Site icon ETHIOREVIEW

በእውሸት “ታሰሩ፣ታፈኑ” በሚል ስማቸው በሚዲያዎች የተሰራጨው ስድስት ወጣቶች የፍቅር ግንኙነት መስርተው ተገኙ

በአንድ አካባቢ የሚኖሩ 7 ታዳጊዎች እንደጠፉና እንደታገቱ ተደርጎ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እና ማህበራዊ ሚዲያዎች እየተሰራጨ ያለው መረጃ እውነትነት የጎደለውና የተዛባ ስለመሆኑ ማረጋገጡን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡ ታዳጊዎቹ በአሁኑ ወቅት በፖሊስ ስር እንደሚገኙም ጨምሮ ገልጿል፡፡

አራት ወንድ እና ሦስት ታዳጊ ሴቶች በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 መካኒሳ ቆሬ አካባቢ ከሚገኘው የወላጆቻቸው መኖሪያ ቤት እንደጠፉ እና ታግተዋል በሚል በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እና ማህበራዊ ሚዲያዎች የተሰራጨው መረጃ ትክክል አለመሆኑን በማስረጃና ታዳፊዎቹን በመያዝ ፖሊስ ዜናውን “ቅጥፈት” ብሎታል።

ታዳጊዎቹ ለመጥፋት በማሰብ ከወላጆቻቸው መኖሪያ ቤት ልብሶቻቸውን ይዘው እንደወጡ እና በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከቤተሰቦቻቸው ተነጥለው መኖር እንደሚፈልጉ የገለፁ ሲሆን፣ በልመና ተግባር ላይ ተሰማርተው ባገኙት ገንዘብ የተወሰኑ የቤት ቁሳቁስ በማሟላት ሰባቱም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ቦታው ቡልቡላ አካባቢ በ1ሺ 800 ብር መኖሪያ ቤት ተከራይተው ሦስቱ ወንዶችና ሦስቱ ሴቶች የፍቅር ግንኙነት በመመስረት በጋራ እየኖሩ እንደሚገኙ ከሰጡት ቃል መረዳት ተችሏል ነው ያለው፡፡

የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባትና ከተለያዩ ቦታዎች መረጃ በማሰባሰብ ባደረገው ክትትል ያሉበትን ቦታ እና ሁኔታ ማወቅ እንደተቻለ ያስታወሰው የአዲስ አበባ ፖሊስ፤ ታዳጊዎቹ የስነ-አእምሮ እና ተያያዥ የጤና ምርመራ እንዲያገኙ እንዲሁም ማህበራዊ ችግራቸው ሊፈታ በሚችልበት ሁኔታ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ይሁንና አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን እና ማህበራዊ ሚዲያዎች መረጃን ስላገኙ ብቻ የሚያስከትለውን አሉታዊ ጫና ታሳቢ ሳያደርጉ ዜናውን ማሰራጨታቸው በህብረተሰቡ የእለት ከእለት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና የሚያስከትል መሆኑን ግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚጠበቅባቸው ሊገነዘቡ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል፡፡

Exit mobile version