ላይ ስጋት የማይሆንበትን ሁኔታ በዘላቂነት ማረጋገጥ እንዲቻል የልዩ ዕቅድ ኦፕሬሽን ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ምክትል ኮሚሽነር ሃሰን ነጋሽ የተናገሩ ሲሆን እስካሁን በተገኘው ውጤት ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና በማቅረብ ትብብሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Leave a Reply