ቻይና በኢትዮጵያ የቪዛ መጠየቂያ ማዕከል መክፈቷን ይፋ አደረገች

የቻይና ቪዛ መጠየቂያ ማዕከል በአዲስ አበባ መከፈቱን በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ አስታወቀ።

በመክፈቻው ላይ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዛኦ ዚያን፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የእስያና ፓስፊክ አገራት ዳይሬክቶሬት የቻይና ዳይሬክተር ሳሙኤል ፍጹም-ብርሃንን ጨምሮ ሌሎች የሁለቱ አገራት ተወካዮች ተገኝተዋል።

ማዕከሉ በአዲስ አበባ መከፈቱ የቪዛ አገልግሎት አሰጣጡን በማሳለጥ የሁለቱን አገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው አምባሳደር ዣኦ ገልጸዋል።

አገልግሎቱም የሁለቱን አገራት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በማሳደግ ወደ ቻይና መጓዝ ለሚፈልጉ ዜጎች በአጭር ጊዜ ግልጽ መረጃ እንዲያገኙ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በቅርቡ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ያደረጉት ይፋዊ የስራ ጉብኝት የአገራቱ ሁለንተናዊ አጋርነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገት እያሳየ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል።

የኢትዮ-ቻይና ዲፕሎማሲ በኢኮኖሚ፣ በሕዝብ ለሕዝብ፣ በባህል እና ሌሎች ዘርፎች ትብብር እያደገ መምጣቱን ነው አምባሳደር ዣኦ የገለጹት።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የእስያ እና ፓስፊክ አገራት ዳይሬክቶሬት የቻይና ዳይሬክተር ሳሙኤል ፍጹም-ብርሃን፤ ኢትዮጵያ እና ቻይና ዘመናትን የተሻገረ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው አገራት ናቸው ብለዋል።

የቻይና ቪዛ መጠየቂያ ማዕከሉ በመዲናዋ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ-02 በሚገኘው ድሪም ታዎር ህንፃ ላይ ይገኛል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና የተለያዩ ከተሞች እያደረገ ያለው የቀጥታ በረራም ቻይና ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ትብብር እንዲጎለብት አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

See also  ደቡብ ወሎ የሞርታር ተተኳሽ የደበቀው ግለሰብ እጅ ከፍንጅ ተያዘ

Leave a Reply