ሚሊየነሩ ሜዳ ላይ – ይህ ጉድ የተፈጸመው ዝዋይ በዘረኞች ነው፤ መርጦ አልቃሽ “ሚዲያዎች” እፈሩ

አቶ ኢያሱ ሻንቅሎ ይባላሉ። ትውልድና እድገታቸው ወላይታ ሶዶ ሲሆን ከ1981 ዓ.ም ጀምሮ ግን ኑሯቸውን ባቱ (ዝዋይ) ከተማ ላይ አድርገዋል። በ14 ዓመታቸው ለስራ ወደ ባቱ የሄዱት እኚህ ሰው አደም በተባለ ሻይ ቤት በ30 ብር የወር ደመወዝ ተቀጥረው ነው የስራን ዓለም የተዋወቁት፤ በዚያ ለጋ እድሜያቸው ኑሯቸውን ለማሸነፍ ሲሉ ጋሪ በመግፋት፤ ሊስትሮ በመጥረግ፤ እንዲሁም በብስክሌት ጥገና ስራ ላይ ተሰማርተው ለዓመታት ደፋ ቀና ብለዋል።

ነገር ግን ሰው ከሰራ ያገኛልና አቶ እያሱም በሚሰሯቸው ስራዎች የገቢ አቅማቸው ከፍ ሲል ትዳር መስርተው አራት ልጆችንም አከታትለው በመውለድ ለስራ በመጡባት ባቱ ከተማ ላይ ደስተኛ ሕይወትን መምራት ቀጠሉ።

አቶ እያሱ የስራ ሰው ናቸውና በተለይም ልጆች ከወለዱ በኋላ አቅማቸውን በማጠናከር ገቢያቸውን ለማሳደግ ልጆቻቸውንም በጥሩ ሁኔታ ለማኖር በርካታ ስራዎችን መስራት ቀጠሉ። እንደ እድልም ሆኖ ያሰቡት የሚሳካላቸው የነኩት ሁሉ ፍሬ የሚያፈራላቸው ነበሩና ቀስ በቀስ የገቢ አቅማቸው እያደገ ኪሳቸው ላይም ጥሩ ገንዘብ እየገባ መጣ።

አቶ እያሱ የያዙትን ገንዘብ ቋጥረው ለልጆቻቸው ማረፊያ ይሆን ዘንድ መሬት ገዝተው ቤት ገነቡ፤ ከዚያም ባሻገር ተጨማሪ ለኪራይ የሚሆኑ ቤቶች በመገንባት ተጨማሪ ገቢን ማግኘት ጀመሩ። በዚህ ብቻ አልተወሰኑም፤ ሌሎች አራት ተጨማሪ መሬቶችን ገዝተው የሚያከራዩትን ቤት ቁጥር 58 አደረሱ። ይህ ከፍ ያለ ሞራልን የጨመረላቸው አቶ እያሱ፤ ዕለት ዕለት ሳይታክቱ ይሰራሉ፤ ለሌሎችም የስራ እድል ፈጥረው ሥራቸውን ያሰፋሉ። ደግሞ ሌላ የገቢ አቅማቸውን የሚያሳድግላቸው የስራ ሃሳብ ለማግኘት ይጥራሉ።

የአካባቢው ማህበረሰብም በአቶ ኢያሱ ስራ ወዳድነትና ታታሪነት ይደነቃል። በተለይ ከሊስትሮነት ጀምሮ ባለሃብት እስኪሆኑ ድረስ ያሳለፉትን ውጣውረድ የሚያውቁ ሰዎች እንደ አቶ ኢያሱ ለመሆን ይመኛሉ። አንዳንዶቹም ተሞክሯቸውን በመውሰድ ወደ ንግድ ዓለም የተቀላቀሉም አሉ። አቶ ኢያሱ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ያላቸውን ጥብቅ ቁርኝት ሲገልፁ ‹‹እኔ ደቡብ ልወለድ እንጂ እድገቴም ሆነ አብዛኛውን ህይወቴ ያሳለፍኩት ኦሮሚያ ውስጥ ነው፤ ሃብት ያካበትኩት፤ ቤተሰብ መስርቼ ልጆችም ያፈራሁት እዚሁ ነው። እትብቴ ከተቀበረበት ከወላይታ ሶዶ በላይ የኦሮሞን ባህልና ወግ ነው የማውቀው። ከከተማው ሕዝብ ጋርም እንደ ቤተሰብ የጠነከረ ግንኙነት ነው ያለኝ›› ይላሉ።

