ለገበያ ሊቀርብ የተዘጋጀ ንፅህናውን ያልጠበቀ በርካታ ቴምር በግለሰብ ግቢ ውስጥ ተከማችቶ መገኘቱን ፖሊስ አስታወቀ

ለገበያ ሊቀርብ የተዘጋጀ ንፅህናውን ያልጠበቀና የተበላሸ በርካታ ቴምር በግለሰብ መኖሪያ ግቢ ውስጥ ተከማችቶ መገኘቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ 2 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራ ይገኛል።

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ/ም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ቦታው ታይዋን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ የግለሰብ መኖሪያ ግቢ ውስጥ ነው።

ግለሰቦቹ በመኖሪያ ግቢያቸው በሚገኝ መጋዘን ውስጥ የተበላሸና በህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል በርካታ ቴምር ንፅህና በጎደለው ሁኔታ አስቀምጠው ለአትራፊ ነጋዴዎች በፌስታል አሽገው የ92 ሺህ ብር ከሸጡላቸው በኋላ ቴምሩ የተበላሸ መሆኑን የተገነዘቡት ገዢዎቹ ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ መሰረት ሊያዙ ችለዋል፡፡

መረጃው የደረሰው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የእፎይታ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ከፍርድ ቤት የመበርበሪያ ትዕዛዝ በማወጣት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በተጠርጣሪዎቹ መኖሪያ ግቢ በሚገኘው መጋዘን ውስጥ ባደረገው ፍተሻ መጥፎ ጠረን ያለው እና የተበላሸ በርካታ ቴምር ተከማችቶ መገኘቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል።

የወረዳ 10 አስተዳደር የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀብቱ መካ በበኩላቸው በቁጥጥር ስር የዋለው ቴምር ወደ ህብረተሰቡ ቢሰራጭ በጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ተናግረው ከተጠርጣሪዎቹ የገዙትን የተበላሸ ቴምር ለህዝብ ሳይሸጡ እና የግል ጥቅም ሳያጓጓቸው ለሰዎች ጤና በማሰብ ለፖሊስ ጥቆማ መስጠታቸው ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል፡፡

በቁጥጥር ስር በዋሉት ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝ የጠቀሰው የአዲስ አበባ ፖሊስ፤ ጊዜና ወቅትን እየጠበቁ ህገወጥ ተግባር የሚፈፅሙ ነጋዴዎችም ሆኑ ሌሎች ግለሰቦች ከህግ ተጠያቂነት እንደማያመልጡ ተገንዝበው ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

See also  በዓለም ባንክና በኢትዮጵያ መንግሥት የሚተገበር የ550 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ዛሬ በይፋ ይጀመራል

Leave a Reply