ሴሬብሮቫስኩላር ህመም ምንድነው? ቅድመ ጥንቃቄውስ?

የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት በተለያዩ የጤና ችግሮች ከደም ስሮች ጋር በተያያዘ እክል የደም ዝውውርን መታወክ በማስከተል እንደሚከሰተው ይኽ ህመም በተለይ ከዕድሜ መግፋት ጋር በተገናኘ በብዛት ሊያጋጥም ይችላል።

ለመሆኑ በእንግሊዝኛ ሴሬብሮቫስኩላር ስለሚባለው የጤና ችግር ሰምተው ይሆን? የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት በተለያዩ የጤና ችግሮች ከደም ስሮች ጋር በተያያዘ እክል የደም ዝውውርን መታወክ በማስከተል እንደሚከሰተው ይኽ ህመም በተለይ ከዕድሜ መግፋት ጋር በተገናኘ በብዛት ሊያጋጥም ይችላል። 

ከፍተኛ የደም ግፊት እንዲሁም የስኳር ህመም ተገቢው ክትትልና ህክምና ካልተደረገለት ጭንቅላት ውስጥ የደም መፍሰስ ሊያስከትል እንደሚችል ይኽም በአንድ ወገን የሰውነት ያለመታዘዝን አልፎ ተርፎም አንደበትን ሊይዝ እንደሚችል የህክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ።  

ስለዚህ የጤና ችግር የህክምና ባለሙያ እንድንጠይቅ ምክንያት የሆነን ከአድማጭ የቀረበልን ጥያቄ ነው። «በዓለማችን ከጤና ጋር የተያያዙ ችግሮች ብዙ ናቸው። አንድ ሁለት ብሎ ለመቁጠርም አዳጋች የሆኑ።» ይላሉ ጠያቂያችን፤ « አንዳንዶችም ሳይንስ ተመራምሮ የደረሰባቸውና መፍትሔም የተገኘላቸው ናቸው ።ብዙዎች ደግም በእንጥልጥል ላይ ያሉ መፍቴሔ የሚሹ ሲሆን ከፊሎች ደግም  የመንሴኤ ምክንያታቸው ያልተደረሰባቸው ናቸው። ወደ ዋና ጥያቄ ልመልስሽና በአብዛኛው የዓለምን ሕዝብ በተለይ ደግሞ በዕድሜ ገፋ ያሉትን እያጠቃ ያለው ሴሬብሮ ቫስኩላር የሚባለው ከእስትሮክ ጋር ተያያዥነት ያለው በሽታ ነው። ለመሆኑ ይህ ሴሬብሮ ቫስኩላር የሚባለው በሽታ መንሴኤው ምንድን ነው ? ሊደረግለት የሚገባው ቅድመ ጥንቃቄስ ? ስለ ተለመደ ትብብራችሁ በቅድሚያ አመሰግናለሁ።» በማለት ጥያቄያቸውን የላኩልን የዘወትር አድማጫችን የመቶ አለቃ ውቤ ታሪኩ ናቸው። የመቶ አለቃ ውቤ እኛም ለዘወትር ተሳትፎው ምስጋናችንን እናስቀድማለን። እርግጥ ነው እርስዎ እንዳሉት ለብዙዎች ሕልፈተ ሕይወትም ሆነ ህመም ምክንያት ሆነው ሳለ እስካሁን መንስኤያቸው በውል ያልተደረሰባቸው ህመሞች መኖራቸውን የህክምና ባለሙያዎች በየጊዜው ይገልጻሉ። በአንጻሩ የደም ዝውውር መታወክ ወይም በህክምናው ስትሮክ በመባል የሚታወቀውን የጤና እክል የሚያስከትሉ መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉ ነገሮች አሉ። ከዚህ የጤና ችግር ጋር የሚገናኘው ደግሞ እርሶ መንስኤውን ማብራሪያ የጠየቁበት በህክምናው ሴሬብሮ ቫስኩላር በሽታ የተባለው ነው። በደም ዝውውር ላይ በሚከሰት እክል ምክንያት የደም ስሮች ሲገዱ አንድም ጭንላት ውስጥ የደም መፍሰስ አለያም የደም ስር መዘጋት ያጋጥማል። ይኽ ነው ሴሬብሮ ቫስኩላር በሽታ ተብሎ በህክምናው የሚገለጸው በማለት ማብራሪያ የጠየቅናቸው የነርቭ ከፍተኛ ሀኪም ለሆኑት ዶክተር ተሻገር ደመቀ ገልጸዋል።

የነርቭ ከፍተኛ ሀኪሙ እንደሚሉትም ለዚህ ችግር የሚዳርጉት በተለይ ከፍተኛ የደም ግፍት እና የስኳር ህመም እንዲሁም በደም ውስጥ የስብ ክምችት በህክምናው ኮሌስትሮል የሚባለው ንጥረ ነገር መበርከት ጋር የተያያዙ የጤና ችግሮች በአግባቡ ክትትል እና ህክምና ያልተደረገላቸው እንደሆነ ነው።

የደም ግፊትን መቆጣጠር እና መከታተል ያስፈልጋል

የጤና ችግሩ በአብዛኛው ከዕድሜ መግፋት ጋር እንደሚገናኝ አልፎ አልፎ ልጆችም ሆነ ወጣቶች ላይ ሊያጋጥም እንደሚችልም ነው ያስረዱት። በተለይ በዘረመል መወራረስ ምክንያት በልጅነትም ይሁን በወጣትነት ዕድሜ የደም መርጋት ችግር የሚያጋጥማቸው ሊኖሩ እንደሚችሉ ይኽ ደግሞ የደም ዝውውርን ለማወክ እንደሚዳርግም አመልክተዋል። በአጠቃላይ ግን ሪህ የሚባለው የጤና እክልም ሆነ  የውስጥ አካል ክፍሎችን እብጠት ወይም መቆጣትን የሚያስከትሉ የጤና ችግሮች የደም ስር ላይም ሊከሰቱ እንደሚችችሉና ለዚህም ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉም አስረድተዋል። ወጣቶች ላይ እንዲህ ያለው የጤና ችግር ሲያጋጥም መንስኤው ከተጠቀሱት የተለየ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ እንደሚኖርም አጽንኦት ሰጥተዋል። ከዕድሜ መግፋት ጋር በተገናኘ ለሚከሰተው ግን የደም ግፊትም ሆነ የስኳር ህመም መኖሩ ታውቆ ተገቢው ክትትል እና ቁጥጥር ካልተደረገበት ለዚህ ሊዳርግ እንደሚችልም ነው የገለጹት። ህክምናውን በተመለከተም ተገቢው ምርመራ ከተደረገ በኋላ እንደችግሩ ምንነት ታይቶ የሚከናወን መሆኑንም አብራርተዋል። ሰዎች እንዲህ ላለው የጤና እክል እንዳይዳረጉ አስቀድመው በቂ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግን፤ አመጋገብ ላይ መጠንቀቅን፤ የሰውነት ክብደትን መቆጣጠር እንደሚያስፈልግ መክረዋል። በተጨማሪም የአልክሆል መጠጥ አወሳሰድ ላይ መጠንቀቅን፤ ትንባሆ ያለማጨስንም አሳስበዋል። የዘወትር አድማጭ እና ተሳታፊያችን የሆኑት የመቶ አለቃ ውቤ ታሪኩ በቂ ማብራሪያ እንዳገኙ ተስፋ እናደርጋለን። ለሙያዊ ማብራሪያው የነርቭ ከፍተኛ ሀኪም የሆኑት ዶክተር ተሻገር ደመቀን እናመሰግናለን።

DW amharic

Leave a Reply