የ”ጋላ ጠገበ” ፖለቲካ ባዶ ጉራ

በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረውና የተከሰተው ጉዳይ እጅግ አሳዛኝ ነው። የመንግስት ሃይሎች የሚችሉትን ያህል ታግሰው በዚህ መልኩ ተግባራቸውን ባይፈጽሙት ያማረ ነበር። ይህ ምኞቴ ነው። ዜናው እጅግ ለአንድ ወገን ያጋደለ ተደርጎ የተሰራ በመሆኑ በሚዛን ለመፍረድ አዳጋች አድርጎታል። ከደረሰው ጉዳትና የደረሰውን ጉዳት ለፖለቲካ ገበያ ለማዋል የተኬደበት ርቀት ሲታይ ደግሞ ጉዳዩ ቅስም ሰባሪና ሃፍት የተላበሰ ይሆናል። እንዴት?

“በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ለመወርወር የሚሆን ድንጋይ የለም። ያ ሁሉ ድንጋይ ከየት መጣ? አሮጎቶች ሳይቀሩ ድንጋይ ይወረውሩ ነበር። ምንም ከመፈጠሩ በፊት “ጋሎች ጠገቡ፣ ጋሎች አላስኖር አሉን፣ ጋሎች …” የሚሉም ድምጾች ተሰምተዋል። ይህ አካሄድና እይታ ትልቁን ስዕል እንዳያበላሽ ስጋት አለኝ” ያሉ አንድ ታዛቢ ነኝ ባይ አሳብ ተከትለን ነገሩን ለመመርመር ሞክረናል። በርግጥም ” ጋሎች ጠገቡ” የሚሉ ሰዎች ነበሩ። ምን ማለት ነው? የኦሮሞ ሕዝብ ጠገበ የሚባለው በምን ሂሳብ ነው? የኦሮሞን ህዝብ ” ጋላ” ብሎ መጥገቡን የሚናገሩ ክፍሎች አሳባቸው ምንድን ነው? ኦሮሞን “ጋላ ጠገበ” በሚል ከአዲስ አበባም ሆን ከአራት ኪሎ መጥረግ? ምን እንደሚፈለግና ኦሮሞን በጅምላ መሳደብ ለምን እንደተመረጠ ግልጽ አይደለም። ኦርሞን ብቻ ሳይሆን በርካታ ወንድምና እህቶችን የሚያስኮርፍፉ ተግባራት በተለያዩ መንገዶች እየተስተዋሉ ነው። በጥቂቱ … እንይ!!

አሁን አሁን ጎልቶ አደባባይ እየወጣና በመናበብ እየተደበደበ ያለው ጉዳይ ቢኖር አንዱ አፍቃሪ ኢትዮጵያ ሌላው ጸረ ኢትዮጵያ እየተደረገ የሚፈረጅበት አግባብ ነው። ረጋ ብሎ ላሰበው ይህ አደገኛ አካሄድ ሁሉንም በአፍጢማቸው የሚደፋ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የተለየ ባለቤትም ሆነ ልዩ ልጅ የላትም።

እንደ እውነቱ ቢሆን በራችንን ዘግተን ድህነታችን ላይ መረባረብ ነበረብን። ድሆች፣ ረሃብተኞች፣ ለማኞች ነን። የሕዝብ ቁጥራችን በየቀኑ እየናረ ነው። አገሪቱ በሌቦች እየታለበች፣ በዕዳ ብዛት ሰክራለች። አበዳሪዎቻችንም “ታማችኋል” ብለው እያሹን ነው። ስራ አጡ የሚታክት ቁጥር እየያዘ ነው። እንዲህ ያለች አገር ውስጥ በዘር ለመባላት፣ በልዩነት ለመናከስ ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባ ነበር? ችግር በተፈጠር ቁጥር ከውሽሞቻችው ጉያ፣ ከሚበሉት የቅጠል ክምር ውስጥ እየወጡ “ተነስ በለው” የሚሉንን እየሰማን እስከመቼ እንንጎድ? መንግስ ቂጥ ስር ሲታከኩ ቆይተው ያሰቡት ሳይሳካላቸው ወደ ስድብና ሴራ ፖለቲካ የተዛወሩትን አጀንዳ የምንቀበለው እስከመቼ ነው?

