የህብረት ስራ ኮሚሽን ገበያ የማረጋጋት ተልእኮውን በተገቢው እንዲወጣ ታዘዘ

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የህብረት ስራ ኮሚሽን ገበያ የማረጋጋት ተልእኮውን በተገቢው እንዲወጣ አሳስቧል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ይህን ያሳሰበው የህብረት ስራ ኮሚሽንን የ20015 በጀት ዓመት የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በገመገመበት ወቅት ነው፡፡

የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ሰለሞን ላሌ በሰጡት አስተያየት የህብረት ስራ ኮሚሽኑ የውስጥ አቅሙን ለመገንባት፤ የቁጠባ ስርዓትንና ብድር አቅርቦትን ለማሳደግ የጀመረውን ስራ በጥንካሬ አንስተው፤ ነገር ግን ትልቁ ተልዕኮው በሆነው ገበያ ማረጋጋት ላይ ያለው አፈጻጸም ዝቅተኛ በመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ የተከሰተው የኑሮ ውድነት መነሻው የምርት አቅርቦት እጥረት ሳይሆን ሰው ሰራሽ በመሆኑ ኮሚሽኑ ችግሩን ቀድሞ በማወቅ መዘጋጀት እንደነበረበት ያስታወሱት የተከበሩ አቶ ሰለሞን፤ የገበያ አሻጥሩ በቀጣይም ባሉት የክርስትና እና የሙስሊም የጾም መፍቻ በዓላት ላይ ሊያጋጥም ስለሚችል ኮሞሽኑ ችግሩን በሚፈታ መልኩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይጠበቅበታል ሲሉም አክለዋል፡፡

ሰብሳቢው አያይዘውም የህብረት ስራ ማህበራት አቅም እንዲኖራቸው ወደ ዩኒየን ማሳደግ እንደሚገባ እና ህብረት ስራ ማህበራት ላይ ከኦዲት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ተደጋጋሚ ጥያቄ ትኩረት ተሰጥቶት መፈታት እንዳለበትም አመላክተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ኮሚሽኑ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት ላይ በሚያጋጥሙ ብልሹ አሰራሮች ምክንያት ከሕዝብ የሚሰሙ ቅሬታዎችን ተከታትሎ መፍታት እንዳለበትና የመረጃ አደረጃጀቱንም ማዘመን እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል፡፡

ከውጭ ንግድ ለማግኘት ከታቀደው 36.3 ሚሊዮን ዶላር 27.6 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ቢቻልም አመርቂ ባለመሆኑ ኮሚሽኑ ለዘርፉ እድገት ትኩረት መስጠት እንዳለበት እና ህብረት ስራ ማህበራት የግብርና መሳሪያዎችን በማቅረብና የስራ እድል ፈጠራን በማሳለጥ ረገድ የጀመሩትን ተግባር የበለጠ እንዲያጠናክሩ የቋሚ ኮሚቴው አባላት አሳስበዋል፡፡

የፌደራል ህብረት ስራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አብዲ መሀመድ እና የስራ ባልደረቦቻቸው በሰጡት አስተያየት የገንዘብ ቁጠባ ተቋማትን ለማስፋፋትና ቁጠባን ለማበረታታት እንዲሁም ከስራ እድል ፈጠራ አኳያ ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ለመፍጠር በትኩረት እየሰሩ መሆኑን አስታውሰው፤ ህብረት ስራ ማህበራት አምራቹም ሸማቹም በማይጎዱበት ሁኔታ ትስስር እንዲፈጥሩ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

See also  ‘ድንገቴ የልብ ምጥ’ በሽታ ምንድነው?

የገበያ ማረጋጋት ስራው አሻጥረኛ ነጋዴዎች ከደላላ ጋር በመሆን በፈጠሩት ችግር ምክንያት የታሰበውን ያህል ባይሆንም ማህበራት በተለይ አዲስ አበባ ከተማ ላይ ያላቸውን ለሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ እያከፋፈሉ መሆኑን ጠቁመው፤ ችግሩ በዋናነት የሚጎዳው የመንግስት ሰራተኛውን በመሆኑ ለመንግስት ተቋማት እያቀረቡ እንደሆነና ነገር ግን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አቅም ያላቸው ማህበራት እንዲኖሩ ለማድረግ ትኩረት መስጠት አለበት ብለዋል፡፡

አርብቶ አደር አካባቢን በስራ ባህሪያቸው መሰረት ተደራሽ ለማድረግ እንዲቻል በሚኒስቴር ደረጃም ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሆነ፣ የቡና ኤክስፖርት ምርትና የቅመማ-ቅመም ግብይትን ለማሳደግ እንዲሁም የማዳበሪያ አቅርቦት ላይ ያለውን የመጋዘን ዝግጅት ችግር ለመፍታት ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው ያሉት ኃላፊዎቹ፤ ከኦዲት ጋር ያለው ችግር ከደሞዝና ጥቅማ-ጥቅም ጋር ተያይዞ የባለሙያ እጥረት በማጋጠሙ ስለሆነ ቋሚ ኮሚቴው የበኩሉን እንዲያግዛቸው ጠይቀዋል፡፡

በ ድረስ ገብሬ – (ዜና ፓርላማ)፤ መጋቢት 27፣ 2015 ዓ.ም

Leave a Reply