የትውልደ ኤርትራዊው ራፐር ኒፕሲ ሃስል ገዳይ 60 ዓመት ተፈረደበት

ኤሪክ ሆልደር ጁኒዬር፤ በመጀመሪያ ደረጃ ግድያ ወንጀለኛ ሆኖ የተገኘው ባለፈው ሐምሌ ነበር። ግለሰቡ ራፐር ኒፕስ ሃስል አሊያም በመዝገብ ስሙ ኤርሚያስ አስገዶምን መግደሉ ተረጋግጧል።

ኤሪክ፤ ወንጀሉን የፈፀመው በፈረንጆቹ 2019 ደቡብ ሎስ አንጀለስ ውስጥ ኒፕስ ሃስል ከከፈተው ሱቅ ደጃፍ ላይ ነው። ለግራሚ የሙዚቃ ሽልማት የታጨው ራፐር ኒፕሲ ሃስል በ33 ዓመቱ ነው የሞተው።

ኤሪክ ወንጀሉን ሲፈፅም ሌሎች ሁለት አላፊ አግዳሚዎችም በተፈጠረው ግርግር ጉዳት ደርሶባቸው ነበር። የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ ኤች ክሌይ ዳኪ እንዳሉት 60 ዓመት የፈረዱት የኒፕሲን ጓደኛ ካናገሩ አልፎም ከገዳዩ አባት የተላከላቸውን ደብዳቤ ካነበቡ በኋላ ነው።

ወራት ከፈጀ የፍርድ ሂደት በኋላ ኤሪክ በግድያ ወንጀልና ሁለት በሥፍራው የነበሩ ሰዎች ላይ የግድያ ሙከራ በማድረግ ወንጀለኛ ሆኖ ተገኝቷል። ግለሰቡ ለሞት ቅጣት ብቁ ሆኖ ባለመገኘቱ የዕድሜ ልክ ፅኑ እሥራት ይጠብቀዋል።

ዳኛው ፍርዳቸውን በሰጡ ጊዜ የማረሚያ ቤት ብርቱካንማ ዩኒፎርም ለብሶ የቆመው ኤሪክ ፊቱ ላይ ምንም ዓይነት ስሜት አይነበብም ነበር።

የኤሪክ ጠበቃዎች ይግባኝ ሊጠይቁ እንዳቀዱ ኤቢሲ ለተሰኘው የዜና ጣቢያ ተናግረዋል።

ችሎቱ ክርክር በሰማበት ወቅት አቃቤ ሕግ ግድያው ታቅዶበት የተደረገ ነው ሲል ተከራክሮ ነበር። የወንጀለኛው ጠበቆች ደግሞ ሁኔታዎች በመጋጋላቸው የተፈጠረ ነው የሚል መከራከሪያ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ገዳዩ፤ ራፐር ኒፕሲ ሃስልን በትንሹ አስር ጊዜ ሽጉጥ ከተኮሰበት በኋላ ጭንቅላቱን በእግሩ መትቶ ከሥፍራ አንዳመለጠ የሎስ አንጀለስ ቀጣና ፖሊስ ጠበቃ አስረድተዋል።

ኒፕሲ ሃስል ደቡብ ሎስ አንጀለስ ውስጥ ነው ያደገው። ታዳጊ ሳለ ሮሊንግስ ሲክስቲስ የተሰኘ ‘ጋንግ’ አባል ነበር።

ራፐሩ፤ ማራቶን የተባለ የልስብ ሱቅ ከፍቶ ላደገበት አካባቢ ውለታ ሲመልስ ቆይቷል።

ከመሞቱ አስቀድሞ ወደ ሎስ አንጀለስ ፖሊስ አቅንቶ የጋንግ ወንጀልን እንዴት መቀነስ ይቻላል ሲል ተወያይቶ ነበር።

ኒፕሲ በፈረንጆቹ 2020 ከኅልፈቱ በኋላ ሁለት የግራሚ ሽልማቶችን በምርጥ የራፕ ትዕይንት ዘርፍ እና በምርጥ የራፕ ጥምር ሥራ አሸንፏል።

ኒፕሲ ሃስል ሁለት ልጆቹን ጥሎ ነው ያለፈው።

See also  "ከድል በኋላ ያሉ ድኅረ ድል መዛነፎችን ማረም እና የጋራ መግባባት መፍጠር አስፈላጊ ነው" አቶ ተመሥገን ጥሩነህ

ራፐሩ በተገደለ ወቅት በርካታ አሜሪካዊያንና ትውልደ ኤርትራዊያን ሃዘናቸውን ለመግለፅ በተለያዩ መታሰቢያዎች አስበውታል።

BBC Amharic

Leave a Reply