ኦርቶዶክስ የአንድ እምነት መለያ ነው። ሙስሊሙ፣ ካቶሊኩ፣ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት፣ አድቪነቲስት፣ ጅሆቫው፣ ዋቄፈታው፣ መካነ ኢየሱስ … እምነት የሌላቸውም ጨምሮ የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው። ሁሉም የዕምነት የወል ስሞች ወይም መለያ ወይም መገለጫ እንጂ አገር አይደሉም። ከሁላቸውም ኢትዮጵያ አብልጣ የምትወደው፣ የምታፈቅረው፣ ልዩ ውል የፈጸመችለት የእምነት ተቋም የላትም። ስለዚ ራስን ልዩ የአንድ ዕምነት ጠባቂና ጠበቃ አድርጎ ማቅረብ ብዙ አያስኬድም። በጥሞና ቢታሰብበት።

See also  በሞባይል ገንዘብ አገልግሎት በሚንቀሳቀስ የገንዘብ መጠን ላይ በድጋሚ ገደብ ሊጣል ነው 

ሁሉም ዕምነቶች የየራሳቸው ታሪክና መገለጫ ፣ የየራሳቸው መርህና መተዳደሪያ ደንብ አላቸው። ከዋናው የዕምነታቸው መሰረታዊ ልዩነት ውጭ እነዚህ ጉዳዮች ስለሚለያዩዋቸው አንዱ የሌላውን አክብሮ መኖር ግዴታ ነው። አንዱ በሌላው ቤት ገብቶ ሊፈተፍት አይችልም። ለዚህም ይመስላል ሁሉም ዕምነቶች ተከባብረውና ተስማምተው የኖሩት። ወደፊትም መኖር የሚችሉት። ከዚያ ባለፈ ግን ምንም መንገድ ለጊዜው አየሩን ያሞቀው ካልሆነ በቀር አድሮ በኪሳራ የሚያበቃ የጅል ጨዋታ ነው። በጥልቅት ቢታሰብበት።

አሁን አሁን ራሳቸውን የታሪክ፣ የዕምነት፣ የባህል፣ የወግና ልምድ ጠባቂ፣ ብቸኛ የኢትዮጵያ ጠበቃ አድርገው የሚያዩ ጎልተው ለመታየትና ሌላውን ለመጫን ሙከራ ሲያደርጉ እየታየ ነው። መንግስት ላይ ቅሬታ ለማቅረብ የሚኬድበት መንገድ የዚህ ማረጋገጫ ይሆናል። መንግስት ካጠፋ፣ ጥፋቱን ነቅሶ እንደ ድርጅት መጠየቅና መብትን ማስከበር ትክክል ቢሆንም፣ “እኔ አገር ነኝ፣ እኔ ልዩ ነኝ፣ እኔን መንካት …” የሚሉ ድምጾች ሌሎችን የሚያስከፉ መሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል። እዚህም ላይ ጥንቃቄ ያሻል።

በኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ሁሉም ነገር እንደተፈለገ በሚመነዘርበትና ለዓመጽ መጠንሰሻ ግብአት በሚውልበት በዚህ ወቅት በተለይ የዕምነት ተጠሪዎችና መሪዎች እጅግ ጥንቃቄ ሊወስዱ እንደሚገባ አስተዋዮች እየመከሩ ነው። አሁን በተያዘው መንገድ ነገ ሙስሊሙ ተነስቶ ” ሙስሊም አገር ነው” ቢል፣ ወነጌላዊያንም ተነስተው እንዲሁ ” እኛ አገር ነን” ቢሉ ጉዳዩ መቆሚያ አይኖረውም። ልዩነቱንም አያጠበውም።

