አብይ አሕመድ የኦሮሞና አማራ ክልል አመራሮችን ስብሰባ ጠሩ

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የአማራና የኦሮሚያ ክልል ከፈተኛ አመራሮችን ስብሰባ ጠርተዋል። ስብሰባው በሁለቱ ክልል አመራሮች መካከል እየተሰነዘረ ላለው የቃላት ጦርነት የመጨረሻ እልባት ለመስጠት እንደሆነ ተሰምቷል።

በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የያዙት ሁለቱ ፓርቲዎች በጋራ ለውጥ እንዲመጣ ተደጋግፈው ከሰሩ በሁዋላ በተለያዩ ጊዚያት ለህዝብ ብዙም ግልጽ ያልሆኑ ቅሬታዎች እንዳሏቸው ሲያስተጋቡ ነበር። በተለይም በመግለጫ መወነጃጀልና እንካ ሰላንቲያ መሰጣጣት የተለመደ ባህሪያቸው ቢሆንም አሁን አሁን ላይ አለመግባባታቸው ገፍቶ እየወጣ ነው።

አንዱ ሌላውን ” ቆሞ ቀር” በሚል ከመፈረጅ ባለፈ በአንድ ፓርቲ ውስጥ የተለያዩ አቋሞችን የማራመድ መዥጎርጎር ማሳየታቸው ህዝብን ግራ አጋብቷል። ለህዝብ ግልጽ ባልሆነ፣ በሚያወጡት መግለጫ የተደበሰበሰ መግለጫ ህዝብ ምን እንደተፈጠረ ባይገባውም ይህን ልዩነት በማጦዝ ነገሮች ወደ አላስፈላጊ ጫፍ እንዲሄዱ ሌሎች አይሎች እየሰሩበት ይገኛል።
ለዚህ ይመስላል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሀገሪቱ በሁለቱ ክልል አመራሮች መካከል የሚታየውን የፖለቲካ ሳይሆን የልዩነት (ህዝብ የማያውቀው ወይም በግልጽ ያልተነገረው ነው) ተንተርሶ የአማራ ክልል ካቢኔ አባላትንና እና የኦሮሚያ ክልል ካቢኔ አባላትን ከብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚዎች ጋር በጋራ ለማወያየትና መፍትሄ ለመፈለግ ስብሰባ እንደጠሩ ተሰምቷል።

በኦሮሞ ብልጽግናም በኩል አንዳንድ ካድሬዎች ከአማራ ብልጽግና መለየት እንዳለባቸው የሚያምኑ ሲሆን፣ በአማራ ብልጽግና በኩል ደርጅቱ ራሱን ማጽዳት አለመቻሉና በሌሎች ሃይሎች የተጠለፉ አመራሮች ውስጡን እየናጡት እንደሆነ ይሰማል። በቅርቡ በጎንደር የዳቦ ቤት ምርቃት ላይ ” አንድ እንሁን” ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ መናገራቸው ይሰማል። ” አንድ እንሁን” ሲሉም አንድ የመሆንን ጥቅምና ሃይልን ጠቅሰው ነበር።

ፓርቲዎቹ ለሕዝብ ግልጽ ባልሆነ ጉዳይና ደጋግመው ቢያነቡት ጥርት ያለ ምስል በማይሰጥ መግለጫ መወቃቀሳቸውን ተከትሎ ” ግልጽ አድርገው ካልነገሩን፣ ጉዳዩን ለሚያውቁት አካላት ብቻ ከጻፉት በአድራሻ ለሚፈለገው አካል መላክ ይቻላል” ሲሉ የተቹ ” ሚስጢር እየለቀለቁ ህዝቡን ከሚያዥጎረጉሩትና ጥላቻ ከሚዘሩበት ጎራ ለይተው ከአንድ ፓርቲ ጥላ ስር ቢወጡ ይሻላል” ሲሉ አስተያየት መስጥታቸውን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል።

See also  Kim Jong Un Urges Officials to Overcome the Country’s ‘Grim Situation’

ሁለቱ ክልሎች በጎጃም በኩል በቡሬ እስከ ወለጋ በዘለቀ ወረራና የተደራጀ ጥቃት ሳቢያ መካከላቸው ቅሬታ መግባቱን ኢትዮ12 መዘገቧ አይዘነጋም። ከጎጃም የተነሱ ታጣቂዎች ሙሉ ምስራቅ ወለጋን ወረው የነበር ሲሆን መከላከያ በወሰደው እርምጃ አሁን ላይ አካባቢዎቹ በሙሉ በራሳቸው ነባር አመራር እየተዳደሩ ነው። በአማራ በኩል አንገር ጉቲን የተለያዩ ቀበሌዎች በአማራ ክልል ስር እንዲተዳደሩ ፍላጎት ያለ ሲሆን፣ ይህ የሆነው የሰፋሪው ቁጥር ከመደበኛ ነዋሪው በላይ በመሆኑ ነው። ይህ ጥያቄ ኦሮሚያን ያስቆጣና ለአለመግባባቱ ዋና መንስኤ እንደሆነ ምንጮቻችን ጠቁመው ነበር።

ሌላውና ዋናው ጉዳይ ግን የፌደራል መንግስት በቡሬ አቅጣጫና በአንገር ጉቲን ሲነቀሳቀስ የነበረው ሃይል ከተመታና አካባቢውን እንዲለቅ ከተደረገ በሁዋላ የተረፈው አፈግፍጎ የገባው ወደ መጣበት አካባቢ በመሆኑ የደህንነት ጥያቄ እያነሳ ነው። መንግስት ይህ ሃይል በክልሉ በኩል ወደ ህጋዊ አግባብ እንዲመለስ ይፈለጋል። ይህን የፌደራሉን መንግስት ጥያቄ የማይቀበሉ የተወሰኑ አመራሮች መኖራቸው ሌላው የክፍተቱ ነጥብ ነው።

አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት ከሆነ ስብሰባው ይህን የሚመልስ ይሆናል። አለያም ግልጽ አቋም በመያዝ ሚናና ጎራ የሚለይበትና አንደኛው በአሸናፊነት የሚወጡበት ጅማሮ ይሆናል። ምክንያቱም በዚህ መልኩ መቀጠል አይቻልም።

Leave a Reply