በመቶ ሺህ የሚቆጠር ህገ ወጥ ግንባታ ፈረሰ፣ ይህ ሁሉ ሲሆን አስተዳደሩ የት ነበር?

” ለመኖሪያ ቤት ግንባታ ምቹ ያልሆኑ ቦታዎችን ጨምሮ ባህላዊና ታሪካዊ ስፍራዎች ጭምር በህገወጥ ግንባታ ተይዘዉ ነበር ” የመልካ ኖኖ ክፍለ ከተማ አርሶ አደሮች

በሸገር ከተማ አስተዳደር ምንም አይነት ህጋዊ ፈቃድ በሌላቸዉ ህገ ወጥ ግንባታዎች ላይ እየተወሰደ ያለዉ ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን በመልካ ኖኖ ክፍለ ከተማም ተመሳሳይ እርምጃ እየተወሰደ ነዉ።

በመልካ ኖኖ ክፍለ ከተማ የጂለ ጉለሌ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዲባባ ደበሌ እና አቶ ታምራት አበበ ለረጅም አመታት የቱሉ እሬቻ በአል ሲከበርበት የነበረዉ የጀሞ ተራራን ጨምሮ መኖሪያ ቤት ለመገንባት አስቸጋሪ የሆኑ ቦታዎች በሙሉ በህገ ወጥ ግንባታ ተይዘዉ እንደነበረ ይናገራሉ።

የሸገር ከተማ አስተዳደር ህገወጥ ግንባታን ለማስቆም እየወሰደ ያለዉ እርምጃ ተገቢ ነዉ ያሉት የአካባቢዉ አርሶ አደሮች በህገ ወጥ መንገድ የገነቡትን ቤት በፈቃዳቸዉ ማፍረሳቸዉን ተናግረዋል።

የመልካ ኖኖ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዲሪባ ሶሪ በወረዳዉ እየተካሄደ ያለዉን ህግ የማስከበር ስራን አስመልክቶ ለOBN HORN OF AFRICA እንደተናገሩት እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ህጋዊ ፈቃድ የሌላቸዉና በህገ ወጥ መንገድ የተገነቡ 22 ሺህ ቤቶችና አጥሮች መፍረሳቸዉን ተናግረዋል።

አብዛኞቹ ግንባታዎች ለመኖሪያ ቤት ምቹ ባልሆኑ ቦታዎች መገንባታቸዉን የተናገሩት አስተዳዳሪዉ ባህላዊና ታሪካ ስፍራዎች ጭምር በህገ ወጥ ግንባታዎች ተይዘዉ እንደነበር ተናግረዋል።

የመልካ ኖኖ ክፍለ ከተማ የመሬት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ብዙነህ ግርማ በበኩላቸዉ ምንም አይነት ህጋዊ ፈቃድ ለሌላቸዉ 38 ሺህ ህገወጥ ቤቶችና አጥሮች መፍረሳቸዉን እና 130 ሄክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ መመለሱን ተናግረዋል።

የመልካ ኖኖ ክፍለ ከተማ ዋና አስተዳዳሪ ወ/ሮ ሮዛ መሃመድ በህገ ወጥ ግንባታዎች ላይ እየተወሰደ ካለዉ እርምጃ ጎን ለጎን የመልካ ኖኖን ክፍለ ከተማ ልማትና ኢንቨስትመንት ለማሳደግ እየተሠራ ነዉ ብለዋል።

የክፍለ ከተማዉን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ስራ ላይ እያዋልን ነዉ ያሉት አስተዳዳሪዋ የክፍለ ከተማዉን የመሬት ሃብት በአግባቡ ለማስተዳደር ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በሁሉም ወረዳዎች ተግባራዊ እያደረግን ነዉ ብለዋል።

See also  የምስ.አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ስትራቴጂክ ከፍተኛ የአማካሪዎች መድረክ በአ.አ በመካሄድ ላይ ነው

በመልካ ኖኖ ክፍለ ከተማ ከ50 ሺህ በሚበልጡ ህገ ወጥ ግንባታዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ለመዉሰድ የታቀደ ሲሆን እስካሁን ድረስ 41 ሺህ 843 ህገ ወጥ ግንባታዎች ተለይተዉ በ37 ሺህ 951 ሺህ ግንባታዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ከክፍለ ከተማዉ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል።
ወንድማገኝ አሰፋ ኦቢኤን

Leave a Reply