ኦሮሚያ- የሕዝብ ተመራጮች ኦነግ ተደራዳሪዎቹን በስም ይፋ እንዲያደርግና ራሱን እንዲገልጥ ጠየቁ

  • በኦሮሚያ እልቂትና የሰላማዊ ነዋሪዎች ስቃይ ሊቆም እንደሚገባ በተደጋጋሚ ህዝብ እየወተወተ ነው፤ ሁሉም ወገኖች እልህና የግል ፍላጎታቸውን ለህዝብ ሲሉ ወደሁዋላ በማድርግ ወደ ሰላም መድረክ ሊመጡ ይገባል፤ ህዝብ ስቃይ ጠንቶበታል። ዘረፋና አፈና ሰልችቶታል፤ የየዕለቱ ለቅሶና ዋይታ ሊያበቃ ግድ ነው

የተለያዩ ባለቤቶች ያሉት ኦነግ የትጥቅ ትግል እያደረገ ያለውን ክፍል ወገን ለማወቅ አዳጋች አድርጎታል። ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር የሚለው ታጣቂ ሃይል ከየትኛው ኦነግ አመራር ጋር እንደሚገናኝና እንደሚሰራ ግልጽ ባለመሆኑ ይመስላል ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተወከሉ እንደራሴዎች ጥያቄውን ያቀረቡት። በኦነግ ስም የተለያዩ ታጣቂዎች፣ ሌቦችና ህገወጥ ተግባር የሚፈጽሙ ሃይላት መስፋፋታቸው ስጋት እንደሆነም ተወካዮቹ ገልጸዋል።

በኦሮሞሚያ ከመንግስት ሃይል ጋር እንደወትሮው ባይሆንም አንዳንድ አካባቢዎች የሚዋጋው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሃይል ወደ ሰላም እንዲመጣና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የአፍሪካ ህብረት ጣልቃ እንዲገባ ተወካዮቹ ደብዳቤ ማስገባታቸውን የገለጹት ለጀርመን ድምጽ አማርኛ ስርጭት ክፍል ነው።

የአፍሪካ ህብረት የሰሜኑ ጦርነት እንዲያበቃ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ገልጸው ይህንኑ በኦሮሚያም እንዲያደርገው በማሰብ ደብዳቤ ማስገባታቸውን የገለጹት የህዝብ ተወካዮች፣ ስለ ሰላም ንግግሩ ይዘትና ዝርዝር ጉዳይ ያሉት ነገር የለም።

የክልሉ መሪ አቶ ሽመልስ አብዲሳ በይፋ ከወር በፊት ያደረጉትን የሰላም ጥሪና ከኦነግ በኩልም የተሰጠውን አዎንታዊ ምላሽ እንደሚያደንቁ ያስታወቁት የህዝብ ወኪሎች ጉዳዩ ከጥሪና ጥሪውን ከመቀበል አለማለፉን አመልክተዋል። በሁለቱም ወገን ፈቃደኝነት ካለ ለምን ላለፉት አንድ ወራት ንግግር ሊጀመር እንዳልቻለ በይፋ አልተናገሩም።

ኢትዮ12 ንግግር መጀመሩን ጠቃሳ መዘገቧ ይታወሳል። ንግግሩ አቶ ሽመልስ በይፋ ጥሪ ከማቅረባቸው በፊት የጀመረ ሲሆን ችግር የሆነው የኦሮሞ ነጻ አውጪ ጦር ነኝ የሚለውን አካል የሚወክሉት ወገኖችና በተመሳሳይ ራሱ የኦሮሞ ነጻ አውጪ ሰራዊት የሚባለው ክፍል ሲያገኘው እርምጃ ይወስድበታል የሚባለው ሸኔ ጉዳይ አስቸጋሪ በመሆኑ ነው። የሕዝብ ወኪል ነን ያሉት ወገኖች ይህን መረጃ ቢያውቁም በይፋ ሳይገልጹ ” በኦነግ ሰራዊት ስም ሌቦችና …” ሲሉ ነው የገለጹት።