ሁላችንም ራሳችንን የምናይበት መነጽር ሌሎችን “አያገባችሁም ወይም ጸረ ኢትዮጵያዊ ናችሁ” የሚል እንደምታ እየተሰጠው እንደሆነም ከቅሬታ አቅራቢዎች ሰፈር እየተሰማ ነው። ይህ አካሄድ ካልተገታ አደጋው የከፋ ሊሆን ይችላል። አደጋው አንዱ ጋር ካፈተለከ ሊቆም እንደማይችልም መረዳት አግባብ እንደሆነ ስጋት የገባቸው እየገለጹ ነው። ጉዳዩ በዴሞክራሲ ስም እጅግ ፈር እየለቀቀና ህዝብ ሰብሰብ ባለ ቁጥር ነውጥ እየተስተዋለ ነው። ይህ ምልክት ተደጋግሟል። ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ እነዲሉ ነውና ያስፈራል። እንጠንቀቅ!!

አሁን ኢትዮጵያ ከተሰራችበት፣ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ከተጓዘችበትና እየተጓዘችበት ካለው ሁኔታ፣ ከአወቃቀሯ አንጻር “አንድ” ተብሎ የሚነገር አንዳችም ጉዳይ ተቀባይነት እንደሌለው አምኖ አካሄድን ማስተካከል አግባብ ነው። “አንድ እምነት፣ አንድ ቤተ ክርስቲያን ” የሚባልበት እግባብ እጅግ ቀና በሆነ መንፈስ ካየነው ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚጎላ ይሆናል። 120 ሚሊዮንና የተለያዩ አመለካካእቶችና እምነቶች ባሉባት አገር ” አንድ” ብሎ መጀመር ልክ አይሆንምና ይታሰበበት።

See also  “የመላዉ ሕዝብ የጸጥታ ስጋት…”

ኢትዮጵያ ላይ ሴራ የሚያሴሩ በሙሉ አንዱ ሲከሽፍ ሌላ አጀንዳ በለዋወጡ ቁጥር ዝም ብሎ መነዳት መመለስ ከማይቻልበት ጣጣ ውስጥ እንዳይከተን ያስፈራል። በተወሰኑ ሰዎች ጥፋት፣ በራስ ዘረኛ እየታ ሳቢያ ኦሮሞ አገር በታኝ፣ አገር ከፋፋይ፣ ጸረ ኢትዮጵያ ወዘተ በሚል የተከፍተውን ዘመቻ በሃይማኖት አስደግፎ ወደ ሌላ ደረጃ ለማሳደግ የሚደረገው ከፓርላማ እስከ ችርቻሮ ላይ የተሰማሩ ሚዲያዎች ዘመቻ የታሰበውን ዓላማ ያሳካል? ወይስ አያሳካም የሚለው እንዳለ ሆኖ እጅግ አደገኛ ወደ ሆነ ቀውስ እንዳይከተን “ኢትዮጵያ” የምታሳዝናችሁ ሁሉ ተረባረቡ።

ተደራጅቶና ጠንካራ መዋቅር ፈጥሮ መንግስት ለመለወጥ ከመስራት ይልቅ በግርግር መንግስትን ለመናድ የሚኬድበት አግባብ ምን አልባትም አሁን መንግስት ካለው ድጋፍ የበለጠ ተቀባይነት ስለማግኘቱ ማንም እርግጠኛ አይደለምና “ዋ” የሚሉትን ሰዎች ማድመጥና ሰክኖ በድርጅት መታገሉ ይበጃል። ህዝብ በተሰበሰበ ቁጥር ሴራ በማምረት በንጹሃን ደም መነገድ ቢበቃ፣ ከትህነግ ትምህርት ቢወሰድበት የሚሻል ይሆናል። አለያ ኪሳራው ትልቅ ነው።

መንግስትን መቃወምና ማውገዝ አይገባም የሚል የዳፍንታሞች አይነት እይታ አግባብ እንዳልሆነ ሁሉ ፣ ተቃውሞንና ቅሬታን ለማቅረብ እጅግ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አለመረዳትም ሌላ ዳፍንታም መንገድ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ስለሆነም መመርመር አስፈላጊ ይሆናል። ቤተ ዕምነቶችን ጨምሮ!!