አቶ እያሱ ሥራቸው እየሰፋ ሲመጣም ለባለቤታቸው አነስተኛ ሻይ ቤት ከፍተው መተጋገዝ ጀመሩ እሳቸውም 75 ሺ ብር ከኮንስትራክሽን ባንክ ተበድረው ስራቸውን አስፋፉ። ተጨማሪ መሬት ገዙና ቤቶች በመገንባት እያከራዩ ገንዘባቸውን አጠራቀሙ። ከሚያከራይዋቸው ቤቶች በተጨማሪ የሸቀጣ ሸቀጥ ማከፋፈያ፤ የሞተር፣ ባጃጅና ብስክሌት መለዋወጫ እንዲሁም መሸጫ ከፈቱ።

የንግድ ተቋሞቻቸውን ለማስፋትና የገንዘብ አቅማቸውን ለማሳደግ ሲሉም ያሏቸውን አስር መሬቶች 13 ሚሊዮን ብር አስገምተው ከባንክ ሶስት ሚሊዮን ብር ብድር ወሰዱ። እንዳሰቡትም እቅዳቸውን ለማሳካት ሲሉ ደፋ ቀናቸውን ቀጠሉ።

ሰው ሲሰራ ችግር ማጋጠሙ አይቀርምና አቶ እያሱም አገር አማን ብለው ስራቸውን እየሰሩ ባሉበት ሁኔታ ያላሰቡት ነገር አጋጠማቸው። ይኸውም በከተማ በሚገኝ አንድ መጠጥ ቤት ውስጥ በሁለት ሰዎች መካከል የተፈጠረው ፀብ አንደኛው ሰው ይጎዳና ሆስፒታል ይገባል፤ ጉዳዩም በህግ ጥላ ስር እንዲታይ ይደረጋል። ሆኖም ፀቡ በሁለቱ ሰዎች ላይ ብቻ ተወስኖ አልቀረም፤ የተጎጂ ሕይወት ማለፉን ተከትሎ በቅፅበት ችግሩ ሰፋ።

ባላሰቡትና በማያውቁት ነገር ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ነዋሪዎች መካከል ደግሞ አቶ ኢያሱ አንዱ ሆኑ። በዕለቱ ስለተፈፀመው ነገር ሲያስረዱም ‹‹ኅዳር 3 ቀን 2010 ዓ.ም ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ላይ ሀገር ሰላም ነው ብዬ ቤቴ በተቀመጥኩበት የድንጋይ ናዳ ወረደብኝ፤ ይህ ግን እኔ ላይ ብቻ የሆነ አልነበረም» ይላሉ።

ይህ ሁሉ ሲሆን ታዲያ ስለተፈጠረው ጉዳይ ምንም ፍንጭ የሌላቸው አቶ እያሱ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከጥቃት ከመከላከል ውጭ ምንም ማድረግ አልቻሉም ነበር። ግን ደግሞ ቤታቸው ተከራይተው ይኖሩ የነበሩ ሁለት ፖሊሶች ቤት ስለነበሩ ግጭቱን ለማስቆም የበኩላቸውን ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር አልሸሸጉም።

ሁኔታው ግን ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ለከተማዋ ፖሊስ ደወሉ ንብረቴ ከመውደሙ በፊት ደረሱ። ይሁንና የደረሱት ፖሊሶች መከላከል ሳይችሉ በመቅረታቸው ለፌደራል ፖሊስ መደወላቸውን የተናገሩት አቶ ኢያሱ የፌደራል ፖሊሶች ባቱ እስከ ደረሱበት 10 ሰዓት ድረስ ተኩሱ አለማቆሙን ያስረዳሉ።

