ኢንሱሊን – የታክሲ ውስጥ ድራማ መሰለ ገጠመኝ

ባለፈው ሳምንት እንደተለመደው ወደ ቤቴ ከስራ ስመለስ በታክሲ ውስጥ ያጋጠመኝን ነገር ላጫውታችሁ። ታሪኩ እንዲህ ነው… እንደተለመደው ሀገር ሰላም ብዬ ታክሲ ውስጥ ገባሁ (3ተኛ ረድፍ ወንበር ) 2 ሰዎች ቀድመው ተቀምጠው ነበር ፣ ጫፉ ላይ ተቀምጦ የነበረው ሰውዬ ቦታውን መልቀቅ ስላልፈለገ መሀል እንድገባ ጠየቀኝ ይመችህ ብዬው መሀል ገብቼ ጉዞ ጀመርኩ::

መድረሻዬ ከመድረሴ ግማሽ መንገድ ሳልደርስ አጠገቤ የተቀመጠው (ጠርዝ ላይ ተቀምጦ እና መሀል እንድቀመጥ የነገረኝ) ሰውዬ በድንገት “ያልተለመደ የሰውነት እንቅስቃሴ” (abnormal body movement) ማሳየት ጀመረ፣ በዛ ወቅት የነበረውን ትክክለኛ የሰውነት እንቅስቃሴ በቃላት ለመግለጽ ትንሽ ከባድ ነው ነገር ግን የታሪኩ ፍሬ ነገር በዚህ ክስተት ውስጥ ስለሆነ ለመግለጽ የምችለውን ሁሉ ለማድረግ እሞክራለሁ።

ድንገት ከተቀመጠበት ጠርዝ ተገልብጦ በመውደቅ መኪናው ወለል ላይ በጀርባው አረፈ፣ መላ ሰውነቱ መገታተር ጀመረ… ቀና ብሎ ወደ መኪናው ጣሪያ እያየ ነበር፣ የተወሰነ ምራቅም ከአፋ ይወጣ ነበር ወዲያው በግራ ጎኑ እንዲተኛ በማድረግ ላይ እያለው በግራ እጁ የታችኛውን የሆድ ክፍሉን ደጋግሞ በመምታት በቃስታ ድምፅ መድሀኒት መድሀኒት ማለት ጀመረ።

ታክሲው ወዲያው ቆመ፣ እኔን ጨምሮ ሁሉም ተሳፋሪዎች ደንግጠው ነበር… እዚያው ቦታ በተደጋጋሚ ሆዱን መምታቱን ቀጠለ (ለተወሰነ ጊዜ የጣለው በሽታ ነው እንደዚህ ምያስደርገው ብዬ አስቤ ነበር) በኋላ ግን እዚያው በተደጋጋሚ ሚመታበት ቦታ ላይ መድሃኒት በኪሱ ይዞ ሊሆን ይችላል ብዬ ጠረጠርኩ። ኪሱን እዚያው ቦታ ከፍቼ ኢንሱሊን እና የኢንሱሊን መርፌ አገኘሁ፣ ሰውዬውም አሁንም በ ቀስታ እና በ ተናነቀ ድምፅ 10 ዩኒት ፣ 10 ዩኒት ማለት ቀጠለ።

ታክሲው ውስጥ ያለ ሁሉም ሰው የስኳር ህመምተኛ ሊሆን እንደሚችልና መድሀኒቱን መውሰድ እንዳለበት መነጋገር ጀመሩ፣ እኔ ከጎኑ ሆኜ ይዤው የነበረውን የኢንሱሊን አይነት እንዲሁም ልብ ምቱን መመርመር ጀመርኩ::

ታክሲ ውስጥ ያሉት ሰዎች ደጋግመው የሱን ኢንሱሊን እንድሰጠው ይነግሩኝ ነበር፡ የበለጠ ግራ ገባኝ፡ እንደውም ከእርሱ ጋር ይዞት የነበረው ኢንሱሊን NPH ነው። የሰውነት ስኳር መጠን ማነስ ሊሆን ይችላል ብዬ በመገመት ኢንሱሊኑን ከመስጠት ተቆጥቤ ከረዳቱ የተቀበልኩትን ኮካ ኮላ ቀስ እያልኩ ለማጠጣት ሞከርኩ::

See also  አሸባሪው ሕወሓት በፈጸመው ወረራና አፍራሽ ተግባራት ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተጎድተዋል

አሁንም ግን ሰውየው 10 ዩኒት፣ 10 ዩኒት እያለ ሆዱን መምታት ቀጠለ … በመኪናው ውስጥ ያለ አንድ ሰው እናቱ ተመሳሳይ ችግር እንዳለባት እና ኢንሱሊን የመስጠት ልምድ እንዳለው በመግለጽ ኢንሱሊኑን ቶሎ እንድሰጠው ሀሳብ አቀረበ። እንደ እድል ሆኖ ታክሲው ከቆመበት አካባቢ ፊት ለፊት ፋርማሲ ነበረ እና ረዳቱን ፋርማሲስቱን ግሉኮሜትር (የሰውነት ስኮር መጠን መለኪያ) እንዲጠይቅ ነገርኩት ፣ፋርማሲስቱ ለመተባበር ፈቃደኛ ሳይሆን በአቅራቢያው ወደሚገኝ ክሊኒክ ጠቆመን፣
አሁንም ግሉኮስ መጠኑ እስካልተረጋገጠ ድረስ ኢንሱሊን አልሰጠውም አልኩኝ እና በምትኩ ኮካውን መስጠት ቀጠልኩ፣ በታክሲው ውስጥ ያሉ ተሳፋሪዎች ለሁለት ተከፍለው (አንዳንዶች) ኢንሱሊን ስጡት ፣ አንዳንዶች ክብሪት ያለው ካለ ብለው ጠይቀው ነበር፣