ሰሞኑንን በእምነት ” አባቶች” መካከል ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት ለማርገብ የተካሄደውን ሁለት ክፍል ውይይት ለሰሙ ዜጎች የጸቡ መጀመሪያና መጨረሻ ብር እንደሆነ ግልጽ ሆኗል። በውይይቱ ሁለቱ ወገኖች ሲካሰሱ የነበሩበት ጉዳይ ለሰላማዊ ሰልፍ የሚያበቃ ነበር? እንደው ጥቁር አስለብሶ የሚያስጮህ ነበር? ደግሞስ አንድ ወገን ” በቃኝ” ቢልና ቢለይ ለምን ይገደዳል ብሎ ማሰብስ አይቻልም? ነገ የአማራ ክልል የዕምነት “አባቶች” ተነስተው “በቃን” ቢሉ ሰላማዊ ስልፍ ልንወጣና ትቁር ለብሰን መንግስት ላይ ልንነሳ ነው? እናስተውል!!

በየቀኑ እየተለኮሰ በሚጠፋው እሳት የሚበሉት ድሆች ናቸው። የድሆችን አስከሬን የብሄር ስምና “ተሰዋ፣ ሰማዕት ሆነ” የሚል ማዕረግ በማሸከም አደባባይ ብንዞር፣ መግለጫ ብናወጣ ልጇን ለተነጠቀች ምስኪን ምን ይፈይድላታል? አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝብ ሰብሰብ ባለ ቁጥር እየተደረገ ያለው እጅግ አሳሳቢ የሚሆነው በብዙ ምክንያት ነው።

አጤ ሚኒሊክ የኢትዮጵያ መሪ፣ የኢትዮጵያ ብልህና አስተዋይ አስተዳዳሪ፣ መለኛ የጦር አዋጊና የአደዋ ድል መሃንዲስ ናቸው። በየደረጃው ለዚህ ድልና ለሳቸው አመራር አመቺ ሁኔታ የፈጠሩ በርካታ ጀግኖችም ከአድዋ ጋር አብረው ይነሳሉ። የህ የጥቁር ህዝብ ሁሉ ድል የሆነው የአደዋ ገድል በምንም መስፈርት አንድ ወገን ጠበቃ ሊሆንለት አይችልም። ሻሽ በማሰርና የወቅቱን መኳንቶች ካባ በመድረብ ልዩ ተቆርቋሪ መስሎ መታየትም አይስኬድም። እሳቸውንማ ሆነ ድሉን ለማሰብ የሚደረገው ቀናዊነት ይበል የሚያሰኝ ሲሆን በዛ ታሪካዊ ሃውልት ስር የፖለቲካ ቁማር መቆመር አይነፋም። ጥንቃቄ ያሻል።

See also  «ውሳኔው የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ ጠላቶች የሚቀንስ፣ኢትዮጵያን ለማጽናት የተውሰደ ነው» አብይ 7ተኛው ጥፋ እንዳይደገም አሳሰቡ

በኢትዮጵያ ነውጦች ታስበውና በድርጅት እንደሚከናወኑ ማሳያው፣ እንዲሆን የሚፈለገው ከሆነ ሰኮንዶች በሁዋላ ተጽፈው የተዘጋጁ ጽሁፎች፣ የተቀናበሩ ምስሎች፣ ከብረሃን ፍጥነት በላይ ማህበራዊ ሚዲያውን እንዲወሩት መደረጉ ነው። ተመርጠው ቃለ ምልልስ የሚደረጉ፣ ተመርጠው ፎቶ የሚነሱ፣ ተመርጠው ህዝብን ስሜታዊ የሚያደርጉ ቪዲዮዎች በቅጽበት ሲዘዋወር ትርጉሙ ለሚገባቸው ይገባቸዋል። ለዚም ነው ብዙ ታስቦ፣ አንዱም ያልተሳካው።

