ከሆሳዕና – ደቡብ አፍሪካ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ላይ 33 ተደራራቢ ክስ ተመሰረተ

የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀኔራል በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ከደቡብ ክልል ሆሳእና ከተማ እስከ ደቡብ አፍሪካ በርካታ ሰዎችን ለስቃይና ለእንግልት እንዲዳረጉ ባደረጉ 9 ግለሰቦች ላይ 33 ተደራራቢ ክሶችን መመስረቱ ተገለጸ

ከህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ በርካታ ዜጎች በህገ-ወጥ ደላላዎች አማካኝነት ለስቃይና ለሞት እየተዳረጉ ነው ሲሉ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሸጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ምህረቱ ቁምላቸው ገለጹ፡፡

እንደ ዳይሬክተር ጀኔራሉ ገለጻ ተቋማችን ከተሰጡት ተግባራት አንዱ አጥፉዎች ላይ ተገቢውን ክስ በማቅረብ በህግ መሰረት በጥፋታቸው ልክ ተመጣጣኝ ቅጣት እንዲያገኙ በማድረግ የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ መስራት ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም 9 ተከሳሾች በፈጸሙት ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል እንደ ወንጀል ተሳትፏቸው 33 ተደራራቢ ክሶችን በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 20ኛ የወንጀል ችሎት የካቲት 10/2015 ዓ.ም ክስ ተመስርቷል ብለዋል፡፡
የክስ ሂደቱን በተመለከተም አቶ ምህረቱ ሲያብራሩ 1ኛ አማኑኤል አበራ፣2ኛ ለማ ተማሮ ፣3ኛ አበበ ኑራሞ፣ 4ኛ አዳነ ሞሌ፣ 5ኛ ወልዴ አባቴ፣ 6ኛ ወሰን ታፈሰ፣ 7ኛ ዳንኤል ደስታ፣ 8ኛ አለሙ ዶልኢሶ እና 9ኛ መስፍን ተፈራ የተባሉ ተከሳሾች በመቀናጀት በ1996 ዓ.ም የወጣዉን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 32/1/ሀ/ እና አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀፅ 3/1/ እንዲሁም ፤አንቀፅ 3/2/ እና አንቀፅ 4/2/ሐ/ስር የተመለከተዉን በመተላለፍ የወንጀል ድርጊቱን ፈጽመዋል በማለት ነው ዐቃቤ ህግ ክሱን የመሰረተው መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡
ዳይሬክተር ጀኔራሉ አያይዘውም የክስ መዝገቡን በተመለከተ 1ኛ ተከሳሽ ካልተያዙ ግብረ-አበሮቹ ጋር በመሆን ከኢትዮጵያ የግዛት ክልል ዉጪ ለስራ መላክ በሚል ሽፋን በሞያሌ በኩል ኬንያ፣ ታንዛንያ፣ ማላዊ፣ ዛምቢያ፣ ወይም ሞዛንቢክ ደቡብ አፍሪካን መዳረሻ በማድረግ በሰዉ ለመነገድ በማሰብ 8 የሚሆኑ የግል ተበዳዮችን ከዚህ ቀደም በርካታ ሰዎችን ወደ ደቡብ አፍሪካ ልኮ ራሳቸውን እንደቀየሩ እና ምንም ችግር ሳይገጥማቸው ደቡብ አፍሪካ እንደሚገቡ ተናግሮ ለዚህም ጉዞ 350 ሺ ብር ያስፈልጋል በማለት የተስፋ ቃል የሰጣቸው መሆኑን አውስተዋል፡፡

