Site icon ETHIOREVIEW

የአማራ ክልል ከትግራይ ጋር ሁሉንም ጉዳይ በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ለመጨረስ ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ

የአማራና ትግራይ ሕዝብ የጦርነትን ጠባሳ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ፣ ወንድማማች፣ አብሮ ሲኖር የነበረ ህዝብ በመሆኑና ወደፊትም በአብሮነት ስለሚቀጥል ማናቸውም ጉዳዮች በሰለጠነ አግባብ ሊያዙ እንደሚገባ ዶ/ር ይልቃል ከፋለ አስታወቁ። የጦርነት ጠብሳን በማከምና ህግን በማስከበር ረገድ ክልሉ ተጠምዶ እንደነበርም አመለከቱ።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶር ይልቃል ለክልሉ መገናኛ በሰጡት የወቅታዊ ሁኔታ መግለጫ “የአማራ እና የትግራይን ህዝብ ወንድማማችነት ለማስቀጠል በቁርጠኝነት እንሰራለን።የፖለቲካ ልዩነትን በውይይት ከመፍታት ይልቅ ጦርነትን አማራጭ ማድረግ መፍትሄ አልባ ኪሳራ እንደሚያደርስ አስተምሮናል” ብለዋል። የጦርነቱን ጠባሳ የሁለቱም ክልል ህዝብ ጠንቅቆ እንደሚያውቀው አመልክተው ዳግም ወደ ቀደመው የጦርነት ምስቅልቅል የመመለስ አሳብ ከቶውንም እንደማያዋጣ አስታውቀዋል።

“የአማራ ክልል ህዝብ የትግራይ ህዝብ ወንድሙ እንደሆነ ድሮም አብሮ ይኖር ነበር ወደፊትም ቢሆን አብሮ ለመኖር የተዘጋጀ ህዝብ ነው ፤ ከወንድሙ ጋር የሚያጋጥመውን ችግር በሰላም እና በድርድር ለመፍታት ነው የሚዘጋጀው የሚያስበው። የትግራይ ክልል ከኛ የሚጠይቀው ጉዳይ ካለ በሰላም በውይይት ፣ ከዚያም ባለፈ በህግ መፍታት እንችላለን ይሄን የሰለጠነ መንገድ ሁላችንም ተቀብለን መፈፀም አለብን” ሲሉ የተደመጡት ዶ/ር ይልቃል፣ ከጦርነቱ በሁዋላ የተዘረፈ፣ ስንልቦናው የተጎዳና ባዶ እጁን የቀረ ዜጋ መኖሩን ሲገልጹ ምስቅልቅሉ ከባድ እንደሆነ በማስታወስ ነው።

የአማራ ህዝብ ተወካይና ተቆርቋሪ መሆናቸውን የሚገልጹ በቅርቡ የክልሉንም ሆነ የፌደራል መንግስቱን በጉልበት እንደሚያስወገዱ መግለጫ ባሰራጩ ማግስት ነው ዶ/ር ከፍ አለ ይህን ከትግራይ ህዝብ ጋር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንደሚፈጠር ይፋ ያደረጉት።

“የአማራ ክልል መንግስትም ሆነ የአማራ ህዝብ ፣ የትግራይ ክልልም ሆነ ህዝብ የኔ ወንድም እና እህት ነው ብሎ የሚያስብ በችግሩ ጊዜ የሚደርስ በመሆኑ በዚያ መንፈስ ነው የምናየው ፤ ሰላም አብሮነትን የሚያፀና ፣ የሚያጠናክር ይሆናል ብለን እምነት እናደርጋለን” ሲሉ የተጀመረው የሰላም ስምምነት ተስፋን አመላክተዋል።

መንግስት በፖለቲካ ውሳኔ በፓርቲ ደረጃ ከየክልሉ የተፈናቀሉ ወደ ቀድሞ ቀያቸው እንዲመለሱ ውሳኔ መወሰኑና ውሳኔውን ለመተግበር ስምምነት መደረሱ ይታወሳል። ከጦነቱ በሁዋላ ይህንኑ ችግር ለመቅረፍና የዜጎችን እንግልት ለመቀነስ የአማራና የኦሮሚያ ክልል አመራሮች መካከል ልዩነት መፈጠሩም አይዘነጋም።
ርዕሰ መስተዳደሩ ሁሉም የአገሪቱ ህዝብ ለሰላም ዋጋ በመስጠት አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርግ፣ የፖለቲካ ልዩነት ያላቸው ሁሉ በሰላማዊ መንገድ ልዩነታቸውን እንዲያስተናግዱ ጥሪ አቅርበዋል።

ጦርነቱ ያስከተለውን ጠባሳና ውድመት፣ የስነልቦና ጫናና የኑሮ ውጥንቅጥ ማሰብ የማይወዱና የማይፍለጉ የስልጣን ጥመኞችና የሚዲያ ነጋዴዎች ሁለቱን ህዝብ ዳግም ለማባላት ሰፊ ዘመቻ በጀመሩበትና የሰላም ስምምነቱ የአማራን ህዝብ እንደሚጎዳ አብዝተው እየወተወቱ እንደሆነም አይዘነጋም። ይህ በመናበብ የሚደረግ የትርምስ ቅስቀሳ የጦርነት እሳት ለበላው ህዝብ ጥቅም ሳይሆን ለሳንቲም ለቀማና ለተራ የስልጣን ጥማት እንደሆነ በርካቶች እየገለጹ ነው።

Exit mobile version