ውሃና ኢነሪጂ ሚኒስተር -ክልሎች አምስት ቢሊዮን ብር ወስደው ከለከሉኝ

ክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ውሃ ለማልማት የተበደሩትን አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ለመመለስ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በንጹህ የመጠጥ ውሃ ተደራሽነት ላይ እንቅፋት መፍጠሩ ተገለጸ። መመለስ ከነበረባቸውም የመለሱት ገንዘብም አንድ ከመቶ በታች መሆኑም ተገልጿል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ በተለይም ለኢትዮጵያ ፕሬሰ ድርጅት እንደገለጹት፤ የውሃ ልማት ፈንድ በሚኒስቴሩ ስር ሲቋቋም የተገኘውን ገንዘብ ከተሞች ተበድረው የመጠጥ ውሃ ግንባታ አከናውነው ለህብረተሰቡ ከሚሰጡት የመጠጥ ውሃ ደግሞ የሚገኘውን ገቢ በመሰብሰብ እዳቸውን የሚከፍሉበትን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ነው።
ብድር የወሰዱ ከተሞች እዳቸውን ሲከፍሉ ደግሞ ሌሎች ውሃ ያላገኙ ከተሞች ገንዘቡን ተበድረው የመጠጥ ውሃ ማልማትን ተደራሽ በማድረግ የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ ያለመ ነው። ይሁንና ክልሎች ከውሃ ልማት ፈንድ የተበደሩትን ገንዘብ ባለፈው በጀት ዓመት መመለስ ከነበረባቸው ውስጥ አምስት ቢሊዮን ለመመለስ ፈቃደኛ አልሆኑም።
እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ ‹‹ይህ አሰራር በአሁኑ ወቅት ትልቅ ፈተና ውስጥ ገብቷል፤ ክልሎችም ገንዘቡ እንዲመለስ እየፈለጉ አይደለም። ክልሎችም ገንዘቡን ሲበደሩ ዋስትና የሚሰጡት የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮችና ፕሬዚዳንቶች ናቸው። ይሁንና በዋስትናቸው ልክ ገንዘቡን እየመለሱ አይደለም›› ብለዋል። የውሃ ፈንድ ልማት ከተመሰረተ ጥቂት ዓመታት ወዲህ 28 ቢሊዮን ብር አልተሰበሰበም። ይህ ገንዘብ ወደሚመለከተው አካል በወቅቱ ባለመመለሱ በስራ ላይ እንቅፋት ፈጥሯል።
ለውሃ ፈንድ የሚውለው ገንዘብ ከዓለም ባንክና ከሌሎች አበዳሪ ተቋማት በብድር መልክ መምጣቱን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ ይህ ገንዘብ ባለመመለሱም አበዳሪዎች ተጨማሪ ገንዘብ ለመስጠትም ፈቃደኛ አይሆኑም። ይህን ብድር ክልሎች ባይመልሱም የፌዴራል መንግሥት ከአበዳሪዎች የወሰደው ስለሆነም የመመለስ ግዴታ አለበት። ይሁንና የከተማ መስተዳድሮች እና ክልሎች ቸልታና በአግባቡ ኃላፊነታቸውን አለመወጣት በመጠጥ ውሃ ተደራሽነት ላይ ሚኒስቴሩ ለሚያደርገው ጥረት ከፍተኛ እክል የሚፈጥር መሆኑን አመልክተዋል። ክልሎች ይህን ገንዘብ ለመመለስ ፈቃደኛ ያልሆኑትም በግዴለሽነት ሲሆን፤ ለአሰራርም በጣም አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸዋል።
የመጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማስፋት በሚደረግ ጥረት ላይ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የመሳሰሉት ችግሮችንም ሀገራዊ ፈተናዎች መሆናቸውን አብራተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ግብዓቶች ከውጭ ሲገቡ በትራንስፖርት ሎጂስቲክስ መዘግየትና የመሳሰሉት አሰራሮች የመጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማሳደግ ለሚደረጉ ጥረቶች ፈተናዎች ናቸው። በእነዚህ ላይ መሰል ችግሮች ሲደማመሩ ደግሞ ችግሩን የሚያወሳስቡ መሆኑን አስገንዝበው፤ ክልሎች ዕዳቸውን እንዲከፍሉ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 4 ቀን 2015 ዓ.ም

See also  "አብዮታዊ ዲሞክራሲ ወይም ሞት!" ብልጽግና እስከመቼ ይሸከማል?

Leave a Reply