እኔ የህክምና ባለሙያ እንደሆንኩና የያዘው መድሃኒት NPH ሚባል የኢንሱሊን አይነት እንደሆነና አሁን ያለበትን ሁኔታ እንደማያቆመው እንደውም ሊያብሰው እንደሚችል … እውን የሰውነት ስኳር መጨመር እንኳን ቢሆን በፍጥነት ማውረድ እንደማይችል(መዳኒቱ ለመስራት ከ2-3 ሰአት የጅማሬ ጊዜ) እንዳለው ለማስረዳት ሞከርኩ።

ምንም እንኳን በዚያ ወሳኝ ጊዜ ነገሮችን በተቻለኝ መጠን ብገልጽም፡ እሰጠዋለሁ ያለው ሰውዬ ኢንሱሊኑን ተቀብሎኝ 10iu እምብርት አካባቢ ሰጠው (ልብ በሉ ታሞ የወደቀው ሰውዬ ኢንሱሊኑን ሚወጋበትን ቦታም እየጠቆመው ነበር)፣ ወድያው መገታተር አቁሞ ራሱን ከወደቀበት አንስቶ ወንበሩ ላይ ተቀመጠ፣ የጠዋት ኢንሱሊኑን ሳይወስድ እንደወጣም ተናገረ

ኢንሱሊኑን የሰጠው ሰው “እንደመሚሰራ አየህ” አለኝ… ተሳፋሪው ሁሉ አፍጥጦ አየኝ “የጥላቻ አይን”…
መኪናው ተነሳና ጉዞአችንን ቀጠልን።

ግራ የመጋባት ስሜት ከቁጣ ጋር ተደባልቆ እየተሰማኝ (የኔ ኢጎ ተጎድቷል… 😂) አጠቃላይ ሁኔታውን እንደገና ማብሰልሰል ጀመርኩ።

ተሳፋሪዎቹ ሰውየውን ወዴት እየሄደ እንደሆን ይጠይቁት ጀመር ፣ እሱም ትንሽ በተላዘዘ ንግግር መድረሻውን ነገረን እና ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ኢንሱሊን እና ግሉኮስ ለመግዛት ገንዘብ እንዳጠረውና ይህንን ችግር ለመቅረፍ 500ብር እንደሚያስፈልገው ገልፆ ገንዘብ መለመን ጀመረ። በመጨረሻም ወደ መድረሻው ደረሰ እና የተሰበሰበውን ገንዘብ ይዞ በዝምታ ሄደ። (በብርሃን ፍጥነት ማለት ይቸቻላል)

በዚህ ሰአት ነው አስመሳይ አርቲስት መሳይ (CON ARTIST) እንዳጋጠመን እና ሚገርም ተውኔት ተውኖ አታሎን እንደሄደ የተረዳሁት። ለምን እንደዛ አልክ ካላቹ ከዚህ በታች ያሉትን ነጥቦች ላስቀምጥ…

See also  በድርድር የሰጥቶ መቀበል መርህ ኢትዮጵያ ከትህነግ ምን ታገኛለች?

1. ገና ከመጀመሪያው ጀምሮ ጫፉ ላይ መቀመጥ ፈልጎ ነበር (ለሚሰራው ትያትር እና ለሚመጣው ተግባር ተጨማሪ ቦታ እንዲኖረው…;)

2. በኪሱ ውስጥ ኢንሱሊን ይዞ ነበር ነገር ግን አልወሰደውም እንዲውም ጠዋት እንደረሳው ተናግሯል

3. የሰውነቱ መገታተር እና መንቀጥቀጥ ያልተለመደነ ነበር፣ (it was asymmetric) እጁ መድሃኒቱን እየጠቆመ አንድ እጁ ግን ወደ ላይ ተገትሮ እንደቀረ ነበር

4. በዚህ ሁላ ክስተት ወስጥ ንቃተ-ህሊናውን አልሳተም ነበረ

5. ከNPH መርፌ በኋላ ወዲያውኑ ከነበረበት ሁኔታ ነቃ (እኔ ኮካ ሳጠጣው አይደለም…)

6.እንደተነሳ ኢንሱሊን ብሎም ጉሉኮስ ለመግዛት ገንዘብ መለመን ጀመረ።

ያልተጠቀሰ ካለ ተጨማሪ ማከል ትችላላችሁ ።

ከዚህ ክስተት የተረዳሁት ነገር ቢኖር በአገራችን አብዛኛው ሰው ስለ ተለመዱ ሥር የሰደዱ በሽታዎች መሠረታዊ እውቀት እንደሌለው፣ (basic knowledge about common chronic diseases) በሌላ በኩል ደግሞ ህዝባችን በጣም ሩህሩህ እና በተስፋ መቁረጥ ውስጥ/ጉዳት ላይ ያለን ሰው ለመርዳት በጣም የሚጓጉ እንደሆኑ (የታሪኩ ዳራ ምንም ቢሆን).. ከዚ በተጨማሪም ብዙ ማከል ይቻላል-

የእኔ ታሪክ በተወሰነ ደረጃ ግንዛቤን እንደሚፈጥር ተስፋ አደርጋለሁ ፣ እንዲሁም እናንተም በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ብትሆኑ ምን ማድረግ እንደሚችሉ ለማወቅ በጣም ጓጉቻለሁ።

የገጠመኝን ክስተት በጥሞና በማንባችሁ አመሰግናለሁ
ዶ/ር አንተነህ ጥሩሰው : ጠቅላላ ሀኪም
Telegram: t.me/HakimEthio

Leave a Reply