በአዲስ አበባ ከሌብነት ጋር በተያያዘ 215 አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ደላሎች ታሰሩ

የፀረ-ሙስና እና ሥነ- ምግባር ኮሚሽን በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ሥራ ከጀመረ አንስቶ፤ በከተማ ደረጃ የፀረ ሙስና ንቅናቄ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ከሕብረተሰቡ ጥቆማ በመቀበል 215 አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ደላሎች በሕግ ቁጥጥር ሥር ሆነው ጉዳያቸው በፍትህ ሂደት ላይ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።

3ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን በከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽ/ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ በመካሄድ ላይ ይገኛል።በጉባኤው የከተማ አስተዳደሩን የ2015፤ የመጀመሪያ 6 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የፀረ-ሌብነት ትግልን በማጠናከር፣ የሕግ በላይነት የማስከበር፣ የተጠያቂነት ለማስፈን በሕዝባዊ ንቅናቄ የተደገፉ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህም በ6 ወራት ውስጥ 215 አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ደላሎች በሕግ ቁጥጥር ሥር ሆነው ጉዳያቸው በፍትህ ሂደት ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ከንቲባዋ፤ የካ ክ/ከተማ 40፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ 42፣ ለሚ ኩራ 48፣ ልደታ 26፣ አቃቂ ቃሊቲ 33፣ በማዕከልና ሴክተሮች 26 የሚሆኑ በሕግ ተጠያቂ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከማዕከል እስከ ወረዳ ባሉ ተቋማት 3 ሺሕ 584 አመራርና ሰራተኞች በተለያዩ የዲሲፕሊን ግድፈቶች አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው መደረጉን ከንቲባዋ አብራርተዋል።

ከንቲባዋ በሪፖርታቸው በ6 ወራቱ የምርት አቅርቦትን በማሳደግ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ዉድነትን ለማረጋጋት የተለያዩ ሥራዎች መሰራታቸውን በመግለጽ፤ በዚህም 170 ሺሕ 128 የሰብል ምርት በገበያ ማዕከላት ትስስር መፍጠር መቻሉን እንዲሁም፤ “የእሁድ ገበያ (Sunday Market) በሁሉም ክ/ከተሞች በ137 የገበያ መዳረሻዎች በማስፋፋት የግብርና ምርቶች ከአርሶ አደሩ ወደ ተጠቃሚው በቀጥታ እንዲደርሱ በማድረግ ሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችን እንዲያገኝ መደረጉን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የመሠረታዊ ፍጆታ ሸቀጦች አቅርቦት ለሕብረትሰቡ በፍትሃዊነት ተደራሽ ከማድረግ አንፃር 272 ሺሕ 777 ስኳር መሰራጨት መቻሉን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፤ በ6 ወራት ውስጥ 10.9 ሚሊዮን ሊትር ፓልም ዘይት መሰራጨቱንና 194 ሚሊዮን የሸገር ዳቦ በሸገር ዳቦ በመሽጫ ሱቆች ማሰራጨት መቻሉን ተንግረዋል። ከሸገር የዳቦ ፋብሪካ በተጨማሪም የተገነቡት የዳቦ ፋብሪካዎች ቁጥር 25 ማድረስ መቻሉን አስረድተዋል።

See also  የአማራ ክልል የነብሮ ልዩ ሃይል የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽንን መርጦ ስልጠና ጀመረ

የከተማ አስተዳደሩ በመደበው 1.4 ቢሊዮን የተዘዋዋሪ ብድር በመጠቀም በድምሩ 356 ሺሕ 761 ኩንታል ጤፍ በሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራት በኩል በማቅረብ ገበያ የማረጋጋት ሥራ መሰራቱን የተናገሩት ከንቲባዋ፤ አክለውም ለትምህርት ቤት ምገባ የወቅቱን ኑሮ ውድነት መነሻ በማድረግ በዓመት ተጨማሪ 54ዐ ሚሊዮን ብር በመመደብ የመጋቢ እናቶችን ጫና የመቀነስ እና የተማሪዎችን ምገባ የተሻለ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።ጉባኤው ዛሬን ጨምሮ ለኹለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ በዛሬው ውሎው በቀረበው የስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ይወያያል። በነገው ዕለትም ምክር ቤቱ የተለያዩ ረቂቅ ደንቦችና አዋጆች ላይ ተወያይቶ እንደሚያፀድቅ እንደሚጠበቅ የአዲስ አበባ ከተማ መገናኛ አመልክቷሎል።

Leave a Reply