ሚያዝያ 5 ቀን 2013 ዓ.ም ጠዋት ሆሳዕና ከተማ ጎንበር ሆቴል ዉስጥ ከ8ቱም የግል ተበዳዮች ቅድሚያ ክፍያ በሚል 100.000 ( አንድ መቶ ሺህ ) ብር ከተቀበለ በኋላ ከሃዋሳ ወደ ሞያሌ እንዲሄዱ በማድረግ በጉዞ ሂደቱ እንደመሸባቸውና ያቤሎ ከተማ እንዲያድሩ ካደረገ በኋላ ሞያሌ ከተማ ሲደርሱ ማንነቱ ላልታወቀ ግብረ አበሩ በማስተላለፍ ግብረ አበሩም በሞተር ጭኖ ጋንቦ የተባለ ጫካ ካደረሳቸዉ በኋላ ከጋንቦ ወደ ሴሎ በረሃ ቀን ቀን ጫካ ዉስጥ እየደበቋቸው፤ በሃያ አራት ሰዓት አንድ ጊዜ መጠኑ ትንሽ የሆነ የተቀቀለ ሩዝ በመስጠት ፤ማታ ማታ በእግር፣ በሞተር እና በመኪና እየተቀባበሉ ኬንያ ናይሮቢ ከተማ በአንድ ቤት ለአስራ አምስት ቀናት በመያዣነት በመያዝ እንዳስቀመጧቸው የወንጀል አፈጻጸም ድርጊቱ ያስረዳል ሲሉ አቶ ምህረቱ ተናግረዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም የተከሳሽ ግብረአበሮች ገንዘብ ካላስገባችሁ እዚሁ ትሞታላችሁ በሚል በኤሌክትሪክ ገመድ እና በዱላ በመደብደብ “100 ሺህ ብር ሀገር ቤት በሚገኙ ዘመዶቻቸው አማካኝነት ማንነቱ ላልታወቀ ግብረ አበሩ እንዲከፍሉ ካደረገ በኋላ ከናይሮቢ ከተማ ከፍተኛ ሙቀት ባለው የዕቃ መጫኛ ኮንቴነር ጭነዉ ሞምባሳ ከተማ በማቆራረጥ ታንዛንያ ድንበር ታፌታ በተባለ ቦታ በግምት ለአንድ ወር ከሶስት ቀናት እንዲቆዩ ማድረጋቸውን አክለው አንስተዋል፡፡

ከዚህ ሂደት በኋላም በእግር ለሰባት ሰዓታት ተጉዘው ታንዛንያ ሃገር ሞዋንጋ የተባለ ቦታ ሲደርሱ በታንዛንያ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ዉለው ሞዋንጋ በተባለ እስር ቤት ከአንድ ዓመት በላይ ለዕስር እንዲዳረጉ አድርገዋል ያሉት ዳይሬክተር ጀኔራሉ በአጠቃላይ የተበዳዮችን ደህንነት አደጋ ላይ በመጣል፤ ለኢ-ሰብዓዊ አያያዝ እና እንግልት እንዲዳረጉ ማድረገጉን አንስተዋል፡፡ አክለውም ከእስር በኋላም ሁሉም ተበዳዮች ብር 150,000(አንድ መቶ ሀምሳ ሺ ብር) በግል ዘመዶቻቸው አማካኝነት ነጃት መሃመድ ለተባለች ግብረ አበሩ ከፍለው ቀኑ በውል ካልታወቀ ሰኔ/2014 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ቀናትና ወራት ወደ ሃገራቸው የተመለሱ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በሰዉ መነገድ ወንጀል በ8 ተደራራቢ ክሶች መከሰሱን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ተከሳሽ አዲስ አበባ በሚገኘው የመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ፖሊስ ባደረገው ብርበራ ማካሮቭ ሽጉጥ ከ08 (ስምንት) መሰል ጥይቶች ጋር አስቀምጦ የተገኘ በመሆኑ በፈፀመው የፀና ፍቃድ ሳይኖር የጦር መሳሪያን አስቀምጦ መገኘት ወንጀል መከሰሱንም አቶ ምህረቱ የወንጀል አፈጻጸም ድርጊቱን በተመለከተ አክለው ገልጸዋል፡፡

ከ2ተኛ እስከ 9ኛ ያሉት ተከሳሾችም በዚህ የወንጀል አፈጻጸም ሂደት የነበራቸውን ሚና በመለየት ዐቃቤ ህግ ክሱን የመሰረተባቸው መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተር ጀኔራሉ የዋስትና ጉዳያቸውን በተመለከተም ዐቃቤ ህግ ከተከሳሾች ጋር ባደረገው ክርክር ጉዳዩን የመራው ችሎት መርምሮ ብይን ለመስጠት ለየካቲ 22/2015 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቷል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም ህብረተሰቡ ከእንደዚህ አይነቱ የተደራጀ ወንጀል ራሱን እየጠበቀ ጥቆማና ማስረጃዎችንም ለህግ አከላት በመስጠት መንግስት ዜጎችን በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር በማስወጣት ለከፋ እንግልትና ስብዕናቸውን ለሚያዋርድ ተግባር እንዲሁም ሂወታቸውን እንዲያጡ በሚያደርጉ ህገ-ወጥ ደላሎች ላይ የጀመረውን የህግ ማስከበር ስራ በጉልህ እንዲያግዘ ዳይሬክተር ጀኔራሉ መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን የፍትህ ሚኒስቴር በማህበራዊ ገጹ ያሰፈረው ዜና ያስረዳል።

Leave a Reply