ደኅንነትና ብሔራዊ ባንክ ህገወጥ የውጭ ምንዛሪ ተዋናዮች ላይ እርምጃ እንደሚወሰዱ አስታወቁ

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በህገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ህገወጥ የውጭ ምንዛሪ እንቅስቃሴ ዙሪያ ያካሄደው ሰፋ ያለ ጥናት ዛሬ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ ሆኗል።

አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ለኢፕድ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የብሔራዊ ባንክ ገዢ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት፣ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት የሥራ ሃላፊዎች፣ ኮሚሽነሮች እንዲሁም የደኅንነትና የፀጥታ ተቋማት ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት የውይይት መድረክ የቀረበው ጥናት በዘርፉ ያሉትን ችግሮች፤ የተለያዩ የውጭ ሀገራትን ተሞክሮም ጭምር በጥልቀት የዳሰሳ ነበር።

የጥናቱ ግኝቶች መነሻ በማድረግ ህገወጥ የውጭ ምንዛሬና የገንዘብ ዝውውርን ሰንሰለት ለመበጠስ፣ የድርጊቱ ተዋናዮች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል የፖሊስ፣ የሥርዓትና የተጠያቂነት መፍትሄዎችን የሚጠቁሙ ምክረ ሐሳቦችና በቀጣይ ሊወሰዱ የሚገባቸውን ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎችንም አመላክቷል።

በጥናቱ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ህገወጥ የውጭ ምንዛሬ ገበያዎች የሀገርን ኢኮኖሚ በማዳከም፣የኑሮ ውድነትን በማናርና ሙስናን በማስፋፋት ሀገርን ለከፋ አደጋ እያጋለጡ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡

በህገወጥ ተግባራቱ መንግሥታዊና የግል ተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም የውጭ ሀገር ዜጎች ጭምር የሚሳተፉ መሆኑን የጠቆመው ጥናቱ፤ ከውጭ ሀገራት እስከ መሀል ሀገር የተዘረጋው ህገወጥ የጥቅም ትስስር በደላሎች፣ በድርጅቶች፣ በኩባንያዎችና በባንክ ሥርዓቱም ጭምር እንደሚደገፍ አመልክቷል። ይህም በሀገራችን እየታየ ላለው ቅጥ ያጣ የዋጋ ንረትና ማህበራዊ ችግር አንዱ ቁልፍ ምክንያት መሆኑን አሳይቷል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ እንዳሉት፤ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ህገወጥ የውጭ ምንዛሬ ንግድ የሀገርን ህልውናና የህዝብን ጥቅም እየተፈታተነ ያለ ብሔራዊ አደጋ መሆኑን በመረዳት አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ በልዩ ትኩረት እየሠራ ይገኛል፡፡

ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሁሉም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የንግዱ ማህበረሰብና ህዝቡ በትብብርና በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በጥናቱ የተለዩና ችግሩ በስፋት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች፣ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ገልጸዋል።

ህገወጥነትን በመቆጣጠር፣ የሀገርንና የህዝብን ህልውና በመታደግ ትግሉ ውስጥ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት፣የፋይናንስ ተቋማት፣የህግ አካላትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በሙሉ ተቀናጅተውና ተናበው ሊሠሩ እንደሚገባም አቶ ተመስገን ጥሩነህ አሳስበዋል፡፡

See also  በከሚሴ ትህነግ እየዘረፈ ነው፤ የኦሮሞ ታጣቂ የት ነው?

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከብሔራዊ ባንክ ጋር በመቀናጀትና ሌሎች አካላትን በማሳተፍ ችግሩ እስኪቀረፍ ድረስ በትኩረት እንደሚሠራም ጠቁመዋል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ህገወጥ የውጭ ምንዛሬ ንግድ ባንኩ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠርና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በአግባቡ ለማስተዳደር እንዳይችል እንቅፋት ሆነዋል፡፡ ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው።

የውጭ ምንዛሬ ብቻ ሳይሆን የብር እንቅስቃሴውም ከባንክ ሥርዓት ውጭ በመዘዋወር ላልተፈለገ ዓላማ እየዋለ መሆኑ ተደርሶበታል ያሉት የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ፤ በርካታ የብር ኖቶችን ከባንክ ሥርዓት ውጭ በማንቀሳቀስ ላልተፈለገ ዓላማ በሚያውሉ ወንጀለኞች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

በቀረበው ጥናት ላይ ውይይት ያደረጉ የብሄራዊ ባንክ ገዢን ጨምሮ የመድረኩ ተሳታፊዎች የቀረበው ጥናት አጠቃለይ ችግሩን፣የችግሩን ተዋን ያን እና የመፍትሄ ሐሳቦችን በሚገባ ያመላከተ በመሆኑ ለአገልግሎት መስሪያ ቤቱ ምስጋና ማቅረባቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አመልክቷል፡፡

Leave a Reply