‹‹……. ቤታችን ከህንፃነት ወደ አመድነት እስኪቀየር ድረስ ሁከቱ አልቆመም ነበር። በመደብሮቹ ላይም ከፍተኛ ውድመት ደረሰ። በዚህም ከአስር ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት አጣሁ›› ይላሉ። አደጋው በደረሰበት ወቅትም የቤተሰባቸውንና የራሳቸውን ነፍስ ለማትረፍ ሲሉ ምንም አይነት ገንዘብም ሆነ ንብረት ሳይዙ በለበሱት ልብስ ብቻ መውጣታቸውን ያስታውሳሉ።

‹‹…..ለ29 ዓመት ባቱ ከተማ ስኖር አንድ ቀን በወንጀል ስሜ ተነስቶ አያውቅም፤ ወህኒ ቤት ገብቼ አላውቅም። ከስራ በስተቀር የማውቀው ነገር የለም። ሆኖም ግለሰቦች በፈጠሩት ጸብ ንብረቴን አጣሁ›› ሲሉ ያብራራሉ። በግላቸውም ከተቃጠሉባቸው ቤቶች በተጨማሪ በርካታ ሞተሮችና ብስክሌቶች እንዲሁም የሸቀጣሸቀጥ ማከፋፈያና የሞተር ብስክሌት መለዋወጫ መደብር በሙሉ የወደመባቸው መሆኑንም አቶ እያሱ ከፍ ባለ ቁጭት ይናገራሉ።

አደጋው ሲከሰት ያልጠበቅነው በመሆኑ ራሳችንን ለማትረፍ በለበስነው ልብስ ነው የወጣነው። በዚያ ጊዜ ውስጥ ግን ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆነው ንብረቴ ወድሟል።

በሁለት ግለሰቦች ፀብ በተስፋፋው ግጭት ምክንያት ለ29 ዓመታት ለፍተው ያፈሩት ንብረት በሙሉ በአንድ ጀምበር ማጣታቸው ከፍተኛ የሆነ የልብ ስብራት አድርሶባቸዋል።

አቶ እያሱ የባንክ ሶስት ሚሊዮን ብር ተበዳሪ ናቸው፤ ለዚህ ብድር ዋስትና ደግሞ ያስያዙት ቤታቸውን ነበር፤ ነገር ግን በደረሰባቸው ችግር ምክንያት የክፍያ ጊዜያቸው እንዲራዘም ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት እንዲሁም ሰላም ሚኒስቴርና ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የትብብር ደብዳቤ ለባንኩ የጻፉላቸው ቢሆንም ባንኩ ችግራቸውን መረዳት ባለመፈለጉ ብቻ ቤታቸውን በዝግ ጨረታ እንደሸጠባቸው ይገልጽሉ። ‹‹…… መክፈል ባለመቻሌ ባንኩ የራሱን እርምጃ ወሰደ ቤቴም በግፍ እንዲሸጥ ሆነ ›› በማለት በሐዘን ተውጠው ይናገራሉ።

በሌላ በኩል ከእሳት ከተረፉት ቤቶቻቸው የተገኘውን አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ የቤት ኪራይ ባንኩ ገቢ አድርጎታል ‹‹ ቤቴ ሲሸጥም ጨረታው የወጣው ደግሞ የእኔ ፊርማ በሌለበት ሲሆን አራት ሚሊዮን ብር ሊሸጥ ሲገባው በአንድ ሚሊዮን አራት መቶ ሺ ብር ነው የተሸጠው። ሁለት ሚሊዮን የሚሸጠው ቦታ ደግሞ በ980 ሺ ብር ተሸጠ››። ይህ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ግን ሊመለስላቸው የሚገባ ቀሪ ገንዘብ እንዳልተሰጣቸው ይናገራሉ።

