የትግራይ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ መደበኛ ህይወት ሊመለሱ ነው

የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ መደበኛ ህይወት በመመለስ የአገርን ሰላምና እድገት በማገዝ ረገድ ጉልህ ሚና እንዲወጡ ይደረጋል- የኮሚሽኑ አደራጅ የቴክኒክ ኮሚቴ

አዲስ አበባ መጋቢት 2/2015 (ኢዜአ) የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ መደበኛ ህይወት በመመለስ የአገርን ሰላምና እድገት በማገዝ ረገድ ጉልህ ሚና እንዲወጡ የሚደረግ መሆኑን የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን አደራጅ የቴክኒክ ኮሚቴ ገለጸ።

የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ሰላማዊ ህይወት በመመለሱ ሂደት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አረጋግጧል።

መንግሥትና ህወሓት የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት ትግበራ አካል የሆነው ብሔራዊ የተሃድሶ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በመቀሌ ተካሂዷል።

በመድረኩም የትጥቅ ማስፍታት፣ የቀድሞ ተዋጊዎችን በአንድ ማዕከል የማሰባሰብና ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል ዝርዝር መርሃ ግብርና የሀገራት ተሞክሮዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን አደራጅ የቴክኒክ ኮሚቴ አባል አቶ ገመዳ አለሚ፤ የቀድሞ ተዋጊዎችን የማቋቋም መርሃ-ግብር ከትጥቅ ማስፍታት ጀምሮ እስከ መልሶ ማቋቋም ድረስ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የሚተገበር መሆኑን ገልጸዋል።

የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም ሂደትም ማህበረሰቡን መሰረት ባደረገ መልኩ በማከናወን ከስራ እድል ፈጠራ ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎች የሚደረግላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የታጠቁ ኃይሎች ትጥቅ ፈትተው ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀላቸውም የሀገርን ሰላምና እድገት በማገዝ ረገድ ጉልህ ሚና እንዲወጡ ያስችላል ነው ያሉት።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የመልሶ ማቋቋም ሂደቱ የሀገራትን ተሞክሮ ከኢትዮጵያ አውድ ጋር ባገናዘበ መልኩ ሊተገበር ይገባል ብለዋል።

ለሁለት ዓመታት ጦርነት በቆየባቸው አካባቢ ያሉ ተዋጊዎችን ብቻ ሳይሆን ግጭት በነበረባቸው ሌሎች አካባቢዎችም ያሉትን ተዋጊዎችና ማህበረሰቡን በብሔራዊ የተሐድሶ መርሃ-ግብሩ ማካተት እንደሚገባ አንስተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች አክለውም የብሔራዊ ተሀድሶ እና የመልሶ ማወቋቋም ሂደቱ የሽግግር ፍትሕንም ሊጨምር እንደሚገባ አንስተዋል።

ሂደቱ የጦር ጉዳተኞችና ሴቶችን በልዩ ሁኔታ መመልከት ይገባል ሲሉም አስተያየት ሰጭዎቹ ገልጸዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዶክተር የሺመብራት መርሻ፤ የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ሰላማዊ ህይወት በመመለሱ ሂደት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።

See also  ደቡብ ወሎ የሞርታር ተተኳሽ የደበቀው ግለሰብ እጅ ከፍንጅ ተያዘ

የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም ሂደት ማህበረሰቡን ባማከለ መልኩ እንዲተገበርም አስፍላጊውን የግንዛቤ መፍጠር፣ የድጋፍና ክትትል ስራዎችን ለማከናወን ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply