ከዘጠና አንድ ሚሊዮን ብር በላይ ዘርፈዋል በተባሉ 85 ሰዎች ላይ ክስ መሰረተ

አርሶ አደር ባልሆኑ 30 ግለሰቦች ስም 13,990 ካሬ ሜትር ቦታ በመውሰድና ከዚሁ ይዞታ ላይ በልማት ምክኒያት እንደተነሱ በማስመሰል በሀሰት ከ33 ሚሊየን ብር በላይ ካሳና የሊዝ ግምቱ ከ58 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ምትክ ቦታ በወሰዱና እንዲወሰድ አድርገዋል በተባሉ 85 ግለሰቦች ላይ ክስ መመስረቱ ተገለጸ

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዐቃቤ ህግ ከመንግስት በህገ-ወጥ መንገድ ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ እንዲሁም የሊዝ ግምቱ ከ58 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ምትክ ቦታ በወሰዱና እንዲወሰድ አድርገዋል በተባሉ በ39 የየካ ክ/ከተማ መሬት አስተዳደር ሰራተኞችና በ15 የአርሶ አደር ኮሚቴዎች እንዲሁም ተጠቃሚ በሆኑት በ30 ግለሰቦች በአጠቃላይ በ85 ግለሰቦች ላይ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ የሙስና ወንጀል ችሎት ሥልጣንን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱን የዳይሬክቶሬቱ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል የሆኑት አቶ ዘላለም ፍቃዱ ገለጹ፡፡

ተከሳሾች በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1) (ሀ)፣33 እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 (1) (ሀ) (ለ) እና (2) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ወንጀሉን ፈጽመዋል በሚል ክስ እንደተመሰረተ አቶ ዘላለም ተናግረዋል፡፡

እንደ ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራሉ ገለጻ 39ኙ የየካ ክ/ከተማ መሬት አስተዳደር ሰራተኞች በተለያየ የስራ ሃላፊነት ላይ፤ እንዲሁም 15ቱ ተከሳሾች የአርሶ አደር ኮሚቴ አባላት ሆነው ሲሰሩ በልማት ምክንያት ለሚነሱ ባለይዞታዎች የሚሰጥ የካሳና ምትክ መሬት አሰጣጥ ሂደትን ተገን በማድረግ አርሶ አደር ያልሆኑ በልማት ምክንያትም ከይዞታቸው ያልተነሱ 30 ለሆኑት ተከሳሽ ግለሰቦች አርሶ አደር እንደሆኑና በልማት ምክንያት እንደተነሱ በማስመሰል በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ ዋጋ ሊያወጡ በሚችሉ በቸርችል ጎዳና፣ በመገናኛና ካራ ኤሎ አካባቢዎች ላይ የሊዝ ዋጋ ግምቱ ከ58ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን መሬት በህገ-ወጥ መንገድ በምትክነት እንዲወስዱ በተቀናጀ አካሔድ መስራታቸውን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ይላሉ ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራሉ የአዲስ አበባ ውሀና ፍሳሽ ባለስልጣን ከ2010 ዓ/ም እስከ 2014 ዓ/ም ድረስ በሰራው የለገዳዲ ፌዝ 2 የውሀ ልማት ፕሮጀክት ምክንያት የልማት ተነሺዎችን እያስተናገደ በነበረበት ወቅት ቀኑ እና ወሩ በውል ባልታወቀ በ2012 ዓ/ም እና 2013 ዓ/ም ላይ የአርሶ አደር ኮሚቴዎች የነበሩት 15ቱ ተከሳሾች ለ31ዱ ተከሳሽ ተጠቃሚ ግለሰቦች የአካባቢው ነዋሪና አርሶ አደር ባልሆኑበት አግባብ አርሶ አደር ናቸው በሚል ሀሰተኛ ቃለ-ጉባኤ በማቅረብ፣ ከየካ ክ/ከተማ መሬት አስተዳደር ሰራተኞች ጋር በመሆን ለህዝብ ጥቅም ሲባል በሚለቀቅ መሬት ላይ ለሰፈረ ንብረት ስለሚከፈል ካሳና ምትክ ቦታ አሰጣጥ በተሻሻለው የአፈጻጸም መመሪያ መሰረት አግባብ ባለው አካል ሳይፈቀድ እንዲሁም ሌሎች እነዚህን ተግባራት ለመከወን የወጡትን መመሪያዎች በመጣስ ወደ ቦታው ወርደው በእርግጥም በልማቱ ምክንያት ከይዞታቸው የሚነሱና የሚፈርስ ቤት ያላቸው መሆኑን ሳያረጋግጡ እና መሟላት ያሉባቸው ሁኔታዎች በአግባቡ ባልተሟሉበት ሁኔታ ለ31ዱ ተጠቃሚ ተከሳሽ ግለሰቦች በሌሎች ሰዎች ይዞታ ላይ በህገ-ወጥ መልኩ የይዞታ ማህደር ተደራጅቶ መብት ከተፈጠረላቸው ይዞታዎች ላይ በልማቱ ምክንያት እንደተነሱ በማስመሰል ህገ-ወጥ የካሳ ማህደሮችን የማደራጀት ስራ በመቀናጀት መስራታቸውን ገልጸዋል፡፡

See also  መንግስት ትግራይን ሊቆጣጠር እንደሚችል ህግን ተንተርሶ ይፋ አደረገ፤ አሜሪካ የተድበሰበሰ መግለጫ ሰጠች

በአጠቃላይ የየካ ክፍለ ከተማ የመሬት አስተዳደር ሰራተኞችና የአርሶ አደር ኮሚቴዎቹ 30 ለሆኑት ተጠቃሚ ግለሰቦች በተጭበረበረ መልኩ በ13,990 (አስራ ሶስት ሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና) ካሬ ሜትር መሬት ላይ ህገ-ወጥ መብት በመፍጠርና የልማት ተነሽ እንደሆኑ በማስመሰል የካሳ ማህደሮችን አደራጅተው የህዝብና የመንግስት ሀብት የሆነውን በአዲስ አበባ ከተማ ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች አጠቃላይ የሊዝ ዋጋ ግምቱ 58,601,735 ብር የሚያወጣ ቦታ በህገ-ወጥ መንገድ እንዲወስዱ እና 33,013,572.00 (ሰላሳ ሶስት ሚልየን አስራ ሶስት ሽህ አምስት መቶ ሰባ ሁለት) ብር የካሳ ገንዘብ እንዲሰራ በማድረጋቸው ሁሉም ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት ሥልጣንን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል መከሰሳቸውን ምክትል ዳይሬክተር ጀነራሉ ተናግረዋል።

ሌሎች ተጠርጣሪዎችን በተመለከተም ምርምራዉ እንደቀጠለ መሆኑን አቶ ዘላለም በመግለጫቸው ላይ አካተው ጠቁመዋል፡፡

ጉዳዩን የተመለከተው ችሎትም የቀረቡትን ተከሳሾች የክስ መቃወሚያ ለመስማት ለመጋቢት 27 ቀን 2015 ዓ.ም ቀጠሮ የያዘ ሲሆን ፖሊስ ያልቀረቡትን ተከሳሾች እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

ፍትህ ሚኒስቴር

All reactions:

8383

Leave a Reply