ለብልጽግናና የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ አባሪ ተደርጎ የተሰራጨው ደብዳቤ ሰላም በኦሮሚያ እንዲሰፍን ፍላጎት ያለውና ጫና የሚፈጥር እንደሆነ ተገልጿል። ለጀርመን ድምጽ «እንደ ህዝብ ተወካይ በኦሮሚያ ውስጥ የሚካሄደው ጦርነት ያሳስበናል» ያሉት 12 ተመራጮች አፍሪካ ህብረት እንዲያሸማግል ሲጠይቁ፣ የፌደራል መንግስትም ጣልቃ እንዲገባ አሳስበዋል።

See also  ታከለ ኡማን ጨምሮ አራት ሚኒስትሮች ከሃላፊነታቸው ተነሱ

በደርግም ሆነ በትህነግ የስልጣን ዘመን የኦነግ ሰራዊት ነጻ መሬት የነበረው አካባቢ በመከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር መዋሉን የመከላከያ መገናኛ ተቋሞች ማስታወቃቸው ይታወሳል። ይህም ቢሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው ግጭት ሊቆምና ክልሉ ወደ ልማት እንዲሸጋገር በህዝብ ዘንድ ሰፊ ግፊት አለ። በተለይም ወለጋ ግጭቱ ክፉኛ የጎዳው በመሆኑ አሁን ላይ ተሰላችተዋል። ለዚህም ይመስላል የህዝብ ወኪሎቹ ታጣቂዎቹም ቢሆኑ የህዝብን ስቃይ ግምት ውስጥ በማስገባት ወደ ድርድር እንዲመጡ ያሰሰቡት። የሚደራደሩ አካላትንም በይፋ እንዲሰይሙ ያስታወቁት።

መንግስት ሸኔ የሚለው አካል በላቤቱ በግልጽ የማይታወቅ፣ መሪው ፊትለፊት የማይወጣ፣ ለምን ዓላማና ግብ እንደሚታገል ያልገለጸ፣ ለድርድር ቢፈልጉት አድራሻ የሌለው መሆኑ ታላቅ ተግዳሮች እንደሆነበት ማስታወቁ አይዘነጋም። ከስራ የጀርመን ድምጽ ዘገባ ሙሉ በሙሉ ሰፍሯል።

በኦሮሚያ ውስጥ በመንግሥት እና ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ጦርነት ዘላቂና ሰላማዊ እልባት እንዲያገኝ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ ከኦሮሚያ ክልል ከተለያዩ አከባቢዎች የተወከሉ የህዝብ እንደራሴዎች ዛሬ ለአፍሪካ ሕብረት ደብዳቤ ማስገባታቸውን አሳወቁ። ይህ ደብዳቤም በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ሰላም እንዲወርድ ጉልህ ሚና የተወጣው የአፍሪካ ሕብረት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ለሚታየው አለመረጋጋትም ተመሳሳይ የአሸማጋይነት ሚና እንዲጫወት የሚጠይቅ ነው። 

«እንደ ህዝብ ተወካይ በኦሮሚያ ውስጥ የሚካሄደው ጦርነት ያሳስበናል» ያሉት የህዝብ እንደራሴዎቹ ፍላጎታቸው በክልሉም ሆነ በመላ አገሪቱ እርቅና ሰላም እንዲመጣ መትጋት ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና ከኦሮሚያ የተወከሉ እንደራሴዎች አስተባባሪ ረዳት ፕሮፌሰር ብዙዓየሁ ደገፋ በተለይም ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት 12 የሚሆኑት ተወካዮች ዛሬ ያሰራጩት ደብዳቤ ከህብረቱ በተጨማሪ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት፣ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለገዢው ብልጽግና ፓርቲም ተዳርሷል።

