በሙስና ወንጀል በተከሰሱ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ላይ የቅጣት ውሳኔ ተሰጠ

በሙስና ወንጀል በተከሰሱ ሁለት የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ላይ የቅጣት ውሳኔ ተሰጠ።

የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ሲሆን፥ የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው ተከሳሾች ዳኛ አዱኛ ነጋሳ እና ዳኛ አክሊሉ ዘሪሁን ይባላሉ።

የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በመዝገብ ቁጥር 27611 አቶ ዳዊት ገብረእግዛብሔር በተባሉ ባለሀብትና ቱፋ ጣፋ በተባለ ግለሰብ በነበረ የስራ ግንኙነት ሳይከፈል የቀረ 276 ሚሊየን ብር እዳ እና 9 ከመቶ ወለድ ማለትም 250 ሺህ ብር የግልግል ዳኝነት ላይ ክርክር ያልተደረገበት ማስረጃ ባልተመዘነበት ተገቢ ያልሆነ የአፈጻጸም ውሳኔ ሰጥተዋል በማለት ህዳር 28 ቀን 2014 ዓ.ም የከባድ ሙስና ወንጀል ክስ መስርቶባቸው ነበር።

ተከሳሾቹ ክሱ ከደረሳቸው በኋላ ታህሳስ 14 ቀን 2014 ዓ.ም በነበረ ቀጠሮ ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን ገልጸው የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ተከትሎ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ቀርበው ተሰምተዋል።

ፍርድ ቤቱም የምስክር ቃል መርምሮ አንደኛ ተከሳሽ ዳኛ አዱኛ ነጋሳ ከቀረቡባቸው ሁለት ክሶች መካከል በህገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ንብረት ህጋዊ አስመስሎ መጠቀም ወንጀል በሚመለከት በምስክር አልተረጋገጠም ሲል ነጻ ብሏቸው ነበር።

በሌላኛው ክስ ማለትም ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም የሙስና ወንጀል እንዲከላከሉ ሐምሌ 13 ቀን 2014 ዓ.ም ብይን ተሰጥቷል።

ሁለተኛ ተከሳሽ ዳኛ አክሊሉ ዘሪሁንን በተመለከተ በወቅቱ በተሰጠው የግልግል ዳኝነት ላይ ሀሰተኛ ሰነድ ስለመቅረቡ እንደማያውቁ በምስክር በመረጋገጡ የተከሰሱበት አንቀጽ ተቀይሮ በግል ተሰሚነት መነገድ አንቀጽ 16/1 ሀ መሰረት እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቶ ነበር።

ይህ አንቀጽ ዋስትናን ስለማያስከለክል በ20 ሺህ ብር ዋስ በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ዋስትና ተፈቅዶላቸውም ነበር። ተከሳሾቹም በተለያየ ጊዜ የመከላከያ ማስረጃ ያቀረቡ ቢሆንም የዐቃቤ ህግ ማስረጃን በተገቢው ማስተባበል አልቻሉም ተብለው የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

የጥፋተኝነት ፍርድ ከተላለፈባቸው በኋላ 1ኛ ተከሳሽ ዳኛ አዱኛ ከመከሰሳቸው በፊት በታማኝነት ለፍትህ ስርዓቱ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን እና ለሀገራዊ ልማት ያበረከቱትን በማስረጃ አስደግፈው አጠቃላይ 12 የቅጣት ማቅለያዎችን አቅርበዋል።

See also  በመሰረተ ልማት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች

2ኛ ተከሳሽ ዳኛ አክሊሉ ዘሪሁንም ከመከሰሳቸው በፊት ለፍትህ ስርዓቱ በታማኝነት ያበረከቱትን አስተዋጾ ጠቅሰው አጠቃላይ 10 የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በጽሁፍ አቅርበዋል።

ፍርድ ቤቱም ያቀረቡትን የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በመያዝ 1ኛ ተከሳሽ ዳኛ አዱኛ ነጋሳን ጥፋተኛ በተባሉበት አንቀጽ በ2 ዓመት ከ9 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጡ እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ ዳኛ አክሊሉ ዘሪሁን ጥፋተኛ በተባሉበት አንቀጽ በ1 አመት ከ6 ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል ሲል ኤፍቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply