“ጉዳይ ለማስፈፀም ቢጫ ትኬት ቁረጡ” በማለት በተለያዩ አካባቢዎች በተሽከርካሪ እየተንቀሳቀሱ የማታለል ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 9 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለፀ።
ተጠርጣሪዎቹ ወንጀሉን የሚፈፅሙት የኢሚግሬሽን፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርና የቦሌ ኤርፖርት ጉምሩክ ሰራተኛና የስራ ኃላፊ በመምሰል እንደሆነ ፖሊስ ገልጿል።
ከአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል እና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዘርፍ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በኢሚግሬሽንና በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ጉዳይ ለማስፈፀም እንዲሁም በቦሌ ኤርፖርት ጉምሩክ ከካርጎ ዕቃ ለማውጣት የሚመጡ ግለሰቦችን ለይተው እና ተከታትለው በመቅረብ ጉዳያቸውን በቀላሉ እንደሚያስጨርሱላቸው ካሳመኗቸው በኋላ ተጨማሪ የማታለያ ዘዴዎችን በመጠቀም ወንጀሉን ሲፈፅሙ የነበሩ ናቸው፡፡
በተጠቀሱት ተቋማት ለጉዳይ የሚመጡት ተገልጋዬች የያዙትን ሞባይል ስልክ ፣ ገንዘብ፣ ቦርሳ፣ እንዲሁም ያደረጉትን ጌጣጌጥ በትኩረት ከተመለከቱ በኋላ ተጠርጣዎቹ በመረጡት ሰው ላይ ወንጀሉን እንደሚፈፅሙ የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልፆ ለዚህም ” ወደ ተቋሙ ውስጥ ለመግባት ቢጫ ትኬት ያስፈልጋል፤ ትኬቱ ከሌላችሁ ወደ ውስጥ መግባት ስለማይቻል በ55 ብር ቆርጣችሁ ኑ ፤ ልትቆርጡ ስትገቡ ግን ምንም አይነት ገንዘብም ሆነ ንብረት ይዞ መግባት ስለማይቻል እዚህ አስቀምጣችሁ ሂዱ“ የሚል የማታለያ ዘዴ በመጠቀም ለወንጀል ተግባር በሚንቀሳቀሱበት ተሽከርካሪ ውስጥ ንብረቱ እንዲቀመጥ ካደረጉ በኋላ የግል ተበዳይ የተነገራቸውን አምነው ትኬት ለመቁረጥ ወደ ውስጥ ሲገቡ ተጠርጣዎቹ ንብረቱን ይዘው እንደሚሰወሩ በምርመራ ተረጋግጧል፡፡
ፖሊስ እንዲህ አይነቱን ወንጀል ለመከላከል እና የፈፃሚዎቹን ማንነት አውቆ ለመያዝ በተለይም ወንጀሉ ይፈፀምባቸዋል በተባሉ አካባቢዎች ላይ የተጠናከረ ጥበቃ እና ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን የጠቀሰው የአዲስ አበባ ፖሊስ በወንጀሉ ተሳትፎ አላቸው የተባሉ 9 ግለሰቦችንና ለወንጀሉ ተግባር ሲጠቀሙባቸው የነበሩ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-A 75522 አ.አ እና የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-B 08277 አ.አ ተሽከርካሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል የምርመራ ስራው መቀጠሉን ገልጿል፡፡
ለተለያዩ ጉዳዮች ወደተለያዩ ተቋማት የሚሄዱ የህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳይ እናስፈፅምላችኋለን እያሉ መሰል የወንጀል ተግባር ለመፈፀም ከሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ያስገነዘበው የአዲስ አበባ ፖሊስ የቁጥጥር እና የክትትል ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለፅ ተመሳሳይ ወንጀል የተፈፀመባቸው ግለሰቦች አዲስ አበባ ፖሊስ ዋናው መስሪያ ቤት በአካል በመቅረብ ከተጠርጣዎች መካከል መምረጥና ማረጋገጥ እንደሚችሉ አሳስቧል፡፡
(ኢ ፕ ድ)