‹‹አሁን ላይ ምንም አይነት የገቢ ምንጭ የለኝም፤ አንዳንድ ጓደኞቼን እየለመንኩ ነው 18 ቤተሰቤን እያስተዳደርኩ ያለሁት። አሁን ባለው የኑሮ ውድነት አይደለም 18 ሰው አንድ ሰው እንኳን ራሱን አስችሎ ማኖር ከባድ ነው፤ ሌላው ይቅርና በፍርድ ቤትና አንዳንድ የፌደራል ተቋማት ጠርተውኝ አዲስ አበባ የምሄድበት ገንዘብ አጥቼ ጉዳዬ የተስተጓጎለበት አጋጣሚ ብዙ ነው›› ሲሉም የችግራቸውን መጠን ከፍ ባለ ሀዘን ውስጥ ሆነው ይናገራሉ።

‹‹……. ትናንት ብዙዎችን ስደግፍ እንዳልኖርኩኝ ዛሬ የሰው እጅ እያዩ መኖር በጣም ከብዶኛል። አሁን ላይ እኔም ሆንኩ ቤተሰቦቼ ጎዳና ወጥተናል። አዲስ አበባም ለጉዳዬ ስሄድ ለሆቴል መክፈል ስለማልችል መገናኛ የሚገኝ ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው የማድረው››። አሁን ላይ እጅግ ተስፋ በመቁረጣቸው ምክንያት በተደጋጋሚ ራሳቸውን ለማጥፋት የሞከሩበት አጋጣሚ እንዳለ አቶ እያሱ እንባ እየተናነቃቸው ይናገራሉ።

በተለይም የእሳቸው ባልሆነ ጥፋት ለዘመናት ያፈሩት ሃብትና ንብረት በሰዓታት ልዩነት አመድ ሆኗል። ከልጅነታቸው ጀምሮ ለፍተው ያካባቱት ሁሉ ዛሬ በእጃቸው የለም። ለብዙዎች ይተርፉ የነበሩት ባለሃብትም ዛሬ ሜዳ ላይ ወድቀዋል።

‹‹……ትናንት 58 ቤት ሳከራይ ኖሬ ዛሬ አንዲት ደሳሳ ጎጆ አጥቼ ከባድ ችግር ውስጥ ነው ያለሁት፤ ሰርቶ ያወቀ ሰው አግኝቶ ማጣት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ይረዳል። ለአቅም አዳም ያልደረሱ ልጆቼን የማበላው አጥቼ ግራ ገብቶኛል። ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር አንድ ሃዋሳ የማውቃቸው ሰው በነፃ ቤታቸው አኑረውኛል። አሁን ላይ ግን ከነቤተሰቤ ጎዳና ወጥቻለሁ›› ይላሉ። በዚህ ችግር ምክንያትም በተለይ የመጀመሪያ ልጃቸውና ባለቤታቸው ለበሽታ መዳረጋቸውን እነሱን ለማሳከም ባለመቻላቸው ተጨማሪ ጭንቀት ፈጥሮባቸዋል። ስለዚህ ‹‹መንግስት የደረሰብኝን ተገንዝቦ መፍትሔ እንዲሰጠኝ እፈልጋለሁ›› ሲሉ ነው አቶ እያሱ የጠየቁት።

ሀገርም ሆነ ግለሰብ የሚጠቀሙት ከሰላም ብቻ ነው። ሰላም ሲሆን ሀገር ትበለጽጋለች፤ ዜጎች ሰርተው ሃብት ያፈራሉ፤ ያፈሩትንም ሃብት በአግባቡ መጠቀም ይችላሉ። ሰላም ከሌለ ግን በሃብትም ሆነ በንብረት መመካት ከንቱ ነው። ለዚህም ነው ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው የሚባለው። አቶ ኢያሱ ሻንቅሎ አሳዛኝ አጋጣሚም የሚያስተምረን ይህንኑ ነው። ስለዚህም በማንኛውም ጊዜና ቦታ ሁሉ ለሰላም ትኩረት እንስጥ።

ማህሌት አብዱል

Leave a Reply