አሁን ላይ አዲስ አበባን በማተራመስ መንግስት መገልበጥ ቢቻል፣ ኦሮሚያ እሺ ይላል? ከላይ በተዘረዘሩት ነጥቦች መሰረት ሶማሌ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል፣ ሃረሪ፣ ደቡብ፣ አማራ ድሬሰዋ… በየትኛው ስሌት ይቀበላሉ? “ተነስ፣ ግፋ በለው” የሚሉ የመጨረሻ ህልማቸው መንግስት መሆን ስለሆነ፣ እሱ ደግሞ በዚህ አግባብ የማይሳካ ከሆነ መታረመሱና አገር እረፍት ማሳጣቱ ምን ይፈይዳል? በዚ አካሄድስ ዳግም ምርጫ ቢመጣ ድርጅት ሳይኖር ህዝብ ማንን አምኖ እጁ ላይ ያለውን ያፈርሳል? ለሁሉም ማስተዋል ግድ ይላል። ዝም ብሎ አንድን ትልቅ ህዝብ ” ጋላ ጠገበ” በሚል መሳደብ ከባዶ ጉራ አያልፍምና አሁንም ደግመን ደጋግመን እናስብ።

“ጋላ አገር በታኝ” በሚል ተራ ስብከት መወሰደ ጉዳቱ ያመዝናል። አንድ ጸሃፊ እንዳሉት በቅርብ ታሪክ በረህ ወርዶ ያዋጋና የተዋጋ፣ ሲስቃዩ ለነበሩ ዜጎች ነጻነት እንዲሆን በአደባባይ የሰራን ሰውና እሱ የሚወክለውን ህዝብ በደቦ መዝለፍ ለኢትዮጵያም ሆነ ለዘላፊዎቹ ምን ያህል እንደሚጠቅማቸው አድሮ የሚታይ ቢሆንም፣ እኛ ይህ አካሄድ አይጠቅምም በለን በድፍርተ ለማሳሰብ ቀዳሚውን ስፍራ ወስደናል። በአመክንዮ መመርመር የሚባል ነገር የጠፋበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ መስመር እንዲይዝ ከማድረግ ውጪ አማራጭ የለምና እንስከን። መንግስትም እርምጥምጥ ካድሬዎችህን አደብ አስይዝ። ህዝብን የሚያስለቅሱ ሌቦችህን እፈስ። በየአደባባዩ እንዳመጣላቸው የሚናገሩትን ልጆችህን ግራ።

ኢትዮጵያ ልዩ ልጅ የላትም። ሚኒሊክም ልዩ ተቆርቋሪ ወክለው አላለፉም። የዕምነት ቤቶችም በስፋትና በእድሜ፣ እንዲሁም በአደረጃጀትና በህገ ደንባቸው ይለያኡ እንጂ በግብር የኢትዮጵያ እኩል ባለድርሻ ናቸው። ኢትዮጵያ የሁሉም ናት። ፖለቲከኞች ነን የምትሉ ህዝብ እንዲረጋጋና አገር እንዲሰክን ቅድሚያ ወስዳችሁ ስሩ። በትግራይ የተጀመረው ሰላም በኦሮሚያም እንዲሆን አግዙ። የተበተኑና ወደ ቅዩያቸው ለመለስ የናፈቁትን ለማገዝ ደፋ ቀና በሉ። ተደራጁና የህዝብ ቀልብ ግዙ። በጓሮ በር ለመግባት እየተሯሯጣችሁ ጊዜ ከምትገድሉ ተደራጁና መንግስትን አስነጥሱት። ሚዲያዎችም ኳስ በምድር እናድርግ። የጥላቻና የቅሰቀሳ ሪፖርት በየቀኑ ሲረጭ አንድ ቀን ምን ሊሆን እንደሚችል በማሰብ የመሪነት ሚና እንጫወት። በ1997 ያጠፋነውን ጥፋ አንርሳ። ” ፓርላማ ተግቡና ዋ” ብለን ያን የመስለ የህዝብ ድምጽ በዜሮ እንዲባዛ ተሳትፏችን ትልቅ ነበር።