ከዚህም በፊት ይህን ጥያቄ አንስተው በኦሮሚያ ውስጥ እርቅ እንዲወርድ እንሻለን ያሉት የህዝብ እንደራሴዎቹ ከአንድ ወር በፊት በኦሮሚያ ክልል በኩል ለታጣቂዎች የቀረበው የሰላም ጥሪም እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል። ይሁንና በክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የቀረበው ጥሪ ከ30 ቀናት በኋላም ምንም ወደሚጨበጥ ተግባራዊ ወደ ሆነ ሥራ አለመሸጋገሩ የተጣለው ተስፋ ላይ ስጋትን ፈጥሯል ብለዋል። ከምዕራብ ወለጋ ተወክለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት እና የዚህ ሃሳብ አቀንቃኝ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ቤቴል መልካሙ ይሰኛሉ። «የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ይህን የእርቅ ጥሪ በማቅረቡ አመስግነናል። ይሁንና ጥሪው ከተላለፈ 30 ቀናት ብያልፉም አንድም የንግግሩ ቅድመ ሁኔታ አልተፈፀመም። አንድም የእርቅ ማስጀመር ምልክት ለህዝብ ሳይገለጽም ቀኑ ነጉዷል። አሁንም ይህን ጉዳይ የክልሉ መንግሥት ላይ ብቻ መተው መፍትሄ እንዳልሆነና የፌዴራሉ መንግሥት የሰሜኑን ችግር እንደፈታው ይህንንም ትኩረት ሰጥቶ እንዲፈታው ነው የምንጠይቀው። በኦሮሚያ ውስጥ ለአራት ዓመታት የቀጠለው ግድያና ውድመት ከዚህ በላይ እንዲቀጥል መፈቀድ የለበትም። ህዝባችን እየተሰቃየ እኛ ሰላም ማግኘት አንችልም ብለን ነው ይህን ሃሳብ ያነሳነው።» ብለዋል።

See also  ኢትዮጵያና ኤርትራ ምሽግ ተቀያየሩ፤ ጌታቸው ረዳ አሁንም [እየፈሰሱ] ነው

የአፍሪቃ ኅብረት ሕንጻ አዲስ አበባ

እንደራሴዎቹ አክለውም፡ «ከጥሪው በኋላ ቀጥሎ መታየት የነበረባቸውን ሂደቶች አላስተዋልንም። የትነው የሚወያዩት፣ ሁለቱንም የሚወክሉ ተወካዮችስ ተመርጠዋል ወይ? የሚሉትና ሌሎችም መኖር ያለባቸው ሂደቶች ለህዝቡ ይፋ ሆነው ወደ ተግባር መገባት አለበት ብለን ነው በመንግሥት በኩል ስምንት ሰዎች ቢካተቱ ብለን ምክረ ሃሳብ ያቀረብነው። ሂደቱን ደግሞ አፍሪቃ ኅብረት ቢያሳልጠው ብለን ነው የያዝነው» ይላሉ።

በኦሮሚያ ውስጥ መንግሥትን የሚፋለመው እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራውና መንግሥት ሸነ በሚል በሽብርትነት የፈረጀው ታጣቂ ቡድን በፊናው ከኦሮሚያ ክልል ከዚህ በፊት የቀረበለትን የሰላም ጥሪ በአዎንታዊነት መቀበሉ መልካም ነው ያሉት የህዝብ እንደራሴዎቹ፤ ታጣቂዎቹም እየደረሰ ያለውን የህዝብ እልቂትና ቀውስ ተመልከተው ተወካዮቻቸውን በመሰየም ወደ ሰላማዊ ድርድሩ እንዲገቡ ጠይቀዋል። «በነሱ ምክንያት ህዝባችን መሰቃየቱ ይበቃል። እነሱን ተገን አድርገው በክልሉ የተሰማሩ ሌቦችና ገዳዮች ብዙ ናቸው። በመሆኑንም እነሱም የመወያያ ቦታና ተወካዮቻቸውን እንዲያዘጋጁ ነው የጠየቅነው። የአፍሪካ ኅብረትም ቢሆን የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ባየበት ዓይን ይህንንም ማየት አለበት፤ የኦሮሚያውን ግጭት እስካሁንም አሳንሶ ማየቱ አሳዝኖናል። ጉዳዩን የአንድ ክልል አድርጎ ከመተው ሁለቱንም ወገን ቢያወያይ መፍትሄ ይመጣ ይሆናል» ብለዋል። ዶይቼ ቬለ ስለጉዳዩ ከአፍሪካ ኅብረት፣ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና የፓርቲ ጽሕፈት ቤት ማረጋገጫ እና ተጨማሪ አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለዛሬ አልሰመረም።

Leave a Reply