የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዋና ዓላማ ለዜጎች የምትመች ሰላማዊት ኢትዮጵያን ማየት

ባሕርዳር:የካቲት 15/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ባለብዙ መልክ ናት። ሕዝቦቿም ከጠበቀ አንድነት ተቀድተው በመዋሃድ እንደ አለላ ቀለም ደምቀው የሚኖሩ ናቸው። ይህንን የአንድነት እሴት ለመናድ የፈለጉ የውስጥ እና የውጭ ጠላቶች በየዘመናቱ ቢነሱም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያ ግን ለክፉው ነገር ሁሉ እምቢ እያሉ የበለጠ በመተሳሰር ዘመናትን ሊሻገሩ ችለዋል።

የኢትዮጵያውያን የኑረት እውነታ ይኸው ቢኾንም ለዘመናት የካበተውን እሴት በሚቃረን መልኩ አፍራሽ የኾኑ የዘመን ውላጅ ባህሪያት በየፈርጁ እየተከሰቱ ያለመግባባት ምንጭ ሲኾኑ ይስተዋላል፡፡ ይህ ባህሪ ሀገራዊ መደማመጥን ቀንሶ ሕዝብን እስከ ጦርነት የዘለቀ አዙሪት ውስጥ መክተቱም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

በሕዝቦች መካከል ያሉ የቅሬታ ምንጮች በሙሉ ተለይተው መፍትሄ እንዲገኝላቸው መንግሥት በማመኑ “የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን” በ2014 ዓ.ም ተቋቁሞ ሥራውን ጀምሯል።

ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም እንደገለጹት ኮሚሽኑ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በሚወክል መልኩ የተቋቋመ ነው። ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ለዘመናት ጠብቀው የዘለቁ ቢኾንም አንዳንድ የማይግባቡባቸው ጉዳዮችም ስለመኖራቸው ኮሚሽነር መላኩ ተናግረዋል።

የምክክር ኮሚሽኑ ዓላማም የልዩነት ምንጭ የኾኑ ጉዳዮች በሙሉ ወደ ጠረጴዛ ቀርበው እንዲመከርባቸው እና መግባባት ላይ እንዲደረስ ነው ብለዋል። ኮሚሽኑ በሕዝብ የተመረጡ 11 ኮሚሽነሮችን ይዞ ከተቋቋመ ዓመት አልፎታል። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር ከሀገር ሽማግሌዎችና ከሐይማኖት አባቶች ጋር ውይይት መደረጉን ኮሚሽነር መላኩ ገልጸዋል።

የኮሚሽኑን ተግባርና ኀላፊነት ከማስተዋወቅ እና ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖረው የሚያስችሉ ውይይቶችን ከማድረግ የዘለለ ተግባር ግን አላከናወነም። የዚህ ማሳያ ደግሞ እስካሁንም ድረስ መሣሪያ ታጥቀው የዜጎችን ሕይወት የሚቀጥፉ ቡድኖች መኖራቸው ነው ብለዋል። እንደ ኮሚሽነር መላኩ ገለጻ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ውጤታማ እንዲኾን ሁሉም ኢትዮጵውያን ኮሚሽኑን በየኔነት ሊመለከቱት እና የራሳቸውን አስተዋጽኦም ሊያበረክቱ ይገባል ብለዋል።

ኮሚሽኑ ለሁሉም አትዮጵያውያን በእኩልነት የሚያገለግል መኾኑን በመገንዘብ የሃሳብ ልዮነት ያላቸው አካላት ወደ ውይይት በመምጣት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት ማድረግ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

“ኮሚሽኑ የማንኛውም የሀሳብ ልዩነት ባለቤት የኾኑ አካላትን አካታች ነው” ያሉት ኮሚሽነር መላኩ ኢትዮጵያ እና ዜጎቿ በመፈቃቀር ላይ የተመሠረተ ሰላም እንዲያገኙ በተለይም በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ አካላት ወደ ውይይት እንዲመጡ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል። “አፍራሽ አጀንዳ ያላቸው አካላት ለእኩይ አላማቸው ማስፈጸሚያ የሚጠቀሙት ወጣቶችን ነው” ሲሉ ኮሚሽነር መላኩ ተናግረዋል።

See also  የፍትህ ያለህ የሚሉት የ87 ዓመት አረጋዊቷ እሮሮ

ለዜጎቿ ምቹ የኾነች እና መደማመጥ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁሉም ወጣቶች ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን በሰከነ ሀሳብ መደገፍ እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል። የምክክር ኮሚሽኑ ወጣቶችን የበለጠ እንዲያካትት በማሰብ በዩኒቨርሲቲዎች ቅጥር ግቢ ውስጥ ጽህፈት ቤቶች እንደሚከፈቱም ኮሚሽነር መላኩ ገልጸዋል።

“ድሬዳዋ፣ ሀሮማያ እና ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲዎች ለኮሚሽኑ ጽህፈት ቤት የሚኾን ሕንፃ በማመቻቸት ወደ ሥራ መግባታቸውንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። “ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ዋና ዓላማ ሰላም የኾነች እና ለዜጎች የምትመች ኢትዮጵያን መገንባት ነው” ያሉት ኮሚሽነር መላኩ ቀጣዩ የኮሚሽኑ ተግባር ኢትዮጵያውያንን የሚከፋፍሉ የተቃርኖ ሀሳቦችን በመለየት ውይይት እንዲደረግባቸው ማመቻቸት ነው ብለዋል። ከውይይት በኋላም መተሳሰብ እና መፈቃቀር የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በትኩረት እንደሚሠራ ኮሚሽነር መላኩ ገልጸዋል።

አማራ መገናኛ ብዙሃን

Leave a Reply