በውጭ አገር በጀትና ድጋፍ የምትንቀሳቀሱ፣ በውጭ አገር በተቋቋሙ ሚዲያዎች ተቀጥራችሁ የምትሰሩ እንዳይቆጫችሁ እርጋታን ምረጡ። ላለፉት ሁለት ዓመታት ጌቶቻችሁን ለማስደሰትና የተቀጠራችሁበትን ዓላማ ለማሳካት ኢትዮጵያ ላይ ስትረጩ የነበረው ሚዛነ ሰባራ መርዝ በየትኛውም ዘመን አይረሳም። ልባሞች አስቀምጠውታል። ለልጅ ልጆችቻሁ የተላለፋል። ልክ እንደ ስራችሁ ሁሉ ዘመን በአንድ ወቅት “ስም” ይሰጣችኋል። እናነተም ወደ ቀልባችሁ ተመለሱ። ጉዳዩ የእምዬ ኢትዮጵያ እንጂ የግለሰቦች ወይም የድርጅት አይደለምና!!

2 Comments

  1. እኔ እምልህ ጠሚ አብይ ለአዳነች አቤቤ የስድስት ቀን ቀነ ገደብ ሰጧታል በስድስት ቀናት ውስጥ ጠሚ አብይ ከንቲባዋን ከስልጣን በማንሳት ከህዝብ ጎን መቆማቸውን ያሳያሉ ያልከው ነገር 11 ቀን ሞላውኮ … ስለዚህ ጠሚሩ ከሌባ ጋር መወገናቸውን አሳዩ ማለት አይደለም ?? እኔ አልላኩም አንተው ራስህ ነው በጹሁፍህ ያልከው //// ለማንኛውም ይሄን ትልቅ የተከበረ ህዝብ እያሳነሱት እኒሰደብ እያደረጉት ያሉ ቁማርተኞች መሆናቸውን ልብ ልትል ይገባል። ጥላሁን ገሰሰ ፡ደራርቱ ቱሉ ፤ ቀነኒሳ በቀለ፤ ፀጋየ ገብረመድህን፤ አብዲሳጋ፤ ጃጋማኪሎን እንድሁም አቡነ ጴጥሮስ በላይ ኢትዮጲያዊ የለመ እነዚህን ድንቆች ያፈራን ማህበረሰብ ማንም ከመሬት ተነስቶ ሊጠላ እና ሊያንቋሽ አይችልም …. እንዲሰደብም እንዲጠላም እያደረጉት ያሉ አሁን የበለጸጉት ቁማርተኞች ናቸው …. ይልቅ አንድ ነገር ብለሃል ከላይ ከህውሃት ያልተማረ ማን ነው ከህውሃት ያልተማረው ??? ራስህን ብጠይቅ ጥሩ ነው።

    1. Author

      ሰላም ይሁንልህ፤ ዜናውን መስራት እንጂ ውሳኔ ሰጪ አይደለንም። ዜናው ላይ ስህተት ካለ ወይም በግልዎ የሚያውቁት ጉዳይ ካለ ቢጠቁሙን ለማከል ዝግጁ ነን። ለመጻፍ ስለማንፈልግ እንጂ ከዚህም በላይ የሚያሙ ጉዳዮች አሉ። ካድሬን ከህዝብ ለይቶ ማየት አጋባብ እንደሆነ ለመጠቆም ያህል እንጂ ከዚህም ያለፈ ብዙ ማለት ይቻላል። ስለ አስተያየትዎ እናመሰግናለን።